ለጡረታ እየተዘጋጁ ያሉት አለቃ ሰራተኞቻቸውን ለማመስገን 13 ሚሊዮን ዶላር ሊሰጡ ነው

ዴቪድ ስቲቨንስ

በዩናይትድ ኪንግደም ጡረታ ለመውጣት በዝግጅት ያሉ አለቃ ሰራተኞቻቸውን ለማመስገን 13 ሚሊዮን ዶላር፣ 480 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሊሰጡ ነው።

አድማይራል የተባለው አለም አቀፍ ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ዴቪድ ስቲቨንስና ባለቤታቸው ሄዘር ለሰራተኞቻቸው በስጦታ መልክ የሚሰጡት ብር በሳውዝ ዌልስ ለሚገኙት 7 ሺህ 500 ሰራተኞችና በተለያዩ አገራት ደግሞ ላሉ 3 ሺህ ሰራተኞች ይከፋፈላል ተብሏል።

ለቋሚ ሰራተኞች 1 ሺህ 300 ዶላር (48 ሺህ ብር) እንዲሁም ለጊዜያዊ ሰራተኞች ግማሹን 24 ሺህ ብር ስጦታ ይሰጣቸዋል።

ዴቪድ ስቲቨንስ አድማይራል የተሰኘውን አለም አቀፍ የመኪናና የሞተር ኢንሹራንስ ኩባንያን የመሰረቱትና ያቋቋሙት ከባለቤታቸው ጋር በጎሮጎሳውያኑ 1991 ነበር።

"ከእንደነዚህ አይነት ምርጥ ሰራተኞች ጋር አብሬ በመስራቴ እድለኛ ነኝ፤ እኮራባቸዋለሁ" ያሉት ኃላፊው "ሰራተኞቼን በዚህ መንገድ ማመስገንም ትክክለኛ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።

"በነሱ የስራ ትጉህነትና ጠንካራ ሰራተኝነት አድማይራል ከትንሽ ነገር ተነስቶ በአለም አቀፍ ደረጃ 11 ሺህ ሰራተኞች ያሉት ትልቅ ኩባንያ ሊሆን የበቃው" በማለት ስለ ሰራተኞቻቸው መስክረዋል።

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ ምርጥ የሚባሉት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጠቅሰው በሳቸውና በባለቤታቸውም ስም ሰራተኞቻቸውን በሙሉ አመስግነዋል።

ከዚህ ቀደምም ሄንሪ ኤንግልሃርድት የተባሉትና ከዴቪድ ስቲቨንስ ጋር አድማይራልን የመሰረቱት የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚም ከአራት አመት በፊት ጡረታ ሲወጡ 48 ሺህ ብር ለእያንዳንዱ ሰራተኛ ሰጥተው ነበር።

በወቅቱም ለአጠቃላይ ሰራተኞቻቸውም የገንዘብ ስጦታውን ለመስጠት ከ 9 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርገዋል።

ዴቪድ ስቲቨንስም በሚሌና ሞንዲኒ ይተካ ተብሏል።

አድማይራል የተባለው ኩባንያ በካርዲግ ግዛት የመኪና ኢንሹራንስን በመሸጥ ሲጀመር 57 ሰራተኞች ብቻ ነበሩት።

ከዩናይትንድ ኪንግደም ቢሮዎቹ በተጨማሪ በስፔን፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ አሜሪካና ህንድ ቅርንጫፎች አሉት።