የዓለም ንግድ ድርጅት የመጀመሪያውን አፍሪካዊ መሪ ይሾም ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) በቅርቡ አዲስ የድርጅቱን መሪ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።
የድርጅቱ ዳይሬክተር ጄነራል ለመሆን በእጩነት ከቀረቡት መካከል በርካታ አፍሪካውያን እንደሚገኙበት ተነግሯል።
የድርጅቱ መሪ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት አፍሪካውያን መካከል መቀመጫቸውን ጄኔቫ ያደረጉት በተባበሩት መንግሥታት የቤኒን አምባሳደር ኤሎኢ ኡሩኦ ይገኙበታል።
የናይጄሪያው የቀድሞ ፋይናንስ ሚንስትር ጎዚ ኦኮንዳህ-ኢዌላ እና የቀድሞ ግብጻዊው ዲፕሎማት እና ድርጅቱን ለዓመታት ያገለገሉት ሃሚድ ማማዱ ቀጣዩ የዓለም ንግድ ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ድርጅቱን እየመሩ የሚገኙት ብራዚላዊው ሮቤርቶ አቬዜዶ ከድርጅቱ ዳይሬክተር ጄነራልነት በገዛ ፍቃዳቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ተከትሎ ነው አዲስ የድርጅቱ መሪን መሾም ያስፈለገው። ብራዚላዊውን ዳይሬክተር ጄነራልን የሚተካ እጩ በአንድ ወር ውስጥ መሾም ይኖርበታል።
የአፍሪካ ሕብረት አንድ እጩ ለማቅረብ ቢመክርም፤ የሚያቀርበውን እጩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ግን መለየት አይቻለውም እየተባለ ነው።
የዓለም ንግድ ድርጅት ከዚህ ቀደም ከአፍሪካ የሆነ ዳይሬክተር ጄነራል ኖሮት አያውቅም፤ በርካቶች አሁን ይህ ታሪክ የሚቀየርበት ወቅት ነው እያሉ ነው።
የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ብራዚላዊውን ተሰናባቸው ዳይሬክተር የሚተካ ከሕብረቱ እንዲሆን ፍላጎት አለው። ሕብረቱም ፍላጎቱን ለማሳካት ጫና እያሳደረ መሆኑ ተነግሯል።
በተለምዶ የድርጅቱ መሪ የሚሾመው አንዴ ከአደጉ አገራት፤ ቀጥሎ ደግሞ እያደጉ ካሉ አገራት በማፈራረቅ መሆኑን በማስታወስ፤ እያደገች ያለች ከምትባለዋ ብራዚል የሆኑትን ተሰናባቹ ዳይሬክተር ጄነራልን የሚተካው 'አደጉ' ከሚባሉ አገራት የሚገኝ እጩ ነው የሚሉም አልጠፉም።












