የምዕራባውያን ልዩ ተዋጊዎች በዩክሬን መኖራቸውን ሾልኮ የወጣ ሰነድ አጋለጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሾልኮ የወጣ ሚስጥራዊ ሰነድ የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ምዕራባውያን ልዩ ኃይሎች በዩክሬን ኦፕሬሽን ላይ እንደሚገኙ አጋለጠ።
መጋቢት 14/2015 ዓ.ም. የሚል ቀን የሰፈረባቸው ሰነዶች በዩክሬን የሚገኙ ትልቁን ቦታ የሚይዙት የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች መሆናቸውን አሳይቷል።
ዩኬ 50፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆነችው ላትቪያ 17፣ የፈረንሳይ 15፣ የአሜሪካ 14 እና ኔዘርላንድስ 1 ተጠባበቂ ልዩ ኃይል አባላት በዩክሬን መኖራቸውን አሳይቷል።
ሰነዶቹ ለአንድ ዓመት ያክል የነበረውን ጥርጣሬ ያረጋገጡ ሆነዋል።
ሾልከው የወጡት ሰነዶች “ጥብቅ ምስጢር” ተብለው የተጻፈባቸው ሲሆን በዩክሬን ስላለው ጦርነት በዝርዝር ከማሳየታቸው በተጨማሪ፤ ኪዬቭ የሩሲያ ጥቃት ለመመከት እያደረገችው ስላለው የመልሶ ማጥቃት ዕቅድ ይዘረዝራል።
የአሜሪካ መንግሥት ሰነዶቹ እንዴት አደባባይ ሊወጡ እንደቻሉ ምርመራ እያደረኩ ነው ብሏል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ላሎይድ ኦስቲን የአገሪቱ ፍትሕ ቢሮ የወንጀል ምርመራ ማድረግ መጀመሩን እና ሰነዶቹን ይፋ ያደረገውን ለመለየት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
“ምርመራ ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ምንጩን እና ስፋቱን እስክንደርስበት ድረስ የማንፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም” ብለዋል።
ሰነዶቹ ምዕራባውያኑ ልዩ ኃይል አባላት በየትኛው የዩክሬን ክፍል እንደሚገኙም ሆነ በጦርነቱ ያላቸው ተሳትፎ ምን እንደሆነ ያሉት ነገር የለም።
በዩክሬን አሉ የተባሉት ምዕራባውያኑ ልዩ ኃይል አባላት በቁጥር አነስተኛ ይሁኑ እንጂ ውጤታማ እንደሆኑ ይታመናል።
ሩሲያ ከዚህ ቀደም እየተዋጋው ያለሁት ከዩክሬን ጋር ብቻ ሳይሆን ከኔቶ ጋር ጭምር ነው ብላ ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚንስቴር በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ትናንት ማክሰኞ በትዊተር ገጹ ሚስጥራዊ ሰነዶች ተብለው የሚጋሩ ሰነዶች “ከፍተኛ ስህተት” ስለሚኖራቸው አንባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብሏል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ስለየትኛው ሚስጥራዊ ሰነድ እንደሆነ በግልጽ ያለው ነገር የለም።
የዩኬ መከላከያ ሚንስትር ይህን ይበል እንጂ የፔንታጎን ኃላፊዎች ሰነዱ ትክክለኛ ስለመሆኑ መናገራቸው እየተዘገበ ነው።
የዩኬ ልዩ ኃይል አባላት በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ እውቀት እና ክህሎት ባላቸው የጦር አባላት የተዋቀረ ሲሆን፤ ስብስቡ በዓለም ላይ ትልቅ አቅም አላቸው ከሚባሉት መካከል አንዱ ነው።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንገድም በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጠንካራ የዩክሬን አጋር ከሆኑ አገራት መካከል ናቸው።












