ያልተፈላ ወተት ለጤና ጠቃሚ ነው ጎጂ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያልተፈላ ወተት ወይም በሳይንሱ 'ፓስቸራይዝ' ያልተደረገ ወተት መጠጣት የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅምን ከመጨመር ባለፈ የተለያዩ አለርጂዎችን መከላከልና ሥርዓተ ልመትን (የምግብ በሰውነታችን ውስጥ መዋሃድን) የማፋጠን ጥቅም እንዳለው ይነገራል።
ነገር ግን ወተትን ማፍላት አስፈላጊ የሆነበት የራሱ ምክንያት አለው። በጥሬ ወተት ውስጥ ያሉትን ባክቴሪያዎች ለመግደልና ወተቱ ሳይበላሽ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ ለማድረግ ነው።
እንግሊዝ፣ ዌልስ፣ ስኮትላንድ እና ሰሜን አየርላንድ ውስጥ ፓስቸራይዝ ያልተደረገ ወተት በሱፐርማርኬቶችም ሆነ በትንንሽ ሱቆች ውስጥ በህግ የተከለከለ ነው። ለመሆኑ ጥሬ ወተት በጣም ወሳኝ ምግብ ነው ወይስ ለጤና ጎጂ ነው?
ብዙዎቻችን ወተት የምንጠጣው በውስጡ ብዙ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ስለያዘ ነው። ነገር ግን በወተት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ቫይታሚኖች ሙቀትን መቋቋም የማይችሉ ናቸው። ይህ ማለት ደግሞ እሳት ሲነካቸው ለሰውነታችን ሊያበረክቱ የሚችሉት ጥቅማቸው በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ማለት ነው።
ካናዳ ውስጥ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት ወተትን ስናፈላው ጥቅሙን የማጣቱ እድል ዝቅተኛ ነው። ነገር ግን ቫይታሚን ቢ2 የሚባለው ንጥረ ነገር በሙቀቱ ምክንያት ሊጠፋ ይችላል።
አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ያልተፈላ ወተትን መጠጣት የሚመርጡት ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆኑ ባክቴሪያዎችን በውስጡ ይዟል ብለው ስለሚያምኑ ነው። ማፍላት በባህሪው ጠቃሚውንም ጎጂውንም ባክቴሪያ ይገድላል።
ነገር ግን ትኩስ ከላም በታለበ ወተት ውስጥ የጠቃሚ ባክቴሪያዎች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። እንዲያውም ወተት ሳይፈላ ለቀናት ሲቆይና እርጎን ወይም አይብን ወደመሳሰሉ የምግብ አይነቶች ሲቀየር በውስጡ በጣም ብዙ ጠቃሚ ባክቴሪያዎችን ይይዛል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አለርጂዎችን ከመከላከልና በሽታ የመከላከል አቅምን ከመጨመር አንጻር ያልተፈላ ወተት ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ቢገለጽም አመርቂ የሆነ ውጤት ግን እስካሁን አልተገኘም።
በግብርና ሥራ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች ላይ በተሰራ አንድ ጥናት ላይ የቤተሰቡ አባላት ያለባቸው የአለርጂ መጠን ዝቅ ያለና በሽታን የመከላከል አቅማቸው ደግሞ ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቁሟል።
ነገር ግን ይህ የሆነው ያልተፈላ ወተት ስለጠጡ ይሁን አይሁን እርግጠኛ መረጃ ማግኘት አልተቻለም።
የእንግሊዙ የምግብ ደረጃዎች አውጪ ባለስልጣን ደግሞ ያልተፈላ ወተት በውስጡ የሚይዛቸው ጎጂ ባክቴሪያዎች የምግብ መመረዝን ሊያስከትሉ ይችላሉ ይላል። አክሎም በሽታን የመካከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ነፍሰ ጡር ሴቶች፣ ህጻናትና በእድሜ የገፉ ሰዎች ያልተፈላ ወተትን ለመቅመስ እንኳን ማሰብ የለባቸውም ብሏል።
ያልተፈላ ወተት ሳልሞኔላ፣ ኢኮላይ እና ካምፒሎባክተር የሚባሉ ጎጂ ባክቴሪያዎች በውስጡ ይገኝበታል።
በእንግሊዙ ሰሬይ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ማይክሮባዮሎጂ መምህር የሆኑት ዶክተር ዮርግ ጉቴሬዝ እንደሚሉት ያልተፈላ ወተት መጠጣት ለጤና ጎጂ ነው። ባልተፈላ ወተት ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎች የአንጀት በሽታ ከማስከተል ባለፈ እስከ ሞት ሊያደርሱ እንደሚችሉም ያስረዳሉ።














