በደብረ ብርሃን መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ኃይሎች መጋጨታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከአማራ ኃይሎች ጋር መጋጨቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ነዋሪዎች ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 03/2015 ዓ.ም. ከንጋት ጀምሮ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ከፋኖ ጋር በመሆን ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር መጋጨታቸውን እና በዚህም ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ገልጸዋል።
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ከተማዋ በግጭቱ ሳቢያ ተረብሻ ውላለች።
መንግሥት መልሶ ለማዋቀር ዕቅድ እንዳለው ካሳወቀ በኋላ ከአዲስ አበባ በ115 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረ ብርሃን ውስጥ በተከሰተው ግጭት ሁለት ሰዎች መሞታቸውን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፌደራሉ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በመበተን አባላቱን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅር የማስገባት ዕቅድ እንዳለው ይፋ ካደረገ በኋላ በተለይ በአማራ ክልል አመጽ የተቀላቀለበት ከፍተኛ የተቃውሞ ድምጽ እየተሰማ ይገኛል።
ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልዲያ እና ቆቦ የተቃውሞ ሰልፎች ከተደረጉባቸው ከተሞች መካከል ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ በቆቦ እሁድ ሚያዚያ 01/2015 ዓ.ም. በአማራ ኃይሎች እና በአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ግጭት ተከስቶ የሰዎች ሕይወት አልፏል።
ደብረ ብርሃንን ጨምሮ ጎንደር እና ደሴ ከተሞችም ከፀጥታ ኃይል አባላት ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን ጨምሮ ሌሎች ገደቦች መጣላቸውን የሦስቱ ከተሞች የፀጥታ ኮማንድ ፖስቶች ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
መንግሥት ለአገር አንድነት እና ለሕዝብ ሰላም ሲባል የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ሌላ መዋቅር ማስገባት ያስፈልጋል ቢልም በአጎራባች ትግራይ እና ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለአማራ ስጋት ስለሆኑ ልዩ ኃይል መበተን የለበትም የሚል መከራከሪያ ከአማራ ክልል በኩል በስፋት ይሰማል።
ግጭት እና የደረሰ ጉዳት
ዛሬ ማለዳ በደብረ ብርሃን ከ1 ሰዓት ጀምሮ የተኩስ ድምጽ መስማት መጀመራቸውን የሚናገሩት ነዋሪ፤ ከባድ የተኩስ ድምጽ እስከ እኩለ ቀን መቀጠሉን እና ከሰዓት በኋላ አልፎ አልፎ የመሳሪያ ድምጽ እንደሚሰማ ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የመከላከያ ሠራዊት ልብስ የለበሱ ከልዩ ኃይል እና ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ተኩስ ገጥመው ነበር። በአዲስ አበባ መግቢያ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አካባቢ ነው የተኩስ ልውውጥ የነበረው። ተኩስ አሁንም አልፎ አልፎ ይሰማል” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ እማኝነታቸውን ለቢቢሲ የሰጡት ሌላ ነዋሪ ደግሞ፣ በተኩስ ልውውጡ በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና አንዲት ሴት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባት ተናግረዋል።
ነዋሪው “ቻይና ካምፕ በሚባለው አካባቢ ነው ሰዎቹ የተገደሉበት። ከምሥራቅ ወለጋ የመጡ ተፈናቃዮች ናቸው። የሞቱን መቅበር አልቻልንም። የተጎዳችውን ህክምና መውሰድ አልቻልንም። በየት በኩል ብለን እንሂድ? መንገድ የለም። አስክሬን ታቅፈን ተቀምጠናል” በማለት ያሉበትን ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ከምዕራብ ኦሮሚያ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ እና ከሌሎችም አካባቢዎች የተፈናቀሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠልለው ይገኛሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላኛው ነዋሪው ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ በመከላከያ እና በአማራ ኃይሎች መካከል በነበረው ግጭት የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር ባይኖርም፣ ሰኞ ሚያዝያ 2 በነበረ ተቃውሞ ግን ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል።
ነዋሪው ሲናገሩ ትናንት ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች እሁድ ዕለት ከነበረው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎችን ከእስር እናስለቅቃለን በማለት ፖሊስ ጣቢያ ሰብረው ከገቡ በኋላ ፖሊስ በተኮሰው ጥይት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን በተጨባጭ አውቃለሁ ብለዋል።
“ከእስር ቤት ያመለጡ እስረኞች ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም፣ ነገር ግን ጠባሴ አካባቢ ካለው እስር ቤት ሰዎች አስለቅቀናል ሲሉ ሰምቻለሁ። ጠባሴ ካለው እስር ቤት 05 ወደ ሚባለው ፖሊስ ጣቢያ ከሄዱ በኋላ ነው ጉዳት የደረሰው። ከሞቱት መካከል አንዱ ሰልፈኛ ነው። ሌላኛዋ ሟች መንገደኛ ሴት ናት” ብሏል ነዋሪው፥
የደብረ ብርሃን ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ
ከአዲስ አበባ ሰሜን ምሥራቅ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደብረ ብርሃን ባለፉት ጥቂት ቀናት ውጥረት ውስጥ ቆይታለች።
ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ በመነሳት ወደ ኮምቦልቻ ደሴ እና ወደ ሌሎችም የምሥራቅ አማራ ክፍሎች ዋነኛ የመተላለፊያ መስመር ናት።
“በከተማዋ የተቃውሞ ድምጽ መሰማት ከጀመረ ሦስት ቀን ሆኖታል። የንግድ ተቋማት እየሰሩ አይደለም። ትራንስፖርት የለም። መንገድ ዝግ ነው። ሁሉም አይነት አገልግሎት ከተቋረጠ ሦስተኛ ቀኑ ነው” ሲሉ አንድ ነዋሪ በደብረ ብርሃን ስላለው ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የተከሰተውን ውጥርት እና ግጭት በእርቅ ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ጨምረው ተናግረዋል።
በደብረ ብርሃን ስለተከሰተው ግጭት እና ስለደረሰው ጉዳት ከዞኑ፣ ከተማዋ እና ከአማራ ክልል ባለሥልጣናት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።












