ቤቶች ልማት ለተፈናቃይ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ ቤት እያስተላለፍኩ ነው አለ

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ በልማት ምክንያት የእርሻ መሬታቸውን ላጡ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ ቤቶች እያስተላልፍኩ ነው አለ።
ቀደም ሲል ቢቢሲ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች አነጋግሮ ባወጣው ዘገባ ላይ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች የተሰጠን የጋራ መኖሪያ ቤት የለም ማለታቸውን ተከትሎ የከተማው ቤቶች ልማት ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው በሰጡት በሰጡት ምላሽ ቤቶቹ እተላለፉ መሆኑን አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ኮሚሽንም የከተማው ካቢኔ ግንቦት 2011 ላይ የእርሻ መሬታቸውን በልማት ምክንያት ላጡ አርሶ አደሮች ከ23 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤት ተላልፎ እንዲሰጥ ቢወስንም የጋራ መኖሪያ ቤቱ ተላልፎ አልተሰጣቸውም ብሎ ነበር።
ዘገባው ከወጣ በኋላ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው በዘገባው ላይ አስተያየታቸው እንዲካተት የጠየቁ ሲሆን በዚህም ቢሮ ወደ 17 ሺህ ለሚጠጉ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ ቤት ማስተላለፉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአርሶ አደሮች አቤቱታ
በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ አርሰው ያድሩ የነበሩ ገበሬዎች፣ በከተማዋ መስፋፋት እና ለልማት በሚል ምክንያት ከእርሻ መሬታቸው የተፈናቀሉ በርካቶች መሆናቸው ይነገራል።
"እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ገበሬ ባዶ እጁን ነው ያለው። ይህ ፈጣሪ የሚያውቀው እውነት ነው" በማለት የተናገሩት ከመሬታቸው ተፈናቅለው የጋራ መኖሪያ ቤት ይሰጣቸዋል ተብለው የጋራ መኖሪያ ቤት እንዳልተሰጣቸው ለቢቢሲ ቃላቸው ከሰጡት አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው።
ከንፋስ ስልክ፣ ቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች ለልማት በሚል ምክንያት ከይዞታቸው የተፈናቀሉ ገበሬዎች ጉዳያቸው መፍትሄ እንዳላገኘ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ዶሮ እንኳ የለንም"
አቶ ተሾመ ፈይሳ በየካ ክፍለ ከተማ 15 ሄክታር መሬታቸው የካ ኮንዶሚኒም ሲሰራ በ2004 ዓ.ም እንተወሰደባቸው ይናገራሉ።
አቶ ተሾመ እንደሚሉት ከሆነ የእርሻ መሬታቸውን ከተነጠቁ ወዲህ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ገልፀዋል።
"የእኔ እና የአባቴን 15 ሄክታር መሬት ሲወስዱብን 1 ካሬ መሬትን በ15 ብር ነው ያሰሉት። እኛ ወደ 14 የቤተሰብ አባላት እንሆናለን። በዛን ወቅት ለአጨዳ የደረሰ እህል እስክናነሳ እንኳን አልጠበቁንም። እህላችንን በዶዘር ነው የጠረጉት።"
ከእርሻ ውጪ ሌላ ክህሎት እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ ተሾመ፤ የእርሻ መሬታቸው ከተወሰደ ወዲህ ላለፉት 8 ዓመታት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
"መሬታችን ከተወሰደ በኋላ እርሻ የለንም፣ ከብት ለንም። ዶሮ እንኳን የለንም። እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ገበሬ ባዶ እጁን ነው ያለው። ይህ ፈጣሪ እና ይህች ምድር የሚያውቁት ሃቅ ነው።" ይላሉ።

አቶ ተሾመ ጨምረው እንደተናገሩት እርሳቸው እና ጎረቤቶቻቸው የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ እንዳልቻሉ ያስረዳሉ።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የነበሩት አቶ ታዬ ከበደም በተመሳሳይ የእርሻ መሬታቸው ለልማት በሚል ምክንያት ከተነጠቁ በኋላ ለችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ከ1995 ጀምሮ ለልማት በሚል ምክንያት የእርሳቸው እና የጎረቤቶቻቸው መሬት ስለተወሰደባቸው፤ ከአዲስ አበባ ተሰድደው መውጣታቸውን አቶ ታዬ ይናገራሉ።
"እኛ አከባቢ መፈናቀል የቆየ ነገር ነው። አያቶቻችንም ከመሃል ከተማ ተገፍተው ነው ወደ ከተማ ዙሪያ የወጡት። አገር ለቀው የተሰደዱም አሉ" በማለት ይናገራሉ።
መሬታቸው የተነጠቁ ገበሬዎች እና የተወሰነ የእርሻ መሬት ያላቸው ገበሬዎች በከተማ ግብርና እንዲሰማሩ ከ2012 ጀምሮ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አርሶ አደሮቹ ጨምረው ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ ግን በቀረችን መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ትከሉበት ብለውን ትንሽ እንቅስቃሴ ተጀምሯል እንጂ ያገኘነው ነገር የለም ይላሉ።
የከተማ አስተዳደሩ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፈትያ መሐመድ በአንድ ዓመት ውስጥ ከይዞታቸው የተፈናቀሉ 67 ሺህ አርሶ አደሮች መረጃ መሰብሰቡን ይናገራሉ።
ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ በ2012 ዓ.ም መሬታቸው ከተወሰደባቸው ገበሬዎች መካከል 1655 የሚሆኑት መጠለያ እና ገቢ ምንጭ በማጣታቸው በእምነት ተቋማት እና መንገድ ላይ በልመና ህይወታቸውን እየገፉ ነው።
"እነዚህ አርሶ አደሮች መሬታቸው ከተወሰደ በኋላ ወዴት እንዳሉ የሚያውቅ አካል የለም፤ መረጃው ያለው ማንም የለም። የተከናወነው ነገር ገበሬዎቹን የማፈናቀል ስራ ነው የሚመስለው" ይላሉ ኮሚሽነሯ።
ከይዞታቸው የተፈናቀሉት አርሶ አደሮች ተበታትነው ይኑሩ እንጂ የአንድ አካባቢ ጎረቤታሞች የነበሩት አርሶ አደሮች ማን የት እንዳለ ያውቃሉ።
ኮሚሽነር ፈቲያም ስለ አርሶ አደሮቹ መረጃ መሰብሰብ የተቻለው በእነዚህ አርሶ አደሮች አማካኝነት እያጠያየቁ ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ እንደሆነ ይናገራሉ።
ኮሚሽኑ መረጃ የተሰበሰበባቸው 67ሺህ አርሶ አደሮች ከቀደመ ኑሯቸው ዝቅ ያለ ደረጃ ላይ ቢገኙም 1ሺህ 655 የሚሆኑት ግን በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ እና በልመና የሚተዳደሩም እንዳሉ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ለእነዚህ ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጡት አርሶ አደሮች በየወሩ ገንዘብ እንዲያገኙ በማድረግ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ 2011 ግንቦት ወር የእርሻ መሬታቸውን የተነጠቁ ገበሬዎች ከ23ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲተላለፍላቸው ቢወስንም ቢቢሲ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ግን የጋራ መኖሪያ ቤቱ ተላልፎ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ወደ 20ሺህ የሚጠጉ ጋራ መኖሪያ ቤቶች በልማት ምክንያት ከእርሻ መሬታቸው ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች መሰጠቱን ተናግረው ነበር።
ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በቅርቡ በኋላ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በከተማው ካቢኔ ውሳኔ መሠረት ለ20ሺህ አርሶ አደሮች ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲሰጥ መወሰኑን አስታውሰዋል።
"እንዲሰጥ የተወሰነው ቤት ቁጥር ከተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በታች ነው። እጣ የወጣው ጥቅምት 2012። ገበሬ እጅ የደረሰ ግን አንድም ቤት የለም። የከተማው የቤቶች ልማት ቢሮ ለምን ይዞ እንደሚቀመጥ ግልጽ አይደለም" የሚሉት ደግሞ ወ/ሮ ፈትያ ናቸው።
የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ምላሽ
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው በልማት ምክንያት ለተነሱ አርሶ አደሮች ተገቢው የማጣራት ሥራ እየተከናወነ በከተማ ካቢኔው ውሳኔ መሠረት የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ቢሯቸው እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማው ካቢኔ ተላልፈው እንዲሰጡ ከወሰናቸው ወደ 23 ሺህ ከሚጠጉ መኖሪያ ቤቶች አብዛኛው ቤቶች ለአርሶ አደሮች ተላልፈው መሰጠታቸውን ተናግረዋል።
ሰናይት ዳምጠው "በልማት የተነሱ አርሶ አደሮች መሆናቸው በኮሚሽኑ [የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ኮሚሽን] ሲረጋገጥ ይሰጣቸው ተብሎ የተወሰነላቸው ወደ 23 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ናቸው" ብለዋል።
ጨምረውም "እስካሁንም ከተጠቀሱት መካከል ለአብዛኞቹ ቤቱን ሰጥተናል። የቀሩት ወደ 5 ሺህ የሚጠጉት ብቻ ናቸው። ለተቀሩትም ተጣርቶ ሲመጣ የከተማው ከቢኔ በወሰነው መሠረት የሚቀጥል ነው የሚሆነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቢሮ ኃላፊዋ እንዳሉት ቤቶቹን ለአርሶ አደሮች በማስተላለፍ ሂደት ላይ መዘግየት መኖሩንም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
"ቤቶቹን አስተላልፈን ከመስጠታችን በፊት የማጣራት ሥራ እንዲሰራ ተደርጓል። አርሶ አደሮቹን ፈልጎ ማግኘት፣ ማንነት ማጣራት፣ የሚገባቸው መሆኑን አለመሆኑን የመለየት በርካታ ሥራዎች በኮሚሽኑ በኩል ሲሰሩ ነበር" ሲሉ ቤቶች ከመተላለፋቸው በፊት ማጣራት እንደሚደረግ አመልክተዋል፥
በቢሮው በኩልም "ዕጣ የማውጣት ሥራ፣ የልኬት ሥራ፣ ካርታ የማጣም ሥራዎች ነበሩብን። ለሌላው የከተማ ነዋሪም የሚሰጥ ቤት ነበር ተደራራቢ ሥራ አለ" በማለት ለአርሶ አደሮች ቤቶች በፍጥነት ተላልፈው ያልተሰጡበትን ምክንያት አስረድተዋል።


















