የኢንሹራንስ ገንዘብ ለማግኘት እጇን የቆረጠችው ታሰረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢንሹራንስ ክፍያ ለማግኘት በማሰብ ሆን ብላ እጇን በገዛ እጇ የቆረጠችው ስሎቬኒያዊት ጥፋተኛ ተብላ ሁለት ዓመት ተፈረደባት።
በዋና ከተማዋ ጁብልጃና የሚገኘው ፍርድ ቤት እንደገለጸው ጁሊያ አድሌሲክ የተባለቸው የ 22 ዓመት ወጣት ከከስተቱ በፊት በያዝነው ዓመት ብቻ አምስት ጊዜ የኢንሹራንስ ክፍያ ተቀብላለች።
በዚህ ወቅት ደግሞ እጇን ሆን ብላ ከቆረጠች በኋላ የዛፍ ቅርንጫፍ ስትቆርጥ አደጋ እንዳጋጠማት በመናገር የኢንሹራንስ ድርጅቱን ለማጭበርበር ሞክራለች ብሏል ፍርድ ቤቱ።
ጁሊያ አድሌሲክ በካሳ መልክ ከኢንሹራንስ ኩባንያው ልትቀበለው ያሰበችው ገንዘብ እስከ 1.6 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ነው።
በአሁኑ ወቅት ግን ጁሊያ ሁለት ዓመት እስር የተፈረደባት ሲሆን የፍቅር አጋሯ ደግሞ ተባባሪ ነው በሚል የሶስት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ጁሊያና በርካታ ዘመዶቿ ወደ ሆስፒታል በመሄድ እጇ እንደተቆረጠ ያስታወቁት ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት 2019 ነበር።
ፍርድ ቤቱ በሰጠው መረጃ መረጃ መሰረት ጁሊያና የፍቅር ጓደኛዋ እጇን ከቆረጡ በኋላ ሆነ ብለው የተቆረጠውን አካል ወደ ሆስፒታል ሳይወስዱት ቀርተዋል። ምክንያታቸው ደግሞ እጇ ተመልሶ እንዳይሰፋና ጉዳቱ ዘላቂ እንዲሆን በማሰብ ነው ብሏል ፍርድ ቤቱ።
ነገር ግን የጤና ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ የተቆረጠው እጅ ተመልሶ መሰፋት ችሏል።
አቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው የክስ ንባብ ላይ የጁሊያ የፍቅር ጓደኛ እጇን ከመቆረጣቸው በፊት ባሉት ቀናት ስለ አርቴፊሻል እጅ በይነ መረብ ላይ መረጃ ሲፈልግ ነበር ብሏል።
አክሎም የደረሰው ጉዳት ሆን ብሎ የተደረገ ለመሆኑ ይሄ ጥሩ ማስረጃ ነው ሲል ክሱን አሰምቷል።
በተጨማሪ ደግሞ የጁሊያ የፍቅር ጓደኛ ወላጅ አባትም በወንጀሉ ተሳትፎ ነበራቸው ተብሎ ምርመራ ሲደርጋበቸው ነበረ ሲሆን ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የአንድ ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።
ሙሉ የፍርድ ሂደቱ ሲከናወን ግን ጁሊያና የፍቅር ጓደኛዋ ወንጀሉን አልፈጸምንም ብለው ተከራክረዋል።












