በሩቁ ህዋ ላይ እና በጥልቁ ውቅያኖስ ውስጥ ታሪክ የሰራችው ሴት

የፎቶው ባለመብት, Enrique Alvarez
ዶክተር ኬቲ ሱሊቫን ሰማይ ቧጠጠች፣ ምድርን አበሰች ማለቱ ይቀላል። በሰማይና በምድር ሩቅ የሚባሉትን ጫፎች ደርሳ በመመለስ ታሪክ ሰርታለች፡፡ ይህን እንዴት ማሳካት ቻለች?

ልጅነት
ዝነኛ መሆን ለኬቲ ሱሊቫን በጭራሽ ውልብ የሚል ሐሳብ አልነበረም።
ሕጻን ሳለች ግን ዝም ብሎ ይገርማታል። የመሬት ነገር፣ የሰማይ ነገር፣ የባሕር ነገር፣ የእእዋፋት ነገር።
ላይ ያለው ምንድነው፤ ከውቅያኖስ ሥር የሚኖረውስ ማነው?
እነዚህ ልጅነቷን የተቆጣጠሩት ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መጡ።
አሁን ሰዎች የመጀመሪያዋ ህዋ ላይ የተራመደች አሜሪካዊት ሴት ብለው ይጠሯታል።
ይህ ብዙም ስሜት የሚሰጣት ሴት አይደለችም። የሴቶች በሁሉም ዘርፍ ውክልና ማጣት ቢያሳስባትም ሁኔታዎች ለሴቶች እስኪመቻቹ መጠበቅ ላይ ግን ተቃውሞ አላት።
ኬቲ ድሮ ልጅ ሳለች ወደ ህዋ በሚደረግ ጉዞ የምታያቸው ሁሉ ወንዶች መሆናቸው ያን ያህልም አይረብሻትም ነበር።
"ዞሮ ዞሮ ወንድም ሆነ ሴት ህዋ ላይ ሰው መውጣቱ እንጂ ነገሩን በጾታ ዓይን ተመልክቼው አላውቅም ነበር" ትላለች።
ህዋ ላይ የተራመደችው በፈረንጆቹ በ1984 ነበር። ያን ጊዜ በአሜሪካ ትልቅ ዜና ሆና ነበር። ያን ጊዜ ወጣት ነበረች።
አሁን ኬቲ 68 ዓመቷ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Kathy Sullivan
በድጋሚ የዓለም መነጋገሪያ ሆናለች። ወደ ላይ ወደ ህዋ እንደወጣችው አሁን ደግሞ ወደ ውቅያኖስ ጥልቅ ገብታ ነው ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም አነጋጋሪዋ ሴት የሆነችው።
ይህን ያሳካችው ደግሞ በውቅያኖስ ውስጥ 11 ኪሎ ሜትር ጠልቃ በመግባቷ ነው።
ኬቲ ዕድለኛ ሳትሆን አትቀርም። ወደታችም ወደ ላይም ክብረ ወሰኑን ይዛዋለች።
የምድርን ምስጢር ለመረዳት እንደርሷ የቀረበ ይኖር ይሆን?
ከሰሞኑ ዳግም ወደ ዝና ከተመለሰች ወዲህ ከቢቢሲ ጋር በስልክ ቆይታ አድርጋ ነበር። "በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፤ የልጅነት ህልሜ በዚህ መልኩ መሳካቱ ይገርማል" ብላለች።
ኬቲ በኒውጀርሲ በእነርሱ አቆጣጠር በ1951 ነበር የተወለደችው። ልጅነቷን ያሳለፈችው በካሊፎርኒያ ነው። አባቷ የኤሮስፔስ መሐንዲስ ነበሩ።
"አባትና እናቴ ሕጻን እያለን ጀምሮ በነጻነት ሐሳባችንን እንድንገልጽ፤ ማሰብ የምንችለውን ያህል በነጻነት እንድናልም ያበረታቱን ነበር" ትላለች።
እሷና ወንድሟ አምስት እና ስድስት ዓመት ሲሆናቸው፣ ወንድሟ አውሮፕላን አብራሪ እንደሚሆን እርግጠኛ ሆነ።
ኬቲ ግን ስለምትሆነው ነገር እርግጠኛ አልነበረችም።
እንዲሁ ግን ብዙዋን የልጅነቷን ዘመን የሚማርኩት የህዋና የመሬት ካርታ እንዲሁም ፎቶግራፎችን ማየት ነበር።
"ሥራዬ ካርታ ላይ ማፍጠጥና እዚህና እዚያ ምን ይሆን ያለው እያልኩ መገረም ነበር" ትላለች።
እሷም ወንድሟ ያለሙትን ሆነዋል ዛሬ።

የፎቶው ባለመብት, NASA
ህዋ ላይ ሆኜ መሬትን ስመለከት ያን ያህልም አልተገረምኩም ነበር፤ ምክንያቱም በፎቶዎችና ካርታዎች ስመለከት ነው የኖርኩት ትላለች ኬቲ። ልዩነቱን አሁን ራሷ በዓይኗ በብረቱ ምድርን ቁልቁል ኳስ አክላ ማየት ነው።
"ድሮ ድሮ የሆኑ ሰዎች ጭራሽ የሰው ልጅ ከዚያ በፊት ሄዶባቸው ወደማያውቅበት ሥፍራ ደርሰው ሲመጡ የሚናገሯቸውን ነገሮች ለመስማት መጽሔትና ጋዜጣ አይቀረኝም ነበር" ትላለች ኬቲ።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለች የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የመሆን ሕልም አልነበራትም። ይህ ነው የምትለውን ቁርጥ ያለ የሥራ ዘርፍ ኖሯት አያውቅም።
"እኔ የነበረኝ ፍላጎት እንዲሁ ምድርንና ከባቢዋን መበርበር፣ ማወቅ፣ መገረም፣ መጠየቅ፣ መፈተሽ ብቻ ነበር።"
ኬቲ መጀመሪያ የውጪ ቋንቋዎችን አጠናች። ከዚያ የመጀመሪያ ዲግሪዋ በመሬት ሳይንስ ጥናት ሆነ። ይህ ዘርፍ በ1970ዎቹ በሴቶች የሚመረጥ ዘርፍ በጭራሽ አልነበረም።
"እነዚህ የክፍል ጓደኞቼ ወደ መስክ ስምሪት ወጥተው ያደፉ ልብሶችን ለብሰው ገላቸውን እንኳ መታጠብ ሳያሳስባቸው ወደ ሥራ ይመለሳሉ፤ የእኔ ብቸኛ ሴት ሆኖ ከእነርሱ ጋር መሆን ምቾታቸውን ሳይነሳቸው አልቀረም።"
የሚደንቀው ግን ኬቲን በዚህ ወቅት ከወንዶች ምንም አይነት ጥቃት አይደርሰባትም ነበር። "እንዲያውም በሚደንቅ ሁኔታ የሚያበረታቱኝ ወንድ ፕሮፌሰሮችና የክፍል ጓደኞቼ ነበሩ" ትላለች።
የባሕር ውስጥ ምርምር ጥናት ክፍለ ጊዜ ፕሮፌሰሮቿ ኬቲ ኦሺኖሎጂን እንድታጠና ገፋፏት።
ከዚህ በኋላ ናሳ ለመግባት አመለከተች።
"ናሳ ለመግባት ሳመለክት ዋናው ጉጉቴ የነበረው ድሮ በፎቶ እመለከታቸው የነበሩ ለምሳሌ በለስ ቀንቶኝ ብመረጥ ከህዋ ምሕዋር ወደ ታች መሬትን በዓይኔ በብረቱ መመልከት ዕድል እንዲገጥመኝ ብቻ ነበር።"
ካትሪና በ1978 ዓ.ም ናሳ ተቀበላት። በዚያን ጊዜ እሷ ወደ ሥነ ፈለክ ስትገባ ናሳ ሴቶችን ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ የሚያበረታታበት ጊዜ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, NASA
ከ35 የአንድ ክፍል ተማሪዎች ስድስቱ ተመረጡ። ሳሊ ራይድ በ1983 ወደ ህዋ ለመሄድ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነች።
ሳሊ ራይድ ያ ጊዜ እንዴት ሴቶችን በህዋ መርሃ ግብር ውስጥ ማሳተፍ ፈተና እንደነበር ታስታውሳለች።
"መሐንዲሶች ለእኛ የሚሆን መኳኳያ ማበጃጀት ጀመሩ። ሺህ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ያስፈልገን ይመስል ብዙ አሰናዱልን።"
የኬቲ የመጀመሪያ ጉዞ STS-41-G ትባል ነበር። በኅዳር 1984 ነበር የተደረገው፡፡ ለናሳ 13ኛው የህዋ ጉዞ ነበር።
በኅዳር 11 ኬቲ ታሪክ ሠራች። በመንኩራኩር ተሳፍራ ህዋ ላይ ለመራመድ የመጀመርያዋ አሜሪካዊት ሴት ሆነች።
እርሷና ወንድ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በህዋ ላይ የተራመዱት ለሦስት ሰዓት ተኩል ጊዜ ብቻ ነበር።
ሴቶች በዘርፉ በብዛት አለመኖራቸው እምብዛም አስገራሚ ያለመሆኑን የምታወሳው ካትሪን "አንዳንድ ጊዜ ሴቶች በሩ ገርበብ ሲልባቸው ታግለው ማስከፈት ይኖርባቸዋል" ትላለች ኬቲ።
ባለፈው ዓመት ሁሉም ሴቶች ብቻ የተሳፈሩበት ጉዞ ተደርገዋል።
ኬቲ ከዚህ በኋላ በከፍተኛ ኃላፊነቶች በተለያዩ ዲፓርትመንቶች ከሰራች በኋላ በ1993 ናሳን ለቀቀች።
ከዚህ በኋላ በብሔራዊ የውቅያኖስና አትሞስፌሪክ አስተዳደር ውስጥ መሪ ሳይንቲስት ለመሆን ወደዚያው አመራች፤ ትንሽ ቆይታም በኦባማ ጊዜ የዚህ ክፍል ዋና ዳይሬክተር ሆና ተሾመች።

የፎቶው ባለመብት, Enrique Alvarez
ወደ ጥልቁ ባሕር መጥለቅ
ከዕለታት አንድ ቀን አስደናቂ ግብዣ ቀረበላት። ግብዣው ከቪክቶር ቪስኮቮ ነበር። ቪስኮቭ የቀድመው የባሕር ኃይል መኮንን ሲሆን በኋላ ላይ ዕውቅ ኢንቨስተር የሆነ ሰው ነው። ለውቅያኖስ ውስጥ ጥናት እና የባሕር ጉብኝት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈስ ሰው ነው።
ዘቻሌንጀር ዲፕ የምድራችን እጅግ ጥልቁ የባሕር ወለል ጥግ ነው። በፓስፊክ ውቅያኖስ 200 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምዕራብ ጉዋም የሚገኝ ሥፍራ ነው ይህ ቦታ።
ይህ ስፍራ ታዲያ በምድር ካሉ ቦታዎች ሁሉ ምናልባት ከባሕር በጥልቀት የሚገኝ ቦታ ስለመሆኑ የተደረሰበት በ1960 ሲሆን ዶን ዋልሽና ስዊዛዊው ጀኪውስ ፒካርድ ናቸው መጀመርያ ወደዚህ ጥልቀት ገብተው የወጡት።
ከዚያ በኋላ ወደዚያ የውቅያኖስ ጥልቀት ውስጥ የተገባው በጣም በጥቂት ሰዎች ነው።
አንዱ ዕድለኛ የታይታኒክ ፊልም ዳይሬክተር ጀምስ ካሜሮን ነበር።
ቬስኮቮ ለባሕር ውስጥ ጥናት ልዩ ፍላጎት ያደረበት ባለሀብት ሲሆን በዚህ ረገድ ብዙ እገዛ የሚያደርግ ሰው ነው። ባለፈው ዓመት በሁሉም ምድር ላይ ባሉ ውቅያኖሶች እጅግ ጥልቆቹን ስፍራዎች ለመጎብኘት የመጀመርያው ሰው ሆኗል።
ይህን ያሳካው የራሱ ንብረት የሆኑትን ዲፕሲ ቬሂኪል የተባሉ የውቅያኖስ መንኩራኩሮችን በመጠቀም ነው።
ይህ ሰው ታዲያ አንድ ቀን ብድግ ብሎ ኬቲን ኢሜይል ጻፈላት። ለምን ጥልቁ ውቅያኖስ ደርሰን አንሄድም የሚል። ይህን ያደረገው ሴቶች በዚያ ጥልቅ ገብተው ስለማያውቁ እርሷን የዚህ ታሪክ አካል እንድትሆን ከመሻት ነበር።
ተስማማች።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ 11 ሺህ ሜትር ጥልቁን ውቅያኖስ አብረው ገብተው ወጡ። ይህን ማሳካት የቻሉት የዓለም ሰዎች ስምንት ብቻ ናቸው። እርሷ የመጀመሪያዋ ሴት ሆና ተመዝግባለች።
"ተአምራዊ ነበር ትላለች" ስለዚህ ጉዞ ለቢቢሲ ስትናገር።
በጉዟቸው ሦስት ነገር አሳክተዋል። አንዱ የጥልቁን ውቅያኖስ ጫፍ በትክክል ከባሕር ጠለል በላይ ያለውን ርቀት መለካት ነበር።
ከውቅያኖስ ሥር ሆኖ ርቀት መለካት በጣም ፈታኝ ተግባር ነው። ሁለተኛው በዚያ ጥልቀት የሚገኙ የእጽዋትም ይሁን ሌሎች ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ናሙና መውሰድ ሲሆን፤ ሦስተኛው በዚያ ጥልቀት የሚገኝን የአለት ናሙና ማምጣት ነበር።
በዚህ ሁሉ ተግባር መካከል እነ ኬቲ 31 ሺህ ጫማ ከባሕር ጠለል በታች ቁጭ ብለው ምሳቸውን ቅርጥፍ አድርገው በምድራችን ጥልቅ ሆነው በልተዋል።
ይህን ጉዞ ያሳካው ኢዮስ የተባለ ኩባንያ እነርሱ ከጥልቁ ሲወጡ ከዓለም አቀፉ ህዋ ጣቢያ ጋር በስልክ አገናኘቸው። ነገሩ በህዋ ላይና በምድር ጥልቅ ስፍራ ያሉ ሰዎችን ማገናኘት ነበር። ተሳክቷል።
ሚስተተር ቫስኮቮስ ልክ እንደ ስፔስ ኤክስ ያለ የግል ኩባንያ ነው ያቋቋመው።
ስፔስኤክስም ቫስከኮቮስ ኢንተርፕራይዝም ሁለቱም የግል ኩባንያዎች ናቸው። ልዩነታቸው አንዱ ምድር ውስጥ ሌላው ከሰማይ ላይ መሆናቸው ነው።
ቫስኮቮስ ኢንተርፕራይዝ በባህር ውስጥ ምርምርና ጉዞ ላይ ተጠምዷል። የቴስላ ፈጣሪ ኤሎን መስክ ያቋቋመው ሰፔስ ኤክስ ደግሞ ወደ ህዋ የሚያመላልስ ታክሲ ሰርቶ በቅርቡ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። የናሳ ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ህዋ ከሄደ ገና አንድ ወር እንኳ አልሞላውም።
ኬቲ ከእዚህ ጥልቅ ከወጣች በኋላ "የእውቀት አድማሳችንን ሁልጊዜም መለጠጥ ይኖርብናል" ብላለች።
ኬቲ ሰማይን ቧጠጠች፣ ውቅያኖስን በእግሯ ረገጠች። ከዚህ በኋላ ደግሞ ምን ቀረሽ? ተብላ ተጠየቀች፤ በቢቢሲ።
"ዓለም በፓስፊክ ውቅያኖስ ጥልቀትና በምድር ሕዋ ምሕዋር የታጠረች አይደለችም። የዕውቀት አድማሳችን መለጠጥ አለበት የምለውም ለዚሁ ነው. . . " ካለች በኋላ፤ በቀሪው ጊዜዋ ምን እንደምትሰራ ተናግራለች።
"እዚያች ጠባብ ሬሳ ሳጥን ውስጥ እስክታስገቡኝ ድረስ የዓለምን ምስጢር መፈተሼ መች ይቀራል?" በማለት።














