የክልል ልዩ ኃይሎችን የማደራጀት ጅማሬ፣ ሂደት እና አሁን የደረሱበት አቋም

የኦሮሚያ እና የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት
የምስሉ መግለጫ, የኦሮሚያ እና የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተመሰረቱት ክልሎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ክልሎች በመደበኛ ሠራዊት ደረጃ ሰልጥነው የተደራጁ ልዩ ኃይሎችን ማደራጀት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ተጠሪነታቸው ለየክልሎቻቸው የሆኑት እነዚህን ልዩ ኃይሎች የማደራጀቱ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በትጥቅም ሆነ በቁጥር እየጨመረ በመሄድ የፌደራሉን መንግሥት ሠራዊት አስከመገዳደር ደርሷል።

ክልሎች ከፖሊስ በሻገር የታጠቀ የፀጥታ ኃይል ለማደራጀት የሚያስችላቸው የሕግ መሠረት ባይኖርም ባለፉት ዓመታት የሶማሌ፣ የትግራይ፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች መደበኛ ሠራዊት በሚመስል መልኩ በተከታታይ በማሰልጠን በከፍተኛ ቁጥር ሲያስመርቁ ነበር።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ክልሎች እንዲህ ያለውን የራሳቸውን ልዩ ኃይል አደራጅተው እና አስታጥቀው ማሰማራታቸው ለአገር ደኅንነት አደጋ ነው የሚሉ አሉ። የእነዚህ ኃይሎች አደረጃጀትም ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው በማለትም ይሞግታሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የልዩ ኃይልን አቅምን ከግምት በማስገባት በየክልሉ የሚያጋጥሙ የፀጥታ ስጋቶችን በቅርበት ለመቆጣጠር እና የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከፖሊስ በተጨማሪ ልዩ ኃይል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበርክት ይችላል የሚሉም አሉ።

የልዩ ኃይል ጅማሬ እና እድገት

በኢትዮጵያ የክልል ልዩ ኃይልን ማደራጀት የተጀመረው በ1998 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል ውስት የነበረውን የሸማቂ ኃይል እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ነበር።

በወቅቱ በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባርን (ኦብነግ) ተዋጊዎች ለመቆጣጠር በፌደራል መንግሥቱ ድጋፍ ነበር ልዩ ኃይሉ የተደራጀው።

ቀጥሎ ደግሞ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የራሳቸውን ልዩ ኃይል ማደራጀት ጀመሩ። በዚህም አዲስ የተመሠረቱትን ጨምሮ በሌሎችም ክልሎች ልዩ ኃይል የማቋቋም ልምዱ ተስፋፍቶ ቀጠለ።

የክልሎች ልዩ ኃይሎች በመጀመሪያ ላይ ሲመሰረቱ በፖሊስ ስም የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት “ልዩ ፖሊስ” በመባል ሲጠሩ ቆይተዋል።

ነገር ግን አደረጃጀታቸው፣ ኃላፊነታቸው እና ትጥቃቸው ከፖሊስ የተለየ ከመሆኑም ባሻገር ከመደበኛ ጦር ሠራዊት ጋር የሚስተካከል በመሆኑ ቀስ በቀስም የእነዚህ ታጣቂ የክልል ኃይሎች መጠሪያ ከልዩ ፖሊስነት ወደ ልዩ ኃይልነት ተሸጋገረ።

እነዚህ ልዩ ኃይሎች የታጠቁ አማጺያን እና የወንጀል ቡድኖች ላይ ያነጣጠሩ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

በተጨማሪም የወሰን ችግር ባለባቸው ክልሎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ የክልሎቹ ልዩ ኃይሎች ጥቃት በመፈጸም ሲከሰሱ ቆይተዋል።

በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ተደራጅተው የሚገኙት ልዩ ኃይሎች አወቃቀር እና ትጥቅን በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ሲነሳበት እና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በተለያዩ ወገኖች ሃሳብ ሲሰነዘር ቆይቷል።

በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ልይ ኃይሎች ከፖሊስ እና ከአካባቢ የፀጥታ ኃይሎች በተለየ ሁኔታ ወታደራዊ ሥልጠና እና ትጥቅ ያላቸው በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን ባለፉት ዓመታት አደራጅተዋል።

ካርታ
የምስሉ መግለጫ, የፌደራሉ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ መከላከያ እና ፖሊስ ኃይል ለማካተት ያወጣውን ዕቅድ ተከትሎ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ውስጥ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል

የልዩ ኃይሎች ሥልጠና እና ትጥቅ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከልዩ ኃይል ጋር በተያያዘ ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ የሰው ኃይላቸው፣ የታጠቁት መሣሪያ አይነት እና ብዛትን የሚመለከት ነው።

በክልሎች የተደራጁ ልዩ ኃይሎች ያላቸውን የሠራዊት ብዛት እና የታጠቁት መሣሪያን በተመለከተ ይፋዊ መረጃ ለማግኘት አዳጋች ነው።

ክልሎች በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የነበራቸውን የልዩ ኃይል ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሲያሳድጉ ታይተዋል። ይህም ሆኖ ያላቸው የልዩ ኃይል ቁጥር ግን በግልጽ አይታወቅም።

በአንዳንድ ክልሎች ያሉት ልዩ ኃይሎች የታጠቋቸው መሣሪያዎች የፖሊስ ኃይል ካለው በእጅጉ የበለጠ እና ዘመናዊ ጭምር መሆኑ ይነገራል።

ሌሎች ደግሞ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር የሚመጣጠን ጭምር መሣሪያ አስከ መታጠቅ የደረሱ እንዳሉ ይጠቁማሉ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከደቡብ ክልል ወጥተው እራሳቸውን የቻሉት አዲሶቹ ክልሎች ሳይቀሩ ካዋቀሯቸው የመስተዳደር አካላት እኩል ይነስም ይብዛ “ልዩ ኃይል” አቋቁመዋል።

ክልሎች በሕግ እንዲኖራቸው ከተቀመጠው የፖሊስ ኃይል በተጨማሪ ይህንን ልዩ ኃይል ሲያዋቅሩ ሥልጠናው፣ የደንብ ልብሱ፣ ትጥቁ እና አደረጃጀቱ የብዙዎቹ ከመደበኛው የፖሊስ መዋቅር የለየ።

ትላልቆቹ ክልሎች በአንድ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ኃይል አባላትን አሠልጥነው በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ማስመረቃቸውን በየጊዜው በመገናኛ ብዙኃን ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል።

ከአውቶማቲክ የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች አንስቶ የቡድን እና ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ያሏቸው እንዳሉም በተለያዩ ጊዜያት ባቀረቧቸው ወታደራዊ ትዕይንቶች ላይ ታይተዋል።

እንደሚታወቀው የክልል መደበኛ ፖሊሶች የክልሎቻቸው መለያ ከሆነው አርማ በስተቀር የመደንብ ልብሳቸው ወጥ እና ተመሳሳይ ነው። ወደ ልዩ ኃይል ሲመጣ ግን የእያንዳንዱ ክልል የደንብ ልብስ የሚለይ ነው።

የአማራ ልዩ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የአማራ ልዩ ኃይል አባላት

ልዩ ኃይል እና ክልሎች

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ክልሎች ሁሉም በሚባል ደረጃ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ የወሰን ይገባኛል ጥያቄን ሲነሱ፣ አንዳንድ ጊዜም ግጭቶች ሲከሰቱ እንደነበር ይታወሳል።

በእንዲህ አይነት በክልሎች መካከል በሚከሰቱ አለምግባባቶች ውስጥ የተለያዩ ክልሎች የልዩ ኃይል አባላት ጥቃቶችን በመፈጸም ሲከሱ ነበር።

በዚህም የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች ተጠቃሶች ናቸው። በሁለቱ ክልሎች መካከል ባሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች ውስጥ በሚነሱ የቦታ ይገባኛል ምክንያት በማኅበረሰቦች መካከል ግጭቶች በተከሰቱ ቁጥር ልዩ ኃይሎች በተደጋጋሚ ስማቸው ሲነሳ ይደመጣል።

በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በሲዳማ እና በደቡብ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ማኅበረሰቦች መበተለያዩ ጊዜያት በግጦሽ መሬት እና በይዞታ ይገባኝል ምክንያት በተከሰቱ አለመግባባቶች እና ግጭቶች መካከል የየክልሎቹ ልዩ ኃይሎች ስም ተደጋግሞ ሲነሳ ቆይቷል።

በዚህም ልዩ ኃይሎቹ ከመጡበት ክልል ወገን ያሉ ማኅበረሰቦችን ወግነው በሌላኛው ላይ ግድያ፣ ጥቃት እና ንብረት ማውደም ፈጽመዋል እየተባለ አንደኛው ሌላኛውን ሲከስ ቆይቷል።

በተጨማሪም በራሳቸው በክልሎቻቸው ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ልዩ ኃይሎች ተሰማርተው የተለያየ መጠን ያለው ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደፈጸሙ የመብት ተሟጋቾች በተለያዩ ጊዜያት የዋጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

የክልል ልዩ ኃይሎች የደቀኑት ስጋት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ መከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት ለማስገባት በሚያደርገው ጥረት ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፣ የክልል ልዩ ኃይሎች ስጋት መደቀናቸውን ጠቅሰዋል።

“ኢትዮጵያ ከክልል ልዩ ኃይሎች ጋር በተያያዘ ከአንዴም ሁለት ጊዜ የአገርን ሉዓላዊነት እና አንድነት የተገዳደሩ ፈተናዎች ገጥመዋት እንደነበር አይዘነጋም። ከአንድነት እና ሉዓላዊነት ሥጋትነት በመለስም በክልሎች መካከል የማያስፈልግ ተፎካካሪነት እና ተገዳዳሪነት እንዲፈጠር መንስኤ ሲሆኑ እናያለን” ብለዋል።

ይህም ከጥቂት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ አሁን በእስር ላይ በሚገኙት የሶማሌ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አማካይነት በክልሉ ኃይል የተወሰደው እርምጃ እና ያስከተለው ጥፋት የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም አገሪቱን ያናጋት ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ክልል የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የክልሉ ልዩ ኃይል የነበረው ሚና ከዚህ አንጻር የሚጠቀስ ነው።

አንዳንድ ጊዜም እነዚህ ኃይሎች ከክልላቸው ውጭ በሚያደርጉት ተሳትፎ ስማቸው በበጎም በክፉም ይነሳል።

በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ወቅት ከመከላከያ ጎን ተሰልፈዋል በሚል በፌደራሉ መንግሥት ወገን ተሰልፈው በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው መስጋና እና አድናቆት ሲቀርብላቸው ነበር።

በዚህ ወቅትም ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የልዩ ኃይል አባላት መሳተፋቸውን መገናኛ ብዙኃን ደጋግመው ዘግበዋል።

በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሷን አሜሪካ ያሳወቀችው በቅርቡ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር፣ የህወሓት ኃይሎች እና የአማራ ኃይሎች ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት የጦር ወንጀሎች እና ከባድ የመብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል በሚል በመብት ድርጅቶች እና በአሜሪካ መንግሥት መከሰሳቸው ይታወቃል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት
የምስሉ መግለጫ, የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት

ልዩ ኃይሎችን መበተን፣ መልሶ ማደራጀት

ባለፉት ዓመታት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተደራጁት ልዩ ኃይሎች የየክልሎቻቸው ድጋፍ ይኑራቸው እንጂ፣ በአገሪቱ ሕግ የልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት የሚደግፍ ነገር የለም።

በዚህም የተነሳ የፌደራሉ መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ ወደ ተደራጀ ሠራዊትንት የደረሱትን የክልል ልዩ ኃይሎች በተመለከተ መላ እንዲፈልግላቸው ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ በተለይም በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መመስረት ከጀመረ ወዲህ፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ልዩ ኃይሎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲመዘግብ ቆይቷል።

አምስቲ እአአ በ2018 ባወጣው መግለጫ መንግሥት ልዩ ፖሊስን እንዲበትን እስከመጠየቅ ደርሶ ነበር።

በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ይፈጽማሉ ያላቸውን ልዩ ኃይሎች መንግሥት እንዲበትን እና ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙሰጠፌ ሞሐመድ ከሦስት ዓመት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ትኩረት ካደረጉባቸው ነገሮች አንዱ የልዩ ኃይል ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ነበር።

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በተደጋጋሚ የመብት ጥሰት እንደሚፈጽም ክስ ይቀርብበት የነበረው የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ፤ የአደረጃጀት ለውጦች እንደተካሄዱበት ፕሬዝደንቱ በወቅቱ ተናግረዋል።

የክልሎች የልዩ ኃይል አስፈላጊነትን በተመለከተም ሙሰጠፌ፤ “አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ልዩ ኃይል የሚያከናውናቸው ቀልጣፋ ሥራዎች አሉ። ልዩ ኃይል በእኛ ክልል ይቀጥላል” ሲሉም ተናግረው ነበር።

ነገር ግን “ወደፊት የክልል ልዩ ኃይሎች ከፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር ስለሚኖራቸው ቁርኝት ወይይቶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ” ብለው ነበር።