ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መጨመር እንዳሳሰባት ገለፀች

በሚሊኒየም አዳራሽ የሚገኘው የፅኑ ህሙማን ክፍል

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ደቡብ ሱዳን እንዳሳሰባት ገልፃለች።

መጋቢት ወር ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጀምሮ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመጣባት ኢትዮጵያ በባለፉት ሳምንታት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደቡብ ሱዳኗ መዲና ጁባ በየቀኑ ከአዲስ አበባ በረራ የሚያደርግ ሲሆን ይሄም ሁኔታ አስጊ ነው በማለት የጤና ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

"በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር በእርግጥ ሊያሳስበን ይገባል፤ ስለዚህ የመከላከያ መንገዶቻችንንም ልናጠናክር ይገባል" በማለት የጤና ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ዶክተር ቶው ሎይ ሲንጎት በጁባ ለሚገኙ ሪፖርተሮች ተናግረዋል።

ሆኖም ከአዲስ አበባ ወደ ጁባ በየቀኑ የሚደረጉት በረራዎችም እንደሚቀጥሉ የተናገሩት ቃለ አቀባይ ሁሉም አገራት ለዜጎቹ ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት እንደሚደረገው ከፍተኛ ጥንቃቄን ተግባራዊ እናደርጋለን ብለዋል።

"ከአዲስ አበባ የሚደረጉ የየቀኑ በረራዎች የሚቀጥሉ ይሆናል። አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ካልሆነ አይቆምም" ብለዋል ዶክተር ቶው ሎይ

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 59 ሺህ 648 ደርሷል፤ ከነዚህም ውስጥ 21 ሺህ 789 ያገገሙ ሲሆን 933 ህይወታቸው እንዳለፈ በትናንትናው ዕለት የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ መግለጫ አስፍሯል።

ኮሮና