ፕሬዝደንት ማዱሮ የአሜሪካ ሰላይ ነዳጅ ማውጫ ስፍራ ላይ ያዝን አሉ

የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ የአሜሪካ ሰላይ ነዳጅ ማውጫ ስፍራ ላይ በቁጥጥር ሥር አዋልን አሉ።

ፕሬዝደንቱ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ለህዝባቸው እንደተናገሩት የአሜሪካ ሰላይ ነው ያሉት ግለሰብ ከጦር መሳሪያ እና ከፍተኛ መጠን ካለው ጥሬ ገንዘብ ጋር የነዳጅ ማውጫ እና ማቀነባባሪያ ስፍራ አቅራቢያ ተይዟል።

ማዱሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው አሜሪካዊ “የአሜሪካ የጦር አባል እና መቀመጫውን በኢራቅ የሲአይኤ ቢሮ ያደረገ ነው” ብለዋል። አሜሪካ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

ፕሬዝደንቱ ጨምረውም በቅርቡ የቬንዙዌላ ባለስልጣናት በነዳጅ ማውጫ ጣቢያዎች ላይ ፍንዳታ ለመፈጸም የተሸረበን ሴራ ማክሸፍ ችለዋል ብለዋል።

ከአንድ ወር በፊት የቬንዙዌላ ፍርድ ቤት ሁለት የቀድሞ የአሜሪካ ጦር አባላት ላይ ፕሬዝደንቱን በኃይል ከስልጣን ለማስወገድ ሞክረዋል በሚል ክስ የ20 ዓመት እስር በይኗል።

ሁለቱ ፍርደኞች ግንቦት ወር ላይ ከሌሎች 11 ሰዎች ጋር ከጎረቤት አገር ኮሎምቢያ በባህር በኩል ወደ ቬንዙዌላ ተደብቀው ሊገቡ ሲሉ ነበር በቬንዙዌላ ጦር በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

አሜሪካ ለፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ እውቅና አትሰጥም። ይልቁንም ዋሽንግተን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሁሃን ጓይዶን ነው ሕጋዊ የቬንዙዌላ ፕሬዝደንት አደርጋ የምትቆጥረው።

በአሜሪካ እና በቬንዙዌላ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እየሻከረ መጥቷል። ማዱሮ አሜሪካ በቬንዙዌላ ፖለቲካ ውስጥ እጇን በማስገባት ነዳጅን ጨምሮ የቬንዙዌላን የተፈጥሮ ሃብት ለመበዝበዝ ጥረት እያደረገች ነው ሲሉ ይከሳሉ።

አሜሪካ እና ጓይዶ በበኩላቸው ቬንዙዌላ ለተዘፈቀችበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማዱሮን ተጠያቂ ያደርጋሉ።