የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከ97 ዓመት በኋላ ዜጎቿን በማርስ ለማስፈር አቅዳለች

የፎቶው ባለመብት, THE MOHAMMED BIN RASHID SPACE CENTR
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንኩራኩር ወደ ማርስ ለመላክ ጫፍ የደረሰች ሲሆን በዚህም ወደ ማርስ የምታመጥቀው የጠፈር መርከብ ከአረቡ ዓለም ቀዳሚ ያደርጋታል።
የዚህ የጠፈር ጉዞ 7 ወራት ይወስዳል። በጠፈር መርከብ ከመሬት ወደ ማርስ ምህዋር ጉዞ 500 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ይጠጋል።
የሰው አልባ መንኩራኮሯ ተልዕኮ የማርስን ምህዋር በመሾር የአየር ንብረትና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ለቃቅሞ ወደ ምድር ማቀበል ነው።
እነዚህን እጅግ አስፈላጊ የተባሉ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለመሰብሰብ 687 ቀናትን በዚያው ትቆያለች።
አንድ ጊዜ የማርስን ምህዋር ለመዞር በአማካይ 55 ሰዓት ይወስድባታል።
ትናንት ሰኞ የዚህ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሰላህ አል አሚሪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ይህ ጉዞ ሲሳካ ለወጣት አረብ ሳይንቲስቶች ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል። "ለህዋ ምሕንድስናም አዲስ ምዕራፍ ይሆናል" ብለዋል።
የዚህች ተልዕኮ ስም "አማል" ሲሆን ትርጉሙም ተስፋ እንደማለት ነው።
የጠፈር መርከቧ የምትነሳው በሩቅ ምሥራቅ ከምትገኝ ታኔጋሺማ ከምትባል የጃፓን ደሴት ሲሆን በሐምሌ 14 ጉዞዋን ትጀምራለች ተብሎ ይጠበቃል።
የምትመጥቅበት ሮኬት የጃፓን ስሪት ሲሆን ሮኬቷ ሦስት ሙቀት መቆጣጠርያና መረጃ መቀበያ መሣሪያዎች ተገጥመውላታል። የያዘችው ከፍተኛ ጥራት ያለው ካሜራ ብናኝና የኦዞን አየርን ጭምር እንዲለካና ቀርጾ እንዲያስቀር ያስችላታል።
ሁለተኛው መሣሪያ ደግሞ የኢንፍራሬድ ስፔክትረም ሲሆን የህዋን የላይኛውና የታችኛውን ሽፋን ይለካል። ይህ መሣሪያ የተሰራውም በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርስቲ ነው።
ሦስተኛው የተገጠመው መሣሪያ አልትራቫዮሌት ስፔክትሮሜትር ሲሆን የኦክሲጂንና የሀይድሮጂን መጠንን ይለካል።
የዚህ ተልዕኮ አንዱ ዓላማ ለውሃ እጅግ አስፈላጊ የሆኑት የኦክሲጅናና የሀይድሮጂን ምጣኔዎች ከፕላኔት እንዴት እየሸሹ እየሄዱ እንደሆነ መረዳት ነው።
ሰር ኢያን ብላችፎርድ በእንግሊዝ ሳይንስ ሙዚየም ግሩፕ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት አብዛኞቹ እስከዛሬ ወደ ማርስ የተደረጉ የምርምር ጉዞዎች ዓላማ የከርሰ ምድር ጥናት (ጂኦሎጂ ተኮር) የነበረ ሲሆን ይቺ የአረብ ኢምሬቶች መንኮራኩር ጉዞ ግን ለአየር ንብረት ጥናት መሆኑ ልዩ ያደርጋታል።
ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የህዋ ጉዞ ስታደርግ ይህ የመጀመርያዋ አይደለም። በተለይ ወደ ምድር ምህዋር ሮኬቶችን ልካ ታውቃለች። አንድ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዋንም ከዚህ ቀደም ወደ ዓለም አቀፉ የህዋ ጣቢያ ልካ ነበር።
በዓረቡ ዓለም ወደ ሕዋ በመጓዝ የመጀርያው ሰው የሳኡዲው ልዑል ሱልጣን ቢን ሳልማን አል ሱኡድ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ1985 በአሜሪካ የህዋ መጓጓዣ ነበር ልዑሉ ጉዞውን ያደረጉት።
ይህ ተልዕኮ ግን ከልዑሉ ጋር የሚስተካከል አይደለም።
አንደኛው ይህ የህዋ መጓጓዣ የተገነባው በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የራሷ አቅም ሲሆን ወደ ጃፓን ደሴት ከተጓጓዘ በኋላ የሥነ ፈለክ ሳይንቲስቶች ለጤና ሲባል ለይቶ ማቆያ ውስጥ ገብተው እንዲቆዩ ይደረጋል።
በብሪታኒያ ኦፕን ዩኒቨርስቲ የህዋ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ሞኒካ ግራዲ እንደሚሉት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የምታደርገው ይህ ጉዞ በዓለም ኃያላን መንግሥታት ብቻ ተይዞ የነበረውን ዘርፍ የሚቀይር ይሆናል።
"ይሳካል ብዬ አስባለሁ፤ የማርስ ጉዞ ብዙውን ጊዜ እክል አያጣውም፤ ዞሮ ዞሮ ይህ ጉዞ በናሳና በአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ መዳፍ ሥር የወደቀውን ዘርፍ ሌሎችም አገራት እንዲገቡበት የሚያደፋፍር ይሆናል።"
ዩናይትር አረብ ኢምሬትስ በዚህ ጉዞ ለዓለም ማሳየት የፈለገችው ከ8 ዓመታት በፊት የአረብ ምሁራን እና ተመራማሪዎች በሳይንሳዊ ምርምር ቀዳሚ እንደነበሩ ነው።
የዱባይ ገዥ በዚህ ሕልማቸው በነበረው የህዋ ጉዞን እጅግ ተደስተዋል ተብሏል።
አንዱ ዓላማ የአረቡን ዓለም በነዳጅ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ያለውን ምጣኔ ሀብት ለመቀያየጥ ያደርጋል።
ይህ የህዋ ጉዞ ስኬታማ ከሆነ ለአረቡ ዓለም ኩራትን የሚፈጥር ነው ተብሏል።
ይቺ መንኩራኩር በለስ ቀንቷት ቀይዋ ፕላኔት ጋር ከደረሰች፣ እዚያ መድረሷ የሚበሰርበት ዕለት ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ 50ኛ ዓመት ብሔራዊ በዓል ጋር ይገጣጠማል።
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እንደ አገር የተመሠረተችው እንደ አውሮፓዊያኑ በ1971 ዓ.ም ነበር።
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በ2117 ዓ.ም በማርስ ዜጎቿን የማስፈር እቅድ አላት። ይህም የሚሆነው ከ97 ዓመታት በኋላ ነው።












