ኮሮናቫይረስ በቻይና ከተባለው ጊዜ ቀድሞ መከሰቱን የሳተላይት ምስሎች ጠቆሙ

ሰዎች በጎዳና ላይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች የታየው ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ የኮሮናቫይረስ እንደተከሰተ ከተነገረበት ጊዜ ቀድሞ ሳይጀምር እንዳልቀረ እንደሚያመለክቱ አንድ ጥናት ጠቆመ።

በከተማዋ የሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች አካባቢ ከነሐሴ እስከ ታኅሳስ ወር ድረስ ባሉት ጊዜያት በትራፊክ ተጨናንቀው መታየታቸውን የሳተላይት ምስል መረጃዎች ማመልከታቸውን ያስታወቁት የሃርቫርድ ተመራማሪዎች ናቸው።

በጊዜው የታየው የትራፊክ ፍሰትም፤ ስለሳልና ተቅማጥ ምልክት ምንነት የተመለከቱ መረጃዎች ለማግኘት ወደ ድረ ገጾች ጎራ የሚሉ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ቁጥር ጋር መገጣጠሙንም ጥናቱ ያስረዳል።

ቻይና ጥናቱ በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ እና እርባና ቢስ ነው ስትል አጣጥለዋለች።

ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻይና የታየው በህዳር ወር እንደሆነ ይታመናል።

ባለሥልጣናትም ባልታወቀ ምክንያት በሳንባ ምች በሽታ የተያዙ ሰዎች እንዳሉ ለዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቁት ግን ታኅሳስ ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ከተገለጸበት ጊዜ አስቀድሞም በተወሰነ ደረጃ ማኅበራዊ መረበሾች እንደነበሩም የጥናቱ መሪ ዶ/ር ጆን ብሮውንስቴን ለኤቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።

በእርግጥ ጥናቱ በዘርፉ ባለሙያዎች አልተገመገመም።

ጥናቱ ያሳየው ምንድን ነው?

አጥኚዎቹ ከአምስት የዉሃን ሆስፒታሎች እንቅስቃሴን የሚያሳዩ የንግድ ሳተላይት የምስል መረጃን የመረመሩ ሲሆን መረጃውን ከዚህ ቀደም ከነበረው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር አነጻጽረውታል።

በዚህም በጎርጎሮሳዊያኑ ህዳር 2018 ቲያንዮ በተባለ በዉሃን በሚገኝ ትልቅ ሆስፒታል 171 መኪናዎች ቆመው የተመለከቱ ሲሆን፤ በ2019 በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ 285 መኪናዎች ቆመው እንደነበር የሳተላይት ምስሉ አሳይቷል ተብሏል።

ይህም ቀድሞ ከነበረው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የትራፊክ ፍሰቱ 67 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በዚሁ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን በቻይና ባይዱ በተሰኘ የኢንትርኔት መፈለጊያ ዘዴ ላይ [ሰርች ኢንጅን] የሚያስሱ ሰዎች ታይተዋል።

ይህም በዉሃን በወቅቱ የተከሰተ አንዳች ነገር ስለመኖሩ የሚያሳዩ ተጨባጭ መረጃዎች ናቸው ብለዋል ዶ/ር ብራውንስቴን።

የዉሃን ሆስፒታል እንቅስቃሴን የሚያሳይ ሳተላይት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Image copyrightHARVARD UNIVERSITY

የምስሉ መግለጫ, አጥኚዎቹ ከተጠቀሙበት የዉሃን ሆስፒታል እንቅስቃሴን ከሚያሳዩ ሳተላይት ምስሎች መካከል አንዱ

የጥናቱ አንድምታዎች ምንድን ናቸው?

በቤይጂንግ የሚገኘው የቢቢሲው ዘጋቢ ጆን ሱድወርዝ፤ ጥናቱ በተካተቱ መረጃዎች ላይ ውስንነት እንዳለ ያሳያል ብሏል። ጆን በምሳሌ ሲያስረዳም፤ አንዳንዶቹ ፎቶግራፎች በደመና የተሸፈኑ በመሆናቸው ለተከታታይ ዓመታት በተመሳሳይ ጊዜ የተነሱ የሳተላይት ምስሎችን ሁልጊዜ ማወዳደር አይቻልም ይላል።

ከዚህም ባሻገር ጥናቱ በጠቀሰው ጊዜ ወረርሽኙ ቢኖር ምናልባት የተወሰኑ ሰዎች ዉሃንን ጥለው በመውጣት ወደ ሌሎች አገራት ይጓዙ ነበር፤ ልክ በሌሎች የዓለም አገራት ኮቪድ-19 ሲከሰት የነበሩና እያየነው ካለው አንዳንድ መረጃዎች ጋር ተመሳሳይ ይሆን ነበር ብሏል።

ምንም እንኳን ቻይና ስለ ቫይረሱ ለማሳወቅ ዘግይታለች ለሚለው ሃሳብ ጥናቱን እንደ ማስረጃ መጠቀም ፍትሃዊ ባይሆንም፤ ምክንያቱ በውል የማይታወቅ በሽታ በማኅበረሰብ ውስጥ ሲከሰት በይፋ የበሽታው ምንነት ሳይታወቅ ሊስፋፋ ይችላል ሲል ሃሳቡን ሰንዝሯል።

ቻይና መነሻው በውል ባልታወቀ የሳንባ ምች በሽታ ሰዎች መያዛቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት ያሳወቀችው በጎርጎሮሳዊያኑ ታህሳስ 31/2019 ነበር።

ከዘጠኝ ቀናት በኋላ የቻይና ባለሥልጣናት የሳንባ ምች በሽታ በተያዙ አብዛኞቹ ሰዎች የኖቨል ኮሮናቫይረስ ማግኘታቸውን አስታወቁ። በኋላም ቫይረሱ ኮቪድ-19 በሽታን የሚያስከትል ሳርስ-ኮቪድ-2 የሚል ስያሜ ተሰጠው።

ከዚያም ጥር 23 /2020 ዉሃንና ሌሎች የቻይና ከተሞች ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ ያቸውን ገደቡ።

የዓለም ጤና ድርጅትም ከሰባት ቀናት በኋላ ከቻይና ውጪ ባሉ አገራት 82 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ በሽታውን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን ማወጁ ይታወሳል።

ኮሮና
Banner