እስክንድር ነጋ ፡ አቶ እስክንድር ጉዳያቸው በግልጽ ችሎት የማይታይ ከሆነ ችሎት መቅረብ እንደማይፈልጉ ገለጹ

እስክንድር ነጋ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ ጉዳያቸው በግልጽ ችሎት የማይታይ ከሆነ በዚህ ሂደት ውስጥ መሳተፍ እንደማይፈልጉና ጠበቃቸውንም ማሰናበታቸውን ለፍርድ ቤት ገለጹ።

አቶ እስክንድር ነጋ ለፍርድ ቤት ይህን ያሉት እራሳቸውና አብረዋቸው የተከሰሱ ሰዎች ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ በጠየቀው መሰራት ለምስክሮች ደኅንነት ሲባል ከመጋረጃ ጀርባ በዝግ ችሎት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ውሳኔ መሰጠቱን ተከትሎ ነው።

ረቡዕ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ጉዳያቸው የታየው የአቶ አስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ቀለብ ስዩም መሆኑን ለቢቢሲ የገለጹት ጠበቃቸው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ችሎቱ ዐቃቤ ህ ቀደም ቀደም ሲል ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ተመልክቷል።

ጠበቃው እንዳሉት ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የምስክሮች ዝርዝር ለተጠርጣሪዎቹ መድረስ የለበትም እንዲሁም ደግሞ ምስክርነት መስጠትን በተመለከተ ከቀረቡት ሰባት ምስክሮች ውስጥ ሦስቱ ማንነታቸው ሳይገለጽና ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ የተቀሩት አራት ምስክሮች ደግሞ ችሎቱ ዝግ ሆኖ ምስክርነታቸው እንዲሰማ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ይህንን ጉዳይ ከደንበኞቻቸው ጋር ተማክረው የጽሁፍ መልስ ይዘው እንደቀረቡ የሚናገሩት ጠበቃ ሄኖክ፤ በዚህም መሰረት ይህ ሂደት የተከሳሾችን መብት በእጅጉ እንደሚነካና የተከሳሾችን የመከላከል መብት እንደሚጎዳ እንዲሁም ቀሪ ምስክሮችም ቢሆኑ በዝግ ሳይሆን በግልጽ ችሎት ምስክርነታቸውን ሊሰጡ ይገባል ማለታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ስለዚህ በተጀመረው ሂደት መቀጠል አለበት፤ በቀረቡት ማስረጃዎች ላይ በአደባባይ እንሟገት፣ እንከራከር የሚል ነበር በአጭሩ የሰጠነው መልስ" ብለዋል ጠበቃው።

ለዚህም ዐቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ የምስክሮች ጥበቃ አዋጅን ጠቅሶ ከሚደረጉ ጥበቃዎች ውስጥ ለምስክሮች ደኅንንት ሲባል ማንነታቸው ሳይገለጽና ሳይታዩ እንዲሁም በዝግ ችሎት እንዲመሰከሩ እንደሚደረግ ገልጿል።

ጨምሮም የምስክሮችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በአዋጁ መሰረት የሚደረገው በዝግ ችሎትና ማንነታቸው ሳይገለጽ ምስክርነት መስጠታቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ጉዳት የሌለው መሆኑን አመልክቶ የተጠርጣሪዎች አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም ይህንን ከሰማ በኋላ በተከሳሾችና በጠበቆች የቀረበውን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ በመቀበል ምስክሮቹን የመስማት ሂደቱ እንዲቀጥል ብይን መስጠቱን አቶ ሄኖክ ተናግረዋል።

በዚህ ጊዜም አቶ እስክንድ ነጋ ለፍርድ ቤቱ የሚገልጹት ሀሳብ እንዳላቸው በመጠየቅ፤ የተጠረጠሩበት ጉዳይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ባህሪ ያለው መሆኑን በመጥቀስ፤ እንዲህ አይነት መሰል ጉዳዮች ደግሞ በዝግ ችሎት መካሄድ የለባቸውም፤ ዓለም አቀፍ ተሞክሮውም በግልጽ እንደሚካሄድ ነው የሚያሳየው ብለዋል።

"ስለዚህ አቃቤ ሕግ ሂደቱ በዝግ እንዲካሄድና ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ እንዲመሰክሩ መደረጉ እኛ ፍትህ እንዳናገኝ ያደርገናል፣ የፍርድ ሂደቱን ይጎዳብናል፣ በእንደዚህ አይነት ፍትህ በማናገኝበት ሁኔታ የክርክሩ ሂደት አካል መሆን ስለማንፈልግ እራሳችንን ከጉዳዩ አግልለናል" ማለታቸውን ጠበቃው ተናግረዋል።

ጨምረውም ከዚህ በኋላም በዚህ ሂደት እንደማይሳተፉና ፍርድ ቤት መምጣት እንደማይፈልጉ ጠቅሰው፤ ፍርድ ቤት ወክለዋቸው ሲቀርቡ የነበሩ ጠበቃዎችንም ማሰናበታቸውን ለችሎቱ ተናግረዋል። ሌሎቹም ተከሳሾች ተመሳሳይ ሃሳብ እንዳላቸው መግለጻቸውን ጠበቃ ሄኖክ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በጉዳዩ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያለውን አስተያየት በፍርድ ቤቱ ተጠይቆ፤ ፖሊስ ተከሳሾችን በቀጠሮ አስገድዶ እንዲያቀርብላቸው ለችሎቱ አመልክቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግን አቤቱታ ከሰማ በኋላ ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ምስክሮቹን እንዲያቀርብና እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹን አስገድዶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፤ ለእነአቶ እስክንድርም መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ይህንን ካደረገ በኋላ አቶ እስክንድር ነጋ ይሄ ትክክል አይደለም በሚል ''እኛ ማንም ጠበቃ እንዲያቆምልን አንፈልግም፤ መከራከር አንፈልግም፤ መንግሥት ጠበቆች እንዲያቆምልን ፈቃደኞች አይደለንም። እኛ የእንደዚህ አይነት የፍርድ ሂደት አካል መሆን አንፈልግም፤ ከዚህ በኋላ ወደ ችሎቱ መምጣትም አንፈልግም''' በማለት መናገራቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ መሰረት የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለነሐሴ 8/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።