ቻይናና አውስትራሊያ፡ ቤይጂንግ የሲድኒን ወይን መመርመሯ አገራቱን እያጣላ ነው

የወይን ጠርሙስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ቻይና ለሁለተኛ ጊዜ ከአውስትራሊያ የሚገቡ ወይኖች ላይ ምርመራ መጀመሯ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ፍጥጫ አክርሮታል።

ቻይና ከሁለት ሳምንት በፊት የአውስትራሊያ ወይኖችን እመረምራለሁ ማለቷን ተከትሎ ሌላ አንድ ዓመት የሚወስድ ምርመራ እንደምትከፍትም አስታውቃለች።

አውስትራሊያ በበኩሏ ቻይና ውስጥ ወይን ስለማራገፏ እንዲሁም እርዳታ ስለመስጠቷ የቀረበባትን ክስ አጣጥላለች።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ተከትሎ፤ ቻይና አውስትራሊያ ላይ የምጣኔ ሀብት ጫና እያሳደረች እንደሆነ ትወነጀላለች።

የኮሮናቫይረስ መነሻን በተመለከተ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ምርመራ አውስትራሊያ ቻይና ላይ ጣት መጠቆሟ፤ የቻይናን ሕዝብ ስሜት እንደጎዳ አንድ ከፍተኛ የቻይና ዲፕሎማት ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

ባለፉት ወራት ቻይና የአውስትራሊያ ገብስ፣ ስጋና ወይን ላይ ያነጣጠሩ እርምጃዎች ወስዳለች። ተማሪዎችና ጎብኚዎች ዘረኛነት እንዳይገጥማቸው ወደ አውስትራሊያ እንዳይሄዱ እየተነገራቸውም ነው።

ባለፈው ሳምንት፤ የአውስትራሊያ መንግሥት ከሌሎች አገራት መንግሥታት ጋር የሚገባውን ውል መሰረዝ የሚያስችል ሕግ ሊተገብር መሆኑ ተሰምቷል። ይህም ቻይናን ኢላማ ያደረገ ነው ተብሏል።

የአውስትራሊያ ትልቅ ገበያ ያለው ቻይና ነው። ይህም ከአገር አቀፍ የውጪ ምርቱ 32.6 በመቶ ነው።

ቻይና የአውስትራሊያ ገብስ ላይ 80 በመቶ ቀረጥ የጣለችው ለአንድ ዓመት ከዘለቀ ምርመራ በኋላ ነው።

በዓለም ንግድ ድርጅት መርህ መሠረት መሰል ምርመራዎች በአውስትራሊያ ወይን ምርቶች ላይ እየተካሄደ እንደነበር ቻይና አስታውቃለች።

አዲሱ “ጸረ ድጎማ” የተባለው ምርምራ ተግባራዊ የሚሆነው ሁለት ሊትርና ከዛ በታች በያዙ ጠርሙሶች ላይ ነው።

የአውስትራሊያው የንግድ ሚንስትር ክሱን አጣጥለዋል። የአገሪቱ የወይን ተክል እና ወይን አምራቾች ወኪል፤ ምርታቸው በቻይና ተፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ወደ ቻይና ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ብረትና ጋዝ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ዘርፎች በወቅታዊው ችኩቻ ተጽዕኖ ስር አልወደቁም።

አውስትራሊያ ወደ ቻይና ከምትልከው ወይንና የባህር እንስሳት ምግብ በተጨማሪ ትምህርትና ቱሪዝምም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ናቸው።