ቻይና የሕንድ ወታደሮች "ተኩሰውብኛል" ስትል ከሰሰች

በሕንድና በቻይና ድንበር አቅራብያ የሕንድ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና የሕንድ ወታደሮች በህገወጥ መልኩ ድንበሯን አቋርጠው በጥበቃ ላይ የነበሩ ወታደሮች ላይ "ጠብ አጫሪ" የማስጠንቀቂያ ተኩስ መተኮሳቸውን በመግለጽ ከሰሰች።

የቻይና ወታደሮች "አፀፋውን ለመመለስ" ተገድደው ነበር ያሉት የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ በትክክል ስለወሰዱት እርምጃ አልገለፁም።

ሕንድና ቻይና በአጨቃጫቂው ድንበር አቅራብያ መሳሪያ ላለመተኮስ የገቡትን ስምምነት በጣሰ መልኩ መሳሪያ ሲተኮስ ከ45 ዓመት ወዲህ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት እያሽቆለቆለ መጥቷል።

የቻይና መገናኛ ብዙኀን እንደዘገበው ከሆነ፣ " የሕንድ ወታደሮች በሺንፓኦ ተራራ አካባቢ በሕገወጥ መልኩ ድንበር አቋርጠዋል" ሲል የዜጎች ነፃነት ጦር ቃል አቀባይ የሆኑትን ኮሎኔል ዛንግ ሹኢሊን በመጥቀስ ዘግቧል።

የሕንድን እርምጃ " ሁለቱ አገራት የገቡትን ስምምነት ፍፁም የሚጥስ፣ ውጥረትን የሚያነግስ. . . እና በባህሪው ጠብ አጫሪ የሆነ" ብለውታል ቃል አቀባዩ።

የሕንድ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ምንም ኣይነት ምላሽ አልሰጡም።

እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር በ1996 ሁለቱ አገራት፣ ምንም እንኳ ወታደሮቻቸው ተጋጭተው የሚያውቁ ቢሆንም፣ የጦር መሳሪያ በድንበር አካባቢ ላለመጠቀም ተስማምተው ነበር።

የሕንድ ወታደሮች መሳሪያ መተኮሳቸው የተሰማው በፓንጎንግ ሀይቅ አቅራብያ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ በሕንድ ወገን " በአስቸኳይ አደገኛ የሆነ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቆሙ፣ ድንበርን ተሻግረው መሳሪያ የተኮሱትን ወታደሮች ከስፍራው እንዲያስወጡ. . . እና ጠብ አጫሪ የሆነ ተኩስ የከፈቱት ላይ ተገቢው ቅጣት እንዲጣልባቸው" ሲሉ ጠይቀዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት መታየት የጀመረው፣ ሕንድ የቻይና ባለስልጣናትን በአጨቃጫቂው ድንበር አካባቢ አምስት ንፁኃን ዜጎች በወታደሮቻቸው ታግተው መወሰዳቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው።

በሰኔ ወር 20 የሕንድ ወታደሮች ከቻይና ወታደሮች ጋር ተጋጭተው ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ በአካባቢው ውጥረት ተባብሷል። የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ወታደሮቹ "ክፉኛ ተደብድበዋል።"

በነሐሴ ወር ሕንድ ቻይናን በድንበር አካባቢ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወታደራዊ ውጥረት እንዲፈጠር እያደረገች ነው ስትል ከስሳ ነበር። ሁለቱንም ክሶች ቻይና ያጣጣለች ሲሆን በድንበር አካባቢ የተፈጠረው ችግር ሙሉ በሙሉ የሕንድ ጥፋት ነው ብላለች።

በቻይናና በሕንድ መካከል ያለው አጨቃጫቂ ድንበር በአግባቡ የተሰመረ እንዳልሆነ ይጠቀሳል። በአካባቢው ወንዞች፣ ሐይቆችና በረዶ መኖሩ ድንበሩ መስመር እንዲተጣጠፍ ያደርጋል።

በሁለቱም ወገን የሚገኙ ወታደሮች፣ በዓለም ላይ የሚገኙ ሁለት ትልልቅ የጦር ኃይሎችን የሚወክሉ ሲሆን፣ በርካታ ጊዜያት ተፋጥጠው ያውቃሉ።

ሕንድ ቻይናን በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ድንበር በማስጠጋት ደጋግማ ከስሳለች። በሁለቱ መንግሥታት መካከል ላለፉት ሶስት አስርታት ንግግር ቢደረግም የድንበር ይገባኛል ጥያቄውን መፍታት አልተቻለም።

ሁለቱ አገራት በ1962 አንዴ ብቻ ውጊያ ያደረጉ ሲሆን ሕንድ ሽንፈትን ተጎናጽፋለች።