የፌስቡክ ሠራተኞች በመሥሪያ ቤታቸው ድርጊት ተበሳጩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፌስቡክ ሠራተኞች ድርጅታቸው የዶናልድ ትራምፕን ‹‹ያልተገባ›› የፌስቡክ 'ፖስት' አለመሰረዙ ወይም ማስጠንቀቂያ አለመጻፉ እንዳበሳጨቸው በይፋ ተናገሩ፡፡
ባለፈው ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ በሜኔሶታ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ሕዝብን ከሕዝብ ሊያጋጭ የሚችል የተባለ መልእክት በትዊተር ገጻቸው ለጥፈው ነበር፡፡
ትዊተር መልእክቱ ላይ ‹‹ህውከት ቀስቃሽ›› እንደሆነ የሚያመላክት ምልክት በማድረጉ ፕሬዝዳንቱን ማስቆጣቱ ይታወሳል፡፡
ያው የፕሬዝዳንቱ የማኅበራዊ መዲያ መልእክት ግን ትራምፕ ፌስቡክ ገጻቸው ላይ ጽፈውት ሳለ ድርጅቱ ምንም እርምጃ አለመወሰዱ የገዛ ሰራተኞችን ቅር አሰኝቷል፡፡
ትዊተር በወቅቱ የፕሬዝዳንቱ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ የጻፉት ነገር ተገቢ አለመሆኑን ለማሳየት ከመልእክቱ ጎን ‹‹ሁከትን የሚያበረታታ›› የሚል የማስጠንቀቂያ ምልክት አድርጎበት ነበር፡፡
ፌስቡክ ግን ይህንኑ ሁከት ቀስቃሽ የተባለ የፕሬዝዳንቱን መልእክት የማንሳትም ሆነ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ሙከራ አለማድረጉ ሲያስተቸው ቆይቷል፡፡
አንዳንድ የፌስቡክ ኩባንያ ሠራተኞች "በድርጅታችን አፍረናል" ሲሉ በይፋ ተናግረዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱ ሁከት ቀስቃሽ የተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መልእክት ‹‹ዝርፍያ ሲጀመር ተኩሱ ይንጣጣል›› የሚል ይዘት ነበረው፡፡ ይህ አባባል በታሪክ ጥቁሮች ላይ ከተደገ ጭቆናና ግድያ የሚተሳሰር "ውስጠ ወይራ መልእክት" እንዳለው ይነገራል፡፡
የፌስቡክ መሥራች ማርክ ዙክርበርግ ይህ የፕሬዝዳንቱ መልእክት ፖሊሲያችንን አይቃረንም ሲል የዶናልድ ትራምፕን መልእክት መርዘኝነት ለማርከስ ሞክሯል፡፡
የማርክ ዙከርበርግ ሠራተኞች ግን ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የመሥሪያ ቤታቸውን "በምናብ ለቆ የመውጣት ተቃውሞ" አድርገዋል፡፡ ይህም የሆነው በየኮምፒውተር ገጾቻቻቸው የጋራ መልእክት መለዋወጫ መድረክ ላይ "በተቃውሞ ምክንያት ከቢሮ ለቅቄ ወጥቻለሁ" የሚል መልእክት በመጻፍ የተደረገ ተቃውሞ ነበር፡፡
ላውረን ታን የተባለች የድርጅቱ ሰራተኛ "በመሥሪያ ቤቴ ድርጊት እጅግ አፍሪያለሁ፤ ምንጊዜም ዝምታ የወንጀል ተባባሪነት ነው፡፡ ዝም አልልም" ስትል ጽፋለች፡፡
ሌሎች ሰራተኞች ደግሞ ተቃውሟቸውን በድርጅቱ የውስጥ መገናኛ ዘዴ ለመግለጽ ተገደዋል፡፡
የፌስቡክ ኩባንያ ቃል አቀባይ በበኩሉ "የሰራተኞች ሕመምና ቅሬታ ይገባናል፤ ዋናው እንዲህ በግልጽ መነጋገራችን ነው፡፡ ሰራተኞቻችንን ቅሬታቸውንም ሆነ ተቃውሟቸውን እንዲህ በግልጽ እንዲናገሩ ነው የምንፈልገው፤ ገና ብዙ አጨቃጫቂ ነገሮች ከፊታችን ይጠብቁን የለ?" ብሏል፡፡
ይህን የፕሬዝዳንቱን አወዛጋቢ ንግግር ተከትሎ ባለፈው ዓርብ ዶናልድ ትራምፕና ማርክ ዙከርበርግ በጉዳዩ ላይ በስልክ የተወያዩ ሲሆን ዝርዝር የንግግራቸው ይዘት ግን ይፋ አልተደረገም፡፡ ሁለቱም ውይይታችን ፍሬያማ ነበር ቢሉም ፍሬያማ ያሰኘው ምኑ እንደሆነ ግን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
ይህን አተካራ ተከትሎ ፌስቡክ ከውስጥም ከውጭም የተነሳበትን ቅሬታ ለማለዘብ ይመስላል 10 ሚሊዮን ዶላር በፍትህ ሂደት ለሚፈጠር ዘረኝነትን ለመዋጋት ይሆን ዘንድ እርዳታ አድርጊያለሁ ሲል ይፋ አድርጓል፡፡
"እንሰማለን፣ እናያለን ከናንተው ጋር ነን" ሲል የጸረ ዘረኝነት ተቃውሞውን እንደሚደግፍ አሳውቋል፡፡
"የጥቁሮችን ድምጽ እናስተጋባለን፤ ዘረኝነትን እንጸየፋለን ከጎናችሁ እንቆማለን" ያለው ፌስቡክ 10 ሚሊዮን ዶላሩን ለምን እንዴትና ለማን እንደሚሰጥ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡

















