ተጨማሪ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን ማደራጀት ለምን አስፈለገ?

የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ምሩቃን

የፎቶው ባለመብት, OBN

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለስድስት ወራት በውትድርና ሳይንስ ያስለጠናቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ኃይል ፖሊሶች አስመርቋል።

የልዩ ኃይል አባላቱን በአዋሽ ቢሾሌ በመገኘት ያስመረቁት የክልሉ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሲሆኑ፤ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ "የልዩ ኃይሉ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ የተገኘውን ድል ማስቀጠል ነው" ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ በተጨማሪም የልዩ ኃይሉ ተልዕኮ የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ከማስጠበቅ በተጨማሪ የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም እና መብት ማረጋገጥ የተጣለበት ሃላፊነት ነው ብለዋል።

አንዳንድ ወገኖች ክልሎች የራሳቸውን ልዩ ኃይል ማደራጀት የለባቸውም ሲሉ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት የደህንነት አማካሪ የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ በበኩላቸው፤ ፌደራላዊ ስርዓትን እየተከተለች ባለች አገር ክልሎች የራሳቸውን ኃይል ማደራጀት የተለመደ ከመሆኑም ባሻገር ሕጋዊ መሠረት አለው ይላሉ።

የኢፌዲሪ ሕግ-መንግሥት አንቀስ 52 ሥር ክልሎች የራሳቸውን የፖሊስ ኃይል ያደራጃሉ፣ ይመራሉ፣ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃሉ ብለዋል ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

ክልሎች የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነት እና የዳኝነት ሥልጣን እንዳላቸው በመጥቀስ፤ ክልላቸው ደህንነቱን ለማስጠበቅ ልዩ ኃይሉን ማቋቋም እንዳስፈለገው ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ ተናግረዋል።

የደህንነት አማካሪው እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት ለሌላው ክልል 'ስጋት ነበር' ይላሉ።

"ከዚህ ቀደም ልዩ ኃይል የሚደራጀው የራሱን ክልል ደህንነት ለማስጠበቅ ሳይሆን የሌላን ክልል ሰላም ለማወክ ነበር። ይህ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው" ብለዋል።

የአንድ ክልል ልዩ ኃይል ሲመሰረት ዓላማው የራሱን ክልል ሰላም ማስጠበቅ እና የሕግ የበላይነትን ማስከበር መሆን ነው ያለበት እንጂ ሌላ ተልዕኮ ይዞ መሆን የለበትም ብለዋል።

የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ምሩቃን

የፎቶው ባለመብት, FBC

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፤ የክልሉ ልዩ ኃይልም የተመሰረተው ለዚሁ ዓላም መሆኑን ያስረዳሉ።

የክልሉን የቆዳ ስፋት እና ህዝብ ቁጥር እንዲሁም ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ ተጨማሪ ልዩ ኃይል ማደራጀት እንዳስፈለገ ተናግረዋል።

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፤ ይህ ልዩ ኃይል በወጣቶች የተደራጀ እንደሆነ ይናገራሉ። "90 በመቶ የሚሆኑት የልዩ ኃይል አባላቱ ወጣቶች ናቸው" ብለዋል።

በክልሉ የሰላም መደፍረስ በሚያጋጥምበት ወቅት የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልግ ክልሉ በራሱ ኃይል የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚያስችለው ጨምረው ተግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት ሙስጠፌ ሞሐመድ፤ በክልሎች ደረጃ የልዩ ኃይል አስፈላጊነትን ተጠይቀው "አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ልዩ ኃይል የሚያከናውናቸው ቀልጣፋ ሥራዎች አሉ። ልዩ ኃይል በእኛ ክልል ይቀጥላል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው ያለው" ማለታቸው ይታወሳል።

ከዚህ በፊት አምነስቲ ኢንትርናሽናል በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅሟል ያለውን የልዩ ፖሊስ ኃይል የኢትዮጵያ መንግሥት ጠይቆ ነበር።