ቻይና፡ አውስትራሊያዊቷ ጋዜጠኛ የቻይናን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ጥላለች ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትራሊያዊቷ ጋዜጠኛ ለሳምንታት በቻይና በቁጥጥር ሥር ውላ እንድትቆይ የተደረገው የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣሏ ነው ተባለ።
የቻይና ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትዎርክ (ሲጂቲኤን) አቅራቢዋ ቼንግ ሊ "የቻይናን ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ መጣል" በሚል ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር እንድትውል መደረጓን ቻይና ይፋ አድርጋለች።
ቻይና ውስጥ በዚህ በመሰል ወንጀል በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው እስከ ስድስት ወራት ድረስ ምርመር ሊደርግለትና ከእሥር ላይወጣ ይችላል።
ቼንግ ሊ ከነሐሴ 8 ጀምሮ በቻይና በቁጥጥር ሥር ውላ ትገኛለች።
በቻይና እና አውስትራሊያ መካከል ያለው ውጥረት እያየለ መጥቷል። በዚህም የአውስትራሊያ መንግሥት ቻይና የሚገኙ ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከዚህ ቀደም ማሳሰቢያ አስተላልፎ ነበር።
የቻይና እና የአውስትራሊያ ግነኙነት እየሻከረ የመጣው አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ መነሾ በይፋ ይጣራ ማለቷን ተከትሎ ነው።
ቻይናም ለዚህ የአውስትራሊያ ተግባር ምላሽ ነው በተባለለት ውሳኔ ቻይና ከአውስትራሊያ ወደ አገሯ በሚገቡ ምርቶች ላይ እገዳዎችን ጥላለች። ከዚህ በተጨማሪም ቻይና ዜጎቿ ለከፍተኛ ትምህርት አውስትራሊያን መዳረሻቸው አድርገው ከመወሰናቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡበት ስታሳስብ ቆይታለች።
ጋዜጠኛዋ ቼንግ ሊ በምትሰራበት የቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ በበርካቶች ዘንድ የተከበረች እና በተመልካቾች ዘንድም የምትወደድ የቢዝነስ ዘጋቢ ነች። በቻይና መንግሥት በቁጥጥር ሥር መዋሏ ይፋ ከመሆኑ በፊት ከቤተሰብ እና ከጓደኞቿ ጋር የነበራትን ግነኙነት በድንገት አቋርጣ ነበር።
ከዚያም የቻይና መንግሥት ጋዜጠኛዋ በቁጥጥር ሥር መዋሏን አስታወቀ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቼንግ ሊ በቁጥጥር ሥር መዋሏ በተገለጸበት ወቅት በየትኛው ወንጀል ተጠርጥራ እንደታሰረች በግልጽ አልተነገረም። ይሁን እንጂ በርካቶች በቤጂንግ እና ካንቤራ መካከል እየሻከረመ የመጣው ግነኙነት አውስትራሊያዊቷን ጋዜጠኛ ለእስር እንድትዳረግ ምክንያት ነው እያሉ ነው።
ከቼንግ በተጨማሪ በቻይና ይሰሩ የነበሩ ሁለት የአውስትራሊያ ዜጋ የሆኑ ጋዜጠኞች ሰኞ ዕለት ቻይናን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።
ቼንግ ለሲጂቲኤን ለስምንት ዓመታት ያገለገለች ሲሆን 'ግሎባል ቢዝነስ' በተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ አቅራቢ ሆና ትሰራለች።
ጋዜጠኛዋ በቻይና መንግሥት ቁጥጥር ሥር ከዋለች ወዲህ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ድረ-ገፅ ላይ ስለእሷና ሥራዎቿ የሚያትተው ገፅ መነሳቱ ተነግሯል።
















