የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ሪክ ማቻር እና ሳልቫ ኪር እርቅ አወረዱ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና ተቃዋሚው ሪክ ማቻር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ተቃዋሚው ሪክ ማቻር (ግራ) እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር (ቀኝ)

አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ አንድ አዳራሽ በሰው ተሞልቷል፤ ጭብጨባው ደርቷል፤ እልልታ እና ፉጨቱም እንዲሁ።

ይህ የሆነው የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና ተቃዋሚው ሪክ ማቻር የመጨረሻ ያሉትን የሰላም ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ነው።

ግለሰቦቹ በፈገግታ በመታጀብ የተፈራረሙትን የሰላመ ሰነድ በጎረቤት ሃገራት መሪዎች ፊት ተቀባብለዋል።

የምስራቅ አፍሪቃ የልማት ትብብር በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) መሪዎች፤ ግለሰቦቹ ወደሰላም እንዲመጡ መግፋት ከጀመሩ ብዙ ጊዜ ሆኗቸዋል።

ለአምስት ዓመታት በዘለቀው የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት አስር ሺዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

የኢጋድ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባም ሁለቱን መሪዎች ወደ እርቅ ለማምጣጥ ያልጣለችው ድግስ አልነበረም።

«ይህንን ታሪካዊ ቅፅበት እውን በምናደርግበት ወቅት፤ በእርስ በርስ ጦርነቱ ያለቁ ሰዎችን ልንረሳ አይገባም። ይህ ስምምነትም የደቡብ ሱዳንን መፃኢ ተስፋ ብሩህ እንደሚያደርገው ተስፋ አለኝ» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ንግግር አድርገዋል።

በደቡብ ሱዳን ለተከሰተው እልቂት ሁለቱም ወገኖች ተጠያቂነቱን እንደሚወስዱ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የተባበሩት መንግሥታት በሃገሪቱ እጅግ አሰቃቂ ግድያዎች እንዲሁም አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎች እንደተፈፀሙ መረጃው አለኝ ይላል።

አልፎም ግጭቱ ባመጣው የኑሮ ውድነት ምክንያት ሚሊዮኖች ለምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ነው የእርዳታ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ያሉት።