ለናሳ ለመስራት የበቃችው የመጀመሪያዋ ኒጀራዊት

ፋድጂ ማኢና ለአሜሪካ የጠፈር ምርመር ተቋም በመስራት የመጀመሪያዋ ኒጀራዊት ሆናለች።
የ29 ዓመቷ ኃይድሮሎጂስት የዶክትሬት ድግሪዋን ያገኘችው ከአራት ዓመታት በፊት እአአ 2016 ላይ ነበር። ከአንድ ወር በፊት ደግሞ ናሳን መቀላቀል ችላለች።
ፋድጂ በአዲሱ ስራዋ አገሯን ኒጀርን እና አፍሪካን ለመካስ እንደምትሰራ ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ማለት የምፈልገው ነገር፤ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። ሁሉም ሰው ከኒጀር የሆነች ወጣት ሴት እዚህ ደረጃ ትደርሳለች ብሎ አይገምትም። ነገር ግን በእራሳችን እምነት ሊኖረን ይገባል" በማለት ተናግራለች።
ፋድጂ ማኢና እንደምትለው ከሆነ በአሁኑ ወቅት በናሳ ውስጥ ብቸኛዋ አፍሪካዊ እርሷ ብቻ ናት።
ኃይድሮሎጂስቷ ፋድጂ በናሳ የከርሰ ምድር ውሃ መጠንን ከየአየር ንብረት ለውጥ መረጃ ጋር በሂሳባዊ ሞዴል ስሌት በማመሳከር የአየር ንብረት ሁኔታን ለመተንበይ የበኩሏን ትወጣለች።
የአየር ንብረት ለውጥ በየትኛው የዓለማችን ክፍል አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ የምትገልጸው ፋድጂ፤ የወደፊት የአየር ንብረት ለውጥን ቀድሞ መተንበይ በአየር ንብረት ለውጥ ሊመጣ የሚችልን ጉዳት ለመቀነስ እንደሚረዳ ታስረዳለች።








