ልዩ ኃይልን መልሶ ከማዋቀር ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል አካባቢዎች የተከሰተው ውጥረት

የአማራ ልዩ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በክልል፣ በፌደራል የፀጥታ መዋቅሮች እና በመከላከያ ውስጥ የማካተት ሥራ መንግሥት መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ ይህንን በተቃወሙ አካባቢዎች ውጥረት ነግሷል ተባለ።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ትጥቅ አይፈታም በሚል የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ሹምዬ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ መልካሙ ሹምዬ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ሲሉ የጠሯቸው ተቃውሞዎች በምዕራብ ጎንደር፣ በመተማ ዮሐንስ፣ በወልዲያ እና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ተደርገዋል ብለዋል።

ሐሙስ መጋቢት 28/2015 ዓ.ም. የፌደራል መከላከያ ሠራዊት ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን እና በአንዳንዶችም አካባቢዎች ግጭት ስለመፈጠሩም መረጃዎች እንደደረሳቸው አቶ መልካሙ ተናግረዋል።

በጎብዬ፣ ቆቦ፣ ከጎንደር ወደ ባህር ዳር የሚወስደው መንገድም የመዝጋት እንቅስቃሴዎች እንደነበሩና በመከላከያ እና በልዩ ኃይሉ መካከል ውጥረት እንደነበረም ጨምረዋል።

ቢቢሲ አርብ ከሰዓት በኋላ በወልዲያ፣ በደጀን እና መተማ ካሉ ነዋሪዎች እንደረሰማው ረፋድ ላይ በተወሰነ ደረጃ ተቃውሞ እና መንገድ የመዝጋት እንቅስቃሴ እንደነበር ገልጸዋል።

አቶ መልካሙም “ቀዝቀዝ እና ጋብ ቢልም” በአርብ ዕለትም ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች የተደረገው ተቃውሞ እንዲሁም የተነሱ ጥያቄዎች ዝርዝርን በተመለከተ በየአካባቢው ያለው መዋቅራቸው መረጃ እየሰበሰ እንደሆነ እና ይህንንም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ከአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን እና የፀጥታ ቢሮ በክልሉ ስላለው ሁኔታ ተጨማሪ መረጃ በስልክ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ ምላሽ ባለማግኘቱ አልተሳካም።

መንግሥት በበኩሉ ልዩ ኃይሎቹን ትጥቅ ማስፈታት ሳይሆን ጠንካራና የተማከለ አገራዊ ሠራዊት ለመገንባት በተያዘው ዕቅድ መሠረት “የክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን” አመልክቷል።

“የሚበተን ኃይል የለም”

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በተለያዩ የፌደራል እና የክልል የፀጥታ መዋቅሮች ውስጥ በመካተት ይደራጃል የሚለው መረጃ መሰማቱን ተከትሎ፣ እርምጃው የክልሉን ልዩ ኃይል ትጥቅ ለማስፈታት ነው በሚል ተቃውሞ እና ውጥረት ተከስቷል።

የፌደራል መንግሥቱ የኮምዩኑኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ግን መልሶ ማዋቀሩ ሁሉንም ክልሎች የሚመለከት እና ከትጥቅ ማስፈታት ጋር የሚያያዝ አለመሆኑን ገልፏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ “የመልሶ ማደራጀት ሥራውን እና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት ታይተዋል” በማለት የተሰማውን ተቃውሞ ውድቅ አድርጎታል።

የአማራ ክልልም አርብ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ተግባር በሁሉም ክልሎች የሚከናወን መሆኑን በመጥቀስ፣ “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው” ብሏል።

ስለሆነም የክልሉ የልዩ ኃይል አባላት እና ሕዝብ “የመልሶ ማደራጀቱ ሥራ የሚከውነው የልዩ ኃይላችንን የሰው ኃይል ለበለጠ ፋይዳ ላለው ተልዕኮ መልሶ የማደራጀት እና ብቁ የማድረግ አገራዊ እና ክልላዊ ፋይዳ ለማዘጋጀት ነው” በማለት በመልሶ ማደራጀቱ ሂደት “የሚበተን ኃይል የለም” ሲል አስረድቷል።

“ልዩ ኃይሉ እየተንቀሳቀሰ ነው”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ ጋር በተያያዘም ልዩ ኃይሉ በተሰማራባቸው አንዳንድ ካምፖች ፀጥታ የማስከበሩን ኃላፊነት እንዳይወጣ የማደናቀፍ ሥራዎችም አሉ የሚሉት አቶ መልካሙ፣ በቂ ምግብ እየደረሳቸው ባለመሆኑም ወደተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

ልዩ ኃይሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የሚጠቅሱት አቶ መልካሙ፣ ከየትኞቹ አካባቢዎች ነው ልዩ ኃይሉ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚለውን ግን “ከደኅንነት አንጻር ለመግለጽ እንደሚቸገሩ” ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች የሚቀርበው ምግብ መቋረጥ ከመቼ ጀምሮ እንደተፈጠረ መረጃ እንደሌላቸው ቢገልጹም፣ አርብ ዕለት ግን በተለያዩ አካባቢዎች እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ጨምረው ጠቅሰዋል።

አቶ መልካሙ የልዩ ኃይሉ አባላት ምናልባት ምላሽ ወደሚሰጣቸው አካል ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ቢያስቀምጡም፣ መዳረሻቸውን በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በኮረም እና በአላማጣ የነበሩ ልዩ ኃይሎች ከየአካባቢዎቹ ወጥተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የየአላማጣ ከንቲባ ኃይሌ አበራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ልዩ ኃይሎቹ ወደየት እየሄዱ እንደሆነ እንደማያውቁ የገለጹት ከንቲባው፣ ከኮረም አካባቢ የመጡትንም ልዩ ኃይሎችም ሕዝብ እያስተናገደ እና እየሸኘ ነው ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ተከሰተ እንደተባለው በልዩ ኃይሉ እና በመከላከያ መካከል ፍጥጫ ባይኖርም፣ አርብ መጋቢት 29/2015 ዓ.ም. የራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ታጣቂ ናቸው ያሏቸው 52 አባላት በመከላከያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ ኃይሌ ገልጸዋል።

ፓርቲው ውጊያው ለመክፈት ሞክሮ እንደነበር የሚገልጹት ከንቲባው የራያ አላማጣ ሕዝባዊ ሠራዊት ብለው የጠሩትም በዚሁ መሳተፉን እና መከላከያም የቡድኑን አባላት መያዙን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል መዋቅር መፍረስ ያስነሳው ጥያቄ

መንግሥት የተለያዩ ክልል ኃይሎች መዋቅር ለውጥ ተደርጎ ወደ መከላከያ ሠራዊት፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ እና ወደ ክልል ፖሊስ እንደሚካተቱ ቢገለጽም የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ መልካሙ አለኝ ባሉት መረጃ፣ “ከአማራ ክልል ውጭ ልዩ ኃይሉን ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ የተጀመረበት ክልል የለም” ይላሉ።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ግን ውሳኔው በሁሉም ክልል አመራሮች ጥናት ተደርጎበት፣ ያለልዩነት ስምምነት የተደረሰበት እንዲሁም ከልዩ ኃይል አመራሮች እና አባላት ጋር ከመግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

አቶ መልካሙ በበኩላቸው የፌደራሉም ሆነ የአማራ ክልል ከልዩ ኃይሉ ጋር ምንም ዓይነት ውይይት አላካሄዱም ይላሉ።

“ሕዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገለጸ እና ከፍተኛ ምሬት እና ብዥታ ባለበት ሁኔታ” እሱን የማጥራት ሥራ እንዳልተሰራም ነው አጽንኦት የሚሰጡት።

“በጥድፊያ፣ በግርግር ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረግ ጥረት ነው። ይኼ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው መቆም አለበት” ይላሉ።

በአማራ ክልል የልዩ ኃይሉ መዋቅር መፍረስ እንደሌለበት አጽንኦት የሚሰጡት አቶ መልካሙ ሌላኛው የሚያነሱት ጉዳይ ክልሉ ከውጭም ከውስጥም የፀጥታ ችግሮች የተጋረጡበት ስለመሆኑ ነው።

በክልሉ ከትግራይ ኃይሎች ጋር በተካሄደው ጦርነት በርካታ ንጹሃን ያለቁበት እንዲሁም በርካታ ንብረቶች የወደሙበት መሆኑንም ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ኃይል የሚሏቸው የሱዳን እና ሌሎች ኃይሎች በተደጋጋሚ ትንኮሳ ይፈጽማሉ ብለዋል።

በአማራ ክልል አንጻራዊ ሰላም እንዲኖረው ያስቻለው የልዩ ኃይሉ ተግባሩን በአግባቡ መፈጸሙ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በአካባቢው ክልሉን የሚፈትኑ ኃይሎች ከልዩ ኃይሉ አቅም በላይ አይደለም ይላሉ።

ሌላኛው በዋቢነት የሚጠቅሱት አጣዬ አካባቢ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን ነው። በከተማዋ በርካታ ንጹሃን ላይ ግድያዎች መፈጸማቸው እንዲሁም ከተማ የሚወድምበትና የሚቃጠልበት ክልል እንደሆነም ይናገራሉ።

“ክልሉ ግልጽና ተጨባጭ የሆነ የፀጥታ ስጋት የነገሰበት እንደሆነ” የሚገልጹት አቶ መልካሙ ውሳኔው ወቅቱን ያልጠበቀና ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ።

ሌላኛው የሚያነሱት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ፖለቲካዊ ቀውሶችን ለመፍታት አገራዊ ምክክር የተጀመረ ሲሆን በዚህም ውይይት ከሚደረግባቸው አንዱ የአገረ መንግሥቱ መዋቅርን ጨምሮ የፀጥታ ኃይሎች አደረጃጀት እንደሆነ ተስፋ ያደርጋሉ።

መዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ ችግሮች ከተፈቱ በኋላ ነው የልዩ ኃይሉ ትጥቅ መፍታትም ሆነ መዋቀር መነሳት ያለበት ይላሉ።