አሜሪካ 3.5 ሚሊዮን ዶላር የሚገመተውን የቀድሞ የጋምቢያ መሪ ቤት ልትወርስ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ 3.5 ሚሊዮን ዶላር የሚተመነውን ቅንጡ የቀድሞ የጋምቢያ መሪ ያህያ ጃሜህ መኖሪያ ቤትን ልትወርስ መሆኑ ተነገረ።
ያህያ ጃሜህ ስልጣን ላይ ሳሉ ነበር በአሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ በአንድ የመኖሪያ መንደር ውስጥ ቅንጡ መኖሪያ ቤቱን የገዙት።
የአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዝደንት መኖሪያ ቤቱን የገዙት በሙስና በተገኘ ገንዘብ እና በሕዝብ ሃብት ነው ብሏል።
ያህያ ጃሜህ መኖሪያ ቤቱን የገዙት ከ10 ዓመታት በፊት በባለቤታቸው ስም በተመዘገበ ድርጅት አማካኝነት መሆኑም ተነግሯል።
ለ20 ዓመታት ጋምቢያን ያመሩት ያህያ ጃሜህ እአአ 2017 ላይ በተካሄደው ምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ አገር ጥለው ተሰደዋል።
ያህያ ጃሜህ በአሁኑ ወቅት በስደት በኢኳቶሪያ ጊኒ እየኖሩ ይገኛሉ።
ያህያ ጃሜህ ማን ናቸው?
እአአ 1965 ላይ የተወለዱት ጃሜህ ወደ ስልጣን የመጡት እአአ 1994 ላይ የ29 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር።
ጃሜህ በስልጣን ዘመናቸው በርካቶችን ያነጋግር የነበረ ተፈጥሯዊ ኃይል እንዳላቸው በተደጋጋሚ ይናገራሉ ነበር። ሰዎችን ከኤች አይቪ ኤድስ የመፈወስ አቅም አለኝ ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።
ጃሜህ እአአ 2017 ላይ በምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ አገር ጥለው ከመሰደዳቸው በፊት አራት አወዛገቢ የነበሩት አገራዊ ምርጫዎችን ማሸነፋቸው ይታወሳል።
እአአ 2011 ላይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ የሊቢያ መሪው ሞአመር ጋዳፊ እጣ ይደርሰኛል ብለው እንደማይሰጉ ተናግረው፤ "አላህ ካለ የጋምቢያን ሕዝብ አንድ ቢሊዮን ዓመት ልመራ እችላለሁ" ብለዋው ነበር።
ጃሜህ የመጀመሪያ ሚስታቸውን ፈተው በተመሳሳይ ጊዜ ሌሎች ሁለት ሴቶችን አግብተው ነበር። በጃሜህ የሰልጣን ዘመን ቀዳማዊ እመቤት የሚለውን መጠሪያ ያገኘችው ግን ዘይነብ ያህያ ጃሜህ የምትባለዋ ባለቤታቸው ብቻ ነበረች።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጃሜህ እአአ 2013 ላይ በተከበረው የኢድ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ንግግር የሞት ፍርድ ተፍርዶባቸው በእስር ቤት ውስጥ ያሉ እስረኞች በሙሉ የሞት ቅጣቱ በአስቸኳይ ተፈጸሚ እንዲሆንባቸው አዘው ነበር።
በዚህም ፖለቲከኞችን እና የቀድሞ የአገሪ ጦር አመራር አባላት ጨምሮ 9 ሰዎች የሞት ብይኑ ተፈጻሚ ሆኖባቸዋል።
ጃሜህ ከስልጣን ወርደው ወደ ጎረቤት አገር ከሸሹ በኋላ በርካቶች ጾታዊ ጥቆች ፈጽመውብናል ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።












