በአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና በፌዴራል የፀጥታ ተቋማት መካከል ውጥረት ተፈጥሯል፡ አብን

ባሕር ዳር ከተማ
የምስሉ መግለጫ, ባሕር ዳር ከተማ

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች እና በአማራ ክልል ልዩ ኃይል መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ገለጸ።

ፓርቲው ሐሙስ መጋቢት 28/2015 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው አለመግባባት እና ውጥረቱ የተከሰተው የክልሉን ልዩ ኃይል “በግዴታ ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ በመደረጉ” እንደሆነ አመልክቷል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሐሙስ ምሽት ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ በሁሉም ክልሎች ያሉ ልዩ ኃይሎችን በተለያየ መልኩ የማዋቀር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ “የመልሶ ማደራጀት ሥራውን እና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት ታይተዋል” ብለዋል።

ነገር ግን ሚኒስትሩ “ሂደቱን የሚያውኩ” ያሏቸው ተግባራት ምን እንደሆኑ እና ምን እንደተከሰተ በዝርዝር ያመለከቱት ነገር የለም።

ባለፈው ሳምንት የፌደራል መንግሥቱ፣ የአገሪቱ ክልሎች ያሏቸው ልዩ ኃይሎች እና አደረጃጀታቸው በሕግ ከተደነገገው ውጪ በመሆኑ ወደ አገር መከላከያ ሠራዊት፣ ወደ ፖሊስ እና ወደ ተለያዩ የፀጥታ ዘርፎች እንደሚካተቱ መግለጹ ይታወሳል።

ይህ ሃሳብም ከተለያዩ ወገኖች ድጋፍ እና ተቃውሞ የቀረበበት ሲሆን፣ አብን ውሳኔውን ወቅቱን ከግንዛቤ ያላስገባ እና አስፈላጊው ውይይት ያልተደረገበት ነው ሲል የተቃውሞ መግለጫ አውጥቶ ነበር።

ቢቢሲ ከአንዳንድ የአማራ አካበቢዎች ባገኘው መረጃ መሠረት በዛሬው ዕለት ከወትሮው የተለየ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ እንቅስቃሴ እንደነበረ የተረዳ ሲሆን፣ በተጨባጭ ያለውን ሁኔታ ከሚመለከታቸው የክልሉ የፀጥታ ተቋማት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ የስልክ ጥሪዎቹ ምላሽ ባለማግኘታቸው አልተሳካም።

ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር ወደ ጎንደር ከተማ የሚወስደው መንገድ ለተወሰነ ሰዓት ተዘግቶ እንደነበር ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም በአካባቢው መታየታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንዲሁም ሰሜን ወሎ ውስጥ በምትገኘው ቆቦ ውስጥም ለአጭር ጊዜ የቆየ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን እና ጠዋት ላይ በነዋሪው ዘንድ ድንጋጤ እና ስጋት ተፈጥሮ እንደነበረ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ነገር ግን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ነዋሪዎች ለመንገድ መዘጋቱም ሆነ ለአጭር ጊዜ ለተሰማው ተኩስ “በይሆናል ከሚባለው ውጭ” ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳላወቁ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ይህንን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ግን የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን “በግዴታ ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባቱ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ኃይሉ እና በፌዴራል የፀጥታ ተቋማት መካከል ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩን” ገልጿል።

ፓርቲው በተለያዩ ቦታዎች በክልሉ ልዩ ኃይል እና በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች መካከል አሳሳቢ ውጥረት መከሰቱን ከመግለጽ ውጪ በየትኞቹ አካባቢዎች ችግር እንዳለ የጠቀሰው ነገር የለም።

አብን ጨምሮም የክልሉን ልዩ ኃይል “ያለ በቂ ዝግጅት እና ውይይት፣ የጋራ መግባባት እና መተማመን ሳይደረስ በድንገት እና ያለበቂ የፀጥታ ዋስትና ለማፍረስ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ኃላፊነት የጎደለው እና ዳፋው ከአማራ ክልል ባሻገር በአገሪቱ ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር ነው” ብሏል።

በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ተደራጅተው የሚገኙት ልዩ ኃይሎች አወቃቀር እና ትጥቅን በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ሲነሳበት እና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በተለያዩ ወገኖች ሃሳብ ሲሰነዘር ቆይቷል።

በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ልይ ኃይሎች ከፖሊስ እና ከአካባቢ የፀጥታ ኃይሎች በተለየ ሁኔታ ወታደራዊ ሥልጠና እና ትጥቅ ያላቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን ባለፉት ዓመታት አደራጅተዋል።

በቅርቡም በዚህ ዙሪያ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌደራሉ የመከላከያ እና የፀጥታ ተቋማት ውስጥ እንዲሁም ሌሎች አማራጮችን ውስጥ እንዲካተቱ በማቅረብ መልሰው እንዲደራጁ ሃሳብ መቅረቡ ይታወሳል።

ይህንን ሃሳብ ቀደም ብሎ የተቃወመው አብን አሁን የተከሰተውን ውጥረት ለማርገብ፣ ልዩ ኃይሉን በተመለከተ የተላለፈው ውሳኔ “በአፋጣኝ እንዲቀለብስ እና ከአማራ ክልል መንግሥት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እና ምክክር እንዲደረግ” ጥሪ አቅርቧል።

ከአማራ ልዩ ኃይል መፍረስ ጋር በተያያዘ መግለጫ ያወጣው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ደግሞ “በመርኅ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ እንዳለበት እና በአገራዊ የመከላከያ ሠራዊት መጠናከር እንዳለበት” እንደሚያምን ገልጾ፣ ነገር ግን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር አሁን ተግባራዊ ማድረግ ግን ተቀባይነት የለውም ብሏል።

ጨምሮም የፌዴራል መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል “እንዲፈርስ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ እና መጠን ተፈፃሚ የማይሆን በመሆኑ” ውሳኔውን ባልደራስ አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጿል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት አስፈላጊው ውይይት እና መግባባት ላይ መደረሱን በመጥቀስ፣ ይህም የሁሉንም ክልሎች ልዩ ኃይሎች የሚመለከት መሆኑን አመልክቷል።