“የክልሎች ልዩ ኃይሎች በህገ መንግሥቱ ዕውቅና ስለሌላቸው ወደ ህጋዊ መስመር እያስገባን ነው” ጄነራል አበባው ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, EBC
የክልሎች ልዩ ኃይሎች ህጋዊ እንዳልሆኑና በህገ መንግሥቱም እውቅና የላቸውም ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ ተናገሩ።
ጄነራል አበባው ታደሰ አርብ መጋቢት 29፣ 2015 ዓ.ም ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ የክልሎች ልዩ ኃይሎች አመሰራረት ህገመንግሥታዊ እውቅና እንደሌለውና ወደ ህጋዊ መስመር ሊገቡ ይገባል ብለዋል።
መንግሥት የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ በማደራጀት በመከላከያ ሰራዊት በፌደራል ፖሊስ እና በክልል መደበኛ ፖሊሶች የማካተት ውሳኔ የጀመረ ሲሆን “በሁሉም ክልሎች እኩል በሆነ መንገድ ተፈጻሚ እየተደረገ መሆኑንም” ጄነራል አበባው ጠቅሰዋል።
“አንደኛውን ክልል ኃይል እንዲኖረው ሌላኛውን ክልል ደግሞ ኃይል እንዳይኖረው አናደርግም። ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ አይታሰብም፤ኢትዮጵያን በእኩል መንገድ ነው የምናያት” ብለዋል።
የክልሎች ልዩ ኃይሎች መልሶ ለማወቀርና ለማደራጀት ያስፈለገበትን ምክንያት፣ አፈጻጸሙንና እንዲሁም የአገሪቱን ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት የ35 ደቂቃ ቆይታ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በየክልሉ ያሉ ልዩ ኃይሎችን ማደራጀትና ማዋቀር ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፣ “ትጥቅ ማስፈታትም ሆነ ልዩ ኃይሉን መበተን “የሚባለው ትክክል አይደለም ወደ ህጋዊ መስመር ውስጥ የማስገባት ሂደት እንደሆነም ነው የጠቀሱት።
የአገሪቱን የጸጥታ ኃይል ግንባታን አስመልክቶ ህገ መንግሥቱ ያስቀመጠው በብሔራዊ ደረጃ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ለክልሎች መደበኛ ፖሊስ ብቻ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል።
የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ ማደራጀት በአሁኑ ወቅት በግብታዊነት ያልተጀመረና ለረጅም ጊዜ ጥናት መደረጉን ጠቅሰዋል።
የክልሉ ልዩ ኃይሎች ጥንካሬያቸው ምንድነው የሚለውንም በተገመገመበት ወቅት ልዩ ኃይሎቹ የክልላቸውን ጸጥታ መጠበቃቸው እንዲሁም ከመከላከያው ጋር አብረው በውጊያዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።
ሆኖም የክልሉ ልዩ ኃይሎች ህጋዊ ካለመሆናቸው በተጨማሪ ሌላኛው እክል ብለው ጄነራሉ የጠቀሱት ጉዳይ ልዩ ኃይሎች ምስረታቸውና አወቃቀራቸው “ብሔር ተኮር መሆናቸውን” ነው።
ባለው አወቃቀርም ምክንያት ልዩ ኃይሎች የራሳቸውን ብሔር ብቻ ለመጠበቅ ቃል የሚገቡበበት “በዚህም የሌሎች ብሔሮች ደህንነት ጉዳያቸው አይደለም” ሲሉም ተደምጠዋል።
አክለውም “ብሔር ተኮር ስለሆኑ አገር አቀፍ የሆነውን አብሮነት የመኖር የህዝቦችን አንድነት ይሸረሽራል” ብለዋል ጄነራሉ።
በዚሁ ቆይታቸው ጄነራሉ ልዩ ኃይል አገሪቷን የፖለቲካ መፍቻ መንገድ አበላሽቷል ብለዋል።
ፖለቲከኞች በኃሳብ ማሸነፍ ሲያቅታቸው ኃይልን መጠቀማቸውን ጠቅሰው ልዩ ኃይሉም የዚህ መሳሪያ ሆኗል በማለት የትግራይን ፖለቲከኞች ጠቅሰዋል።
በጥናቱ ላይ ተካቷል ያሉትና በባለፉት ዓመት ተስተውሏል ያሉት ሌላኛው ጉዳይ ልዩ ኃይሉ ብሔራዊ የሆነውን መከላከያ ኃይል መገዳዳሩን በመጠቆም ነው።
ጥናቱም ሆነ ህዝቡ “ይህ አካሄድ ልክ አለመሆኑን ሲጠቁም ወደ ሶስት፣ አራት አመታት ፈጅቷል” ብለዋል።
የልዩ ኃይሎቹን እንደገና ማደራጀት የዘገየውና ቅድሚያ መሰጠት የነበረበት የሰሜን ጦርነት ስለነበር እንደሆነም ለቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግረዋል።
ልዩ ኃይሉን በማሻሻል እናደራጅ የሚል ውሳኔ ነው እንጂ እንበትነው የሚል ውሳኔ እንዳልተሰጠም አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ትጥቁንም እናስፈታው፣ እንበትነው አልተባለም” ብለዋል።
የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ ማደረጀት ጋር በተያያዘ ልዩ ኃይል ሊበተን እንዲሁም ሊፈርስ ነው በሚል በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተቃውሞ እና ውጥረት ተከስቷል። ልዩ ኃይልና መከላከያ በአንዳንድ አካባቢዎችም መፋጠጣቸውም ተገልጿል።
ጄነራሉ በበኩላቸው ይህ ማሻሻያ ልዩ ኃይሉን በአዲስ መልኩ በማዋቀር አባላቱን በመከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ መደበኛ ፖሊስ በማካተት ህጋዊ ስርዓት ማስያዝ ነው ብለዋል። “ይህ ምን ክፋት አለው? “ ሲሉም ጠይቀዋል።
“ይህ የሚከናወነውም በልዩ ኃይሎች አባላት ምርጫና ክብሩና ሞራሉን እንዲሁም ጥቅሙን በማይነካ መልኩ” እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የአገሪቱን የጸጥታ ኃይል እንደ አቅም ለመጠቀም የክልሎቹንም ኃይል እንደ አገር ለመጠቀም ተደርጓል ባሉትም ጥናት ውሳኔ ሰጭ ለሆኑት የሁሉም የክልል አመራሮችና የመንግሥት ባለስልጣናት ቀርቦ ለረጅም ጊዜም ተወያይተው ነው የወሰኑት ይላሉ።
ጥናቱን ማስፈጸም የሚችልም ብሔራዊ ኮሚቴ ከመከላከያ፣ ከፌደራል ፖሊስና ከብሔራዊ ደኅነነት፣ የህግ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞችን ባወቀረ መልኩ ሆኖ ስለመቋቋሙም ተናግረዋል።
የዚህ ኮሚቴ ዋነኛ አላማም አፈጻጸሙ ላይ ጉድለት እንዳይኖረው ለማድረግ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
“ብሄርን የማያይ፣ ዘርን የማይመርጥ ኢትዮጵያዊ የሆነ የጸጥታ መዋቅር መገንባቱ ከማንም በላይ ደህንነቱን የሚጠብቅለት ኃይል መኖሩ ከማንም በላይ ህዝቡ ይፈልገዋል” ብለዋል።
አፈጻጸሙ ላይ ጥናት ቀርቦበት፣ መንግሥት ወስኖ፣ ኮሚቴ ተቋቁሞ “እኩል በጋራ ነው እየተፈጸመ ያለው” ብለዋል።
መንግሥት የተለያዩ ክልል ኃይሎች መዋቅር ለውጥ ተደርጎ ወደ መከላከያ ሠራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ እና ወደ ክልል ፖሊስ እንደሚካተቱ ቢገለጽም አብን በበኩሉ “ከአማራ ክልል ውጭ ልዩ ኃይሉን ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ የተጀመረበት ክልል የለም” ይላሉ።
ጄነራሉ በዚህ አይስማሙም “አንደኛውን ክልል አሳብጠን አንደኛው ኃይል እንዳይኖረው የምናደርግበት አካሄድ የለም” ብለዋል።
“በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም እኩል ባደረገ መልኩ ወደሚፈለገው መስመር ይገባሉ “ ሲሉም አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል።
“ክልሎች ሊይዙት የሚችሉት የጸጥታ ኃይል አንድ ብቻ ነው እሱም መደበኛ ፖሊስ ነው።ክልሎች ከዚህ ውጭ አይኖራቸውም፣ አይፈቀድላቸው፣ ህጉም አይፈቅድም” ሲሉም ተደምጠዋል።
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ውጥረት መንገሱን አስመልክቶ የተናገሩት ጄነራሉ በአንዳንድ አማራ አካባቢዎችና ክፍሎች ካልሆነም አብዛኛው የአማራ ልዩ ኃይል ይህንኑ ውሳኔ መቀበሉን ነው የተናገሩት።
ጄነራሉ በአጠቃላይ የአገሪቱ የጸጥታ ብሔራዊ ኃይል የማሻሻያ ስራውን ከጀመረ፣ ሶስት አራት አመት እንደሆነ ጠቅሰው ማሻሻያው የአገሪቷን የግዛት አንድነት፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የአገሪቷን የህዝቦች ደህንነት መነሻ አድርጎ እንዲጠብቀና እንዲከላከልም ያለመ ነው ብለዋል።
ይህንን ኃይል ለማደረጀት መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ብሄራዊ ደህንነትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችንም መሻሻልም እንደተሰራ አብራርተዋል።
በዚህም ማሻሻያ ኢትዮጵያዊነትን ያማከለ ወይም ሁሉንም በእኩል መልኩ የሚያይ የጸጥታ ግብረ ኃይል፣ ለኢትጵያዊነት ጠቅላይ ግዛት የሚመች ችሎታን ማዳበር እንዲሁም በቴክኖሎጂና በትጥቅ የዘመነ፣ አሰራሩም በዘመነ ሁኔታ ላይ አተኩሮም ማሻሻያው እየተሰራ እንደሆነም ነው የተናገሩት።












