ኮሮናቫይረስ ፡ ተስፋ የተጣለበት የኦክስፎርዱ የኮቪድ-19 ክትባት ለምን እንዲቆም ተደረገ?

አንዲት ባለሙያ በላብራቶሪ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Oxford University / John Cairns

የምስሉ መግለጫ, አስትራዜኔካ እና ኦክስፎርድ በጋራ የኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት እየሰሩ ነው

አስትራዜኔካና ኦክስፎርድ ተባብረው ከፊት ቀድመው እየሰሩ ነበር። ከክትባት ሙከራዎች ሁሉ ተስፋ ሰጪዎቹ ሆነው ነበር። ዓለም ትንፋሹን ሰብስቦ እየጠበቃቸው ነበር።

ድንገት እክል ገጠማቸው። አንድ ሰው ታመመባቸው። ከዚያም ሁሉም ነገር ቆመ። ለጊዜው ነው ታዲያ።

ቢሆንም ዜናው ብዙ መንግሥታትን አስደንግጧል።

ምክንያቱም በወረርሽኝ የተፍረከረከችውን ዓለማችንን ይታደጋል ተብሎ ነበር የሚጠበቀው፤ክትባቱ።

የነኦክስፎርድ ክትባት ምንም እክል እንዲገጥመው አይፈለግም ነበር። በተለይ ዶናልድ ትራምፕ ከኅዳር በፊት ይደርስልኛል ብለው በተስፋ እየጠበቁ ነበር።

አውስትራሊያና እንግሊዝ ከወዲሁ ክፍያ ፈጽመው ነበር። አሜሪካም እንዲሁ። በርካታ መድኃኒት ፋብሪካዎች የነኦክስፎርድ ክትባት ይሳካል በሚል ማምረቻ ማሽናቸውን መወልወል ጀምረውም ነበር። ለዚህም ነው ይህ ሙከራ እንዲቆም መደረጉ ድንጋጤ የፈጠረው።

ደግሞ ከብዙ ክትባቶች በተሻለ ይህኛው ክትባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነበር። በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ፣ በብራዚልና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ በጎ ፍቃደኞች ክትባቱን ወስደውታል።

እነዚህ ሰዎች በድምሩ 30 ሺህ ይሆናሉ። ከእነዚህ መካከል አንድ ሰው መታመሙ ነው አሁን ያ ሁሉ የተደከመበት ክትባት እንዲቆም ያደረገው፤ ለጊዜውም ቢሆን።

አስትራዜኔካ ግን "እረ ምንም መደናገጥ አያስፈልግም፤ በመድኃኒት ሙከራ ጥርሳችንን ነቅለንበታል። ይህ ሁልጊዜም የሚያጋጥም ነገር ነው እኮ" ብሏል።

ጨምሮም "ምርምሩ የቆመውም ለጊዜው ነው። ደግሞ ታማሚው በምን ምክንያት እንደታመመ አልታወቀም። ምናልባትም ከክትባቱ ጋር ተያይዞም ላይሆን ይችላል" ብለዋል።

ለመሆኑ ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ በመድኃኒት ፍብረካ ሂደት ምን ያህል የተለመደ ነው? የነኦክስፎርድ ሙከራ ከወዲሁ ከሽፎ ይሆን?

በሙከራው ከተሳተፉ ሰዎች መካከል አንዷ ስትከተብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የክትባቱ ሙከራ በብራዚል፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በአሜሪካና በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 30 ሺህ ሰዎችን አሳትፏል።

ምንም ማለት ላይሆን ይችላል፤ ሊሆንም ይችላል

አስትራዜኔካ ግዙፍ መድኃኒት አምራች ነው፡፡ ከኦክስፎርድ ጋር በጥምረት እየሰሩ መሆኑ ከተነገረ ጀምሮ ጥሩ እምርታ እያሳዩ ነው የመጡት። ዓለም ተስፋ ያደረገውም በሁለቱ ላይ ነው።

ምንም እንኳ እነሱ ሲደናቀፉ ዓለም ክው ብሎ መቅረቱ የሚያስገርም ባይሆንም አሁን በሙከራ ለይ ካሉ 24 የሚሆኑ ክትባቶች ውስጥ እንደ ኦክስፎርድና አስትራዜኔካ መስመሩን ተከትሎ፣ ሳይንሱን ሳያዛንፍ እየሄደ ያለ የለም።

ለምሳሌ ሩሲያ ጣጣዬን ጨርሻለሁ ብትልም ያመናት የለም። የሩሲያን መድኃኒት ፈብርኪያለው ፉከራ ዓለም ቁብም አልሰጠውም። ወይም አላመነበትም። ሩሲያዊያን ግን እኛ እንዲያውም ለሕዝባችን ማደል ልንጀምር ነው እያሉ ነው።

ፑቲን ያልታመኑት እንዲሁ ምዕራቡ ስለማይወዳቸው ብቻ አይደለም። አንድን መድኃኒት ለመፈብረክ በአቋራጭ የማይኬድባቸው የጊዜ ሰሌዳዎች አሉ። ፑቲን ወታደራዊ የቆረጣ ስልታቸውን ወደ መድኃኒት ሳያመጡት አልቀሩም።

የዚህ የኦክስፎርድና አስትራዜኔካ ጥምረት እክል እንደገጠመው ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው ስታትኒውስ ነው። በዚህ ዘገባው እንዳብራራው እክሉ የተፈጠረው ከ30 ሺህ ክትባት ወሳጆች መካከል አንድ በዚያው በዩናይትድ ኪንግደም የምትገኝ ተሳታፊ መታመሟን ተከትሎ ነው። ሕመሟ ደግሞ ከክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይቸላል የሚል ስጋት አለ።

ከዚህ ከፍ ያለ ዝርዝር መረጃ የለም። ሆኖም ስታትኒውስ የአስትራዜኔካ ምንጮቼ ነገሩኝ እንዳለው ታማሚዋ አሁን እያገገመች ነው።

አስትራዜኔካ ባወጣው መግለጫ "ምርምሩ እንዲቆም የሆነው አሰራሩ እንዲያ እንዲሆን ስለሚያዝ ነው ብሏል። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲከሰቱ የጥንቃቄ ሂደቶች በድጋሚ ይፈተሸሉ። የተለመደ አሰራር ነው" ብሏል። ይህ ሂደትም ቀናትን ሊወስድ ይችላል።

የክትባቱ ብልቃጥ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በአንድ ሰው ላይ ያልተጠበቀ ውጤት ከታየ የክትባት ሙከራው እንዲቆም ተደርጎ መርምራ ይደረጋል

ይህ በክትባት ፈጠራ ሂደት ምን ያህል የተለመደ ነገር ነው?

ክስተቱ ተሰምቶ የማያውቅ ነገር አይደለም። "አንድ መድኃኒት ሦስተኛ ምዕራፍ ሙከራ ላይ ካለና ከሚሞከርባቸው ሰዎች አንድ እንኳ ሰው ሆስፒታል ቢገባ ወዲያውኑ ሙከራ እንዲቆም ይደረጋል" ተብሏል።

ገለልተኛ ወገን ምርምሩና ሙከራው የሄደበትን መንገድ ይፈትሻል እንጂ። ሙከራው ይቆማል ማለት ግን አይደለም።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ "በትልልቅ የሕክምና ሙከራዎች ሂደት ሰዎች መታመማቸው የለመደ ነው። ይህ ሲሆን ሁልጊዜም ቢሆን ገለልተኛ አካል የሙከራ ሂደቱን ይፈትሻል። እየሆነ ያለውም ይኸው ነው" ብለዋል።

ለበኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት በሚደረግ ሂደት ውስጥ ሰው ታሞ ሙከራ እንዲቆም ሲደረግም ይህ የመጀመርያው አይደለም።

በሚያዝያ ወር በተመሳሳይ አንድ ሰው እንዲሁ ታሞ የክትባት ሙከራው እንዲቆም ተደርጎ ነበር።

ሰው እንዲህ እየታመመ ክትባቱን መውሰድ ችግር አይኖረውም?

ይህ ዜና ገና ከመውጣቱ ጸረ-ክትባት አቀንቃኞች "ምን ብለናችሁ ነበር" ማለት ጀመሩ። ክትባቱ ይቅርብን፣ የዓለምን ሕዝብ ሊጨርሱ ነው ሐሳባቸው" ብለው አስወሩ።

ኦክስፎርድና አስትራዜኔካ በጋራ በሰጡት መግለጫ ግን ይህ የሚደረገው አስተማማኝ ክትባት ለመፈብረክ ሲባል ነው።

ምርምሩ እንዲቆም መደረጉ ምን ያህል ለሰዎች ጤና ቅድሚያ እንደሚሰጥም ማሳያ ነው ብለዋል።

እንዲያውም ባለፈው ማክሰኞ ለኮሮናቫይረስ ክትባት እያመረቱ የሚገኙ የዓለም መድኃኒት አምራቾች፤ ዝነኛው አስትራዜኔካን ጨምሮ ማለት ነው፤ የሰዎችን ጤና ደኅንነት ለማስቀደም የስምምነት ሰነድ ፈርመዋል። ይህም ታሪካዊ ነው።

ይህንን ፊርማ ካኖሩት መካከል ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ ባዮኤንቴክ፣ ግላክሶስሚዝክላይን፣ መርክ ሞደርና፣ ሳኖፊ እና ኖቫቫክስ ይገኙበታል።

የስምምነት ሰነዱ ቅድሚያ ለገበያ ሳይሆን ለሳይንስ እንዲሰጡ የሚያስገደድ ነው።

እኛ ፈራሚዎች ለሥነ ሣይንሳዊ ዘዴ ታማኝ ሆነን፣ ሥነ ምግባር ኖሮን እንሰራለን ብለው ነው የተስማሙት። ከዚህም በተጨማሪ ክትባቱ ሲገኝ ለዓለም ሕዝቦች በበቂ እንዲዳረስ እንደሚያግዙም ቃል ገብተዋል።

አንዲት የሩሲያ ባለሙያ በላብራቶሪ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ የኮሮናቫይረስ ለማግኘት እየተቃረበች መሆኗን አሳውቃለች

መድኃኒቱን ለማግኘት ምን ያህል ተቃርበናል

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው አሁን በመላው ዓለም 180 ክትባቶች እየተሞከሩ ነው። ነገር ግን አንዳቸውም የክሊኒካል ሂደትን አላጠናቀቁም።

ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት ድርጅት እንደሚለው ሳይንሳዊውን የመድኃኒት ፍብረካ ተከትለው በዚህ ዓመት ሊደርሱ የሚችሉ ክትባቶች አይኖሩም።

ድርጅቱ እዚህ ይህን ከወዲሁ እንዲደመድም ያስቻለው ታዲያ አንድን መድኃኒት ለማምረት የሚወስደውን መደበኛ ጊዜ ከግምት በማስገባት ነው።

የአስትራዜኔካና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥምረት የመጀመርያው ፈብራኪ ለመሆን ሰፊ ዕድል አለው የተባለው እስከአሁን ያሉ ሂደቶችን (ምዕራፍ አንድ እና ሁለትን) በአጥጋቢ ሁኔታ ማለፍ በመቻሉ ነው።

ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ ከገባም ቆይቷል፤ መውጣት ነው አሁን ያቃተው። 30 ሺህ ሰዎች ላይ ክትባቱ ተሞክሮባቸው የሚያሳዩት ውጤት እየተጠበቀ ሳለ ነው አንድ ሰው መታመሙ ነገሩን ያሰናከለው።

በተለመደው ጥብቅ የመድኃኒት ግኝት ሳይሳዊ አካሄድ ምዕራፍ ሦስት የሙከራ ሂደት ብዙ ሺህ ፍቃደኞች ላይ መድኃኒቱ የሚሞከርበት ሂደት ሲሆን ይህ ምዕራፍ እስኪጠናቀቅ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል።

ኮሮና
Banner