"የክልሎች ልዩ ኃይልን በተመለከተ ውይይት ያስፈልጋል" የሶማሌ ክልል ም/ፕሬዝደንት

ከ16 ወራት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ መንበረ ስልጣኑን ተረክበው ሃገሪቱን መምራት ሲጀምሩ፤ ለአስተዳደራቸው ከፍተኛ ፈተና ይሆናል ተብሎ ተገምቶ የነበረው የሶማሌ ክልል ሁኔታ ነበር።
ይሁን እንጂ የሶማሌ ክልል እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ ምናልባትም ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል በተሻለ መልኩ አንጻራዊ ሰላም የሚታይበት ክልል ሆኗል በማለት የሚመሰክሩ በርካቶች ናቸው።
የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ ሙሐመድ በክልሉ ለተመዘገበው አዎንታዊ ውጤት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል። እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ በርካቶች ክልሉ ወደ መረጋጋት በቀላሉ አይመለስም ብለው እንዲያስቡ ያደረጓቸው ሦስት ነጥቦች አሉ ይላሉ።
የመጀመሪያው "አቅሙ ይብዛም ይነስ በክልሉ የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ኃይል ነበር። ሁለተኛው ደግሞ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል አጎራባቸው ቀበሌዎች የተከሰቱት ግጭቶች ሲሆኑ ሦስተኛው ደግሞ ሐምሌ 8 በጅግጅጋ ትውልደ ሶማሌ ያልሆኑ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ከግምት በማስገባት ነው" ይላሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በሃገር አቀር አቀፍ ደረጃ እንደታየው፤ በርካታ ታጥቀው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደ ሃገር ተመልሰዋል። ታጥቆ የፖለቲካ ትግል ሲያደርግ የነበረው ኃይልም ወደ ክልላችን በሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰኑ ለክልላችን ሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል ይላሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ።
"በኦሮሚያ እና ሶማሌ ደንበር አቅራቢያ ችግሮችን ይፈጥር የነበረው አመራሩ ነበር። አመራሩ ከተቀየረ በኋላ ህዝቡ በሰላም መኖር ጀመረ። ከዚያ ችግሩ ተቀርፏል።"
ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በጅግጅጋ ተከስቶ የነበረው ሁከት አሁን ተረጋግቶ ህዝቡ የተመለደውን ህይወት እየመራ እንደሆነ እና ክልሉ ላስመዘገበው ውጤት ይህ ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ ይናገራሉ።
የድንበር ይገባኛል ግጭቶች
ባለፉት ሦስት ዓመታት በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች አዋሳን ስፍራዎች ላይ ለሚከሰቱ ግጭቶች እንደምክንያት ተደርገው ሲቀርቡ ከነበሩት መካከል የግጦሽ መሬት እና የድንበር ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው።
ከድንበር ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አስተዳደራቸው ምን እየሰራ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ ሲመልሱ "በመጀመሪያ ደረጃ ባለፉት ዓመታት ለተከሰቱት ግጭቶች ምክንያቱ የግጦሽ መሬት ወይም የድንበር ጉዳዮች አልነበሩም። የመንግሥት መዋቅር ያለበት አሻጥር ነው ህዝቡን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተው እና ያፈናቀለው።"
ምክትል ፕሬዝድንት ሙሰጠፌ እንደሚሉት ከሆነ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ድንበር ላይ ለተከሰተው ግጭት የድንበር ወሰን ማበጀት መፍትሄ አይሆንም።
"የህዝቡ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው በማካለል [ድንበር] አይደልም። ህዝቡ አብሮ እንዲኖር የአመለካከት ለውጥ በማምጣት እና ሁሉንም ከልማት ተጠቃሚ በማድረግ ነው።"
ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ እንደሚሉት አሁን ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ የድንበር ማካለል ሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን እና ወደፊት መንግሥት በሚያስቀምጠው መርሃ ግብር ሊከናወን እንደሚችል ጠቁመዋል።
የሞያሌ ከተማ እጣ-ፈንታ
ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር የምታዋስነው የሞያሌ ከተማ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄድባታል። የኬንያ እና የኢትዮጵያን መንግሥትን ጨምሮ በብዙ ሃገራት የተያዘው የላሙ ወደብ ፕሮጀክት ሞያሌን የደረቅ ወደብ መናኸሪያ ያደርጋታል ተብሎም ይጠበቃል።
ሞያሌ በርካታ የኦሮሞ እና የሶማሌ ተወላጆች በስፋት ይኖሩባታል። ታዲያ ይህች የንግድ ከተማ ትገባኛለች በሚል በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደጋጋሚ ግጭቶች ተከስተዋል ጉዳትም ደርሷል።
ለዚህ ችግር መፍትሄ ለማበጀት የፌደራል እና የሁለቱ ክልል መንግሥታት ምን እየሰሩ ነው? ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ ሲመልሱ፤ "ቅድሚያ የምንሰጠው ለሰላም ነው። ስላም ለማስፈን እየሰራን ነው። በአሁኑ ወቅት ግጭቶች የሉም። በሞያሌ ከተማ ዙሪያ ከአከባቢው ነዋሪዎች፣ ኦሮሚያ እና ከፌደራል መንግሥት ጋር በመወያየት መፍትሄ እንሰጣለን እንጂ፤ አሁን ላይ መፍትሄው ይህ ነው ብዬ ለመናገር ይከብደኛል" ብለዋል።
ፍትህ እና ነጻነት
ከአንድ ዓመት በፊት በጅግጅጋ የሶማሌ ተወላጅ ባልሆኑ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ነበር። በወቅቱ መንግሥት ለጥቃቱ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን ኃይሎች ለፍርድ እንደሚያቀርብ የገለጸ ሲሆን፤ ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌም አስተዳደራቸው ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ተናግረዋል።
"የጥቃቱ ዋና አቀነባባሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ሌሎች ተሳታፊ የሆኑት ደግሞ አሁንም ድረስ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፤ ተይዘው እየቀረቡ ነው። በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውንም በተቻለን አቅም እየደገፍን ነው።"
ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ፤ "ዋናው ትኩረታችን መሰል ጥቃቶች በክልላችን ዳግም እንዳይከሰቱ ማደረግ ነው። ባለፈው አንድ ዓመት ምንም አይነት ችግር አልገጠማቸውም። ማንም ሰው የየትኛውም እምነት ተከታይ ሆኖ መኖር ይችላል። ለዚህም የክልሉ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወስዳል" ሲሉ ተናግረዋል።
ይህን የፕሬዝዳንቱን ቃል የበለጠ የሚያጠናክረው ደግሞ ባለፈው ዓመት በተፈጸመ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናትን ጥገና ለማድረግ የክልሉ አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በይፋ የሰጠችው እውቅና የሚጠቀስ ነው።
የሙሰጠፌ አስተዳደር ፈተናዎች
ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ ትልቁ የአስተዳደራቸው ፈተና ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሥራ አጥ ወጣት ሥራ መስጠት መሆኑን ይናገራሉ። ሥራ አጥ የሆነው ወጣት ቁጥር በጨመረ መጠን የክልሉ ሰላም የመደፍረስ እና የልማት እንቅስቃሴዎች የመስተጓጎል አጋጣሚዎች ከፍ እንደሚሉ ያስረዳሉ።
"ሥራ አጥ የሆነን ወጣት የትኛውም ኃይል ሊጠቀምበት ይችላል" የሚሉት ምክት ፕሬዝደንቱ ለወጣቶች ሥራ የሚያስገኙ የልማት ሥራዎች ላይትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ይናገራሉ።
ልዩ ፖሊስ
በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በተደጋጋሚ የመብት ጥሰት እንደሚፈጽም ክስ ይቀርብበት የነበረው የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ፤ የአደረጃጀት ለውጦች እንደተካሄዱበት ምክትል ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል።
ጥፋተኛ የተባሉት ከልዩ ኃይሉ እንዲገለሉ ከተደረገ በኋላ በሰብዓዊ መብት አያያዝ እና የሕገ መንግሥት ስልጠናዎች እንዲወስዱ እንደተደረጉ ምክትል ፕሬዝደንቱ ተናግርዋል። "ከፍተኛ መሻሻል እንዳለ ህዝቡ ይመሰክራል። ልዩ ኃይል አሁን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይፈጽምም" ብለዋል።
በክልሎች ደረጃ የልዩ ኃይል አስፈላጊነትን የተጠየቁት ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ፤ "አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ልዩ ኃይል የሚያከናውናቸው ቀልጣፋ ሥራዎች አሉ። ልዩ ኃይል በእኛ ክልል ይቀጥላል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው ያለው" ያሉ ሲሆን "ወደፊት የክልል ልዩ ኃይሎች ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር ስለሚኖራቸው ቁርኝት ወይይቶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ" ብለዋል።
ኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በቅርቡ የትጥቅ ትግሉን አቁሞ ወደ ሃገር መመለሱ ይታወሳል። ምክትል ፕሬዝደንት ሙሰጠፌ እንደሚሉት ታጥቆ ልዩ ኃይልን የተቀላቀለ የኦብነግ ኃይል የለም። "የኦብነግ ታጣቂዎች አስፈላጊው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ነው የተደረጉት" ብለዋል።












