ኮሮናቫይረስ ፡ አውስትራሊያ 85 ሚሊዮን ክትባቶች ለዜጎቿ ልታቀርብ ነው

አውስትራሊያ ባህር ዳርቻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚንስትር አሁን እየበለጸጉ የሚገኙት ሁለቱ ክትባቶች ስኬታማ የሚሆኑ ከሆነ 85 ሚሊዮን ክትባቶችን መንግሥት ለሕዝቡ እንደሚያቀርብ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን አገራቸው የኮሮናቫይረስ ክትባት ለዜጎቿ በነጻ ለማቅረብ ሁለት የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ለመግዛት ስምምነቶችን ፈርማለች ብለዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሆነ አውስትራሊያ ክትባቶቹን ለመግዛት 1.24 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች።

"25 ሚሊዮን አውስትራሊያውያን ከየካቲት 2013 ጀምሮ ክትባቱን ማግኘት ይችላሉ ለዚህ ግን ማረጋገጫ የለም" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት የካቲት ላይ ለዜጎች ክትባቱን በነጻ ማቅረቡ መቶ በመቶ እርግጠኛ ባይሆንም የአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ክትባቶቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይሁንታቸውን የሚሰጡ ከሆነ፤ አውስትራሊያ ክትባቶቹን ቀድማ እንደምታገኝ ጠቁመዋል።

አንደኛው ክትባት በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና በመድኃኒት አምራቹ ኩባንያ አስትራዜኔካ ጥምረት እየበለጸገ የሚገኝ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በአውስትራሊያው ኩዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ እና ሲኤስኤል የሚመረት ነው።

አውስትራሊያ ለመግዛት ውል ከያዘችው መካከል 33.8 ሚሊዮን ክትባት ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን 51 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ በኩዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ የሚመረተውን ነው።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየተዘጋጀ የሚገኘው ክትባት በሦስተኛ ደረጃ ክሊኒካዊ ሙከራ ላይ የደረሰ ሲሆን በ30ሺህ ሰዎች ላይ ክትባቱ ተሞክሯል።

በመላው ዓለም የሚገኙ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባት እንዲደርሳቸው የተለያዩ አይነት ጥረቶችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ሐምሌ ወር ላይ የዓለም ጤና ድርጅት 165 የዓለም አገራት፤ ድሃ አገራት ክትባቱን ለዜጎቻቸው እንዲያደርሱ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን አስታውቆ ነበር።

በዓለም ዙሪያ በአሁኑ ወቅት 140 የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ለማበልጸግ ምርምሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

አውስትራሊያ እስካሁን ድረስ ከ26ሺህ በላይ ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን 769 ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።