የተባበሩት መንግሥታት ወረርሽኙን ለመዋጋት ከፍተኛ የተባለውን 10.3 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት 10.3 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ ጠየቀ።
አሃዙ እስካሁን ከነበረው ከፍተኛ ገንዘብ የተጠየቀበት የገቢ ማሰባሰቢያ ጥሪ ነው ተብሏል።
ድርጅቱ እንዳለው ወረርሽኙ ባስከተለው ተፅዕኖ ሳቢያ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 265 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ለርሃብ ሊጋለጡ ይችላሉ።
በመሆኑም የሚሰበሰበው ገንዘብ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና በዚህ የተጎዱ አገራትን ለመደገፍ ይውላል ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት እርምጃ ካልተወሰደ የአስርተ ዓማታትን እድገት ወደኋላ እንደሚመልስ ያስጠነቀቀ ሲሆን ወረርሽኙ መስፋፋት በጀመረበት መጋቢት ወር ላይ 2 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ ጠይቋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም በአለማችን ድሃ አገራት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያደረሰ ይገኛል።
ይህ የተሻሻለው የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄም ከፍተኛ ቢሆንም፤ ሃብታም አገራት የፋይናንስ ሕጋቸውን ወደ ኋላ አድርገው ለደሃ አገራት ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብሏል ድርጅቱ።
ይህን ካለደረጉ ግን ሚሊየኖች ለርሃብ እንደሚጋለጡና ዓለም ከፍተኛ የሆነ ቀውስ እንደሚገጥማት ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
ድርጅቱ፤ "በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኛ ሰራተኞች በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ሥራ እየሰሩ ባለመሆናቸው ወደ አገራቸው ገንዘብ መላክ አይችሉም።
ለህፃናት የሚሰጡ የክትባት ፕሮግራሞችም ቆመዋል። ለዓመታት በግጭት ውስጥ ያሉ አገራትም ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም የላቸውም" ሲል ያሉትን ተግዳሮቶች አስረድቷል።
በየመን በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች አንድ አራተኛ የሚሆኑት በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም በዓለም ላይ ካለው አማካይ የሞት ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በአምስት እጥፍ ይልቃል።
በመሆኑም በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቁ አገራትን ለመርዳት ገንዘብ ለማሰባሰብ በዩናይትድ ኪንግደም የድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ኮሚቴ ተጀመሯል።
ኦክስፋም፣ ክርስቲያን ኤድ፣ እስላሚክ ሪሊፍ እና ብሪቲሽ ሬድ ክሮስን ጨምሮ አስራ አራት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የእንግሊዝ ሕዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ ለመጠየቅ እንቅስቃሴውን ይቀላቀላሉ ተብሏል።
በአለም አቀፍ ደረጃ እስከሁን ከ13 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 600 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።












