በስሪ ላንካ 361 ዝሆኖች ተገድለዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Anbarasan Ethirajan
ስሪ ላንካ በታሪኳ እጅግ ከፍተኛው በተባለ የዝሆኖች ሞት በፈረንጆቹ 2019 361ዱን እንዳጣች አንድ የአካባቢ ተቆርቋሪ ቡድን አስታወቀ።
ስሪ ላንካ ነጻነቷን ካገኘችበት የፈረንጆቹ 1948 ጀምሮ እንዲህ አይነት የዝሆኖች ሞት ታይቶ አይታወቅም ያለው ቡድኑ ለአብዛኛዎቹ የሞታቸው ምክንያት ሰዎች እንደሆኑ ገልጿል።
በስሪ ላንካ እስከ 7500 ሚደርሱ ዝሆኖች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን እነሱን መግደል በሀገሪቱ ሕግ መሰረት ወንጀል ነው። ዝሆኖቹ ምግብና ውሀ ፍለጋ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወደ ሰዎች መኖሪያ አካባቢ ይገባሉ።
በገጠራማዊቱ ስሪ ላንካ የሚኖሩ ዜጎች ደግሞ ዝሆኖቹ ሰብላቸውን ስለሚያበላሹባቸው እንደ ጠላት ነው የሚመለከቷቸው።
'ሳጂዋ ቻሚካራ' የተባለው የአካባቢ ተቆርቋሪ ቡድን ለቢቢሲ እንደገለጸው ባለፈው ዓመት ከሞቱት 361 ዝሆኖች መካከል እስከ 85 በመቶ የሚደርሱት የተደገሉት በሰዎች ነው።
የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ አጥሮችን፣ መርዝና ፈንጂዎችን በመጠቀም ዝሆኖቹን የሚገድሉ ሲሆን አንዳንዶቹም ለምግብነት እንደሚጠቀሟቸው ቡድኑ ገልጿል።
ባለፈው መስከረም ወር ላይ የሀገሪቱ ሃላፊዎች እንደገለጹት ሰባት የሚሆኑ ዝሆኖች 'ምርት አበላሹ' በሚል ምክንያት በአካባቢው ነዋሪዎች ተመርዘው እንዲሞቱ ተደርገዋል።
ቢቢሲ የዘርፉ ባለሙያዎችን አነጋግሮ ባገኘው መረጃ መሰረት በስሪ ላንካ ገጠራማ ክፍሎች ጫካዎች እየተመነጠሩ አዳዲስ የእርሻ ማሳዎች ስለሚዘጋጁ ዝሆኖቹ ተፈጥሯዊ መኖሪያቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ እየተገደዱ ነው።
በዚህም ምክንያት ለዝሆኖቹ ምግብና ውሃ ማግኘት እጅግ ከባድ ሆኖባቸዋል ተብሏል።












