በቆቦ ከተማ በአማራ ኃይሎች እና በመከላከያ መካከል ግጭት ተፈጥሮ እንደነበረ ተገለጸ

በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ በአማራ ኃይሎች እና በአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ትናንት እሁድ ሚያዚያ 01/2015 ዓ.ም. ግጭት ተከስቶ እንደነበረ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ፋኖ እና የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በአንድ ወገን ሆነው ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል ቢሉም፣ ሌላኛው ነዋሪ ግን ግጭት የነበረው በፋኖ እና በመከላከያ መካከል ብቻ ነው በማለት የልዩ ኃይል አባላት በግጭቱ ተሳታፊ እንደልነበሩ ተናግረዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ያናገራቸው በቆቦ ከተማ የሚገኙ ሁለት ነዋሪዎች ከከተማዋ ውጪ የመድፍ ተኩስ መስማታቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ ተኩስ ከየትኛው ወገን እንደሆነ አለማወቃቸውን ዘግቧል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ በራያ ቆቦ ከተማ እና በዙሪያዋ “በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ተኩስ” ሲደረግ እንደነበር ገልጿል።
ይህ በአማራ ኃይሎች እና በአገር መከላከያ ሠራዊት መካከል ግጭት የተሰማው የፌደራሉ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በመበተን አባላቱን ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅር የማስገባት ዕቅድ እንዳለው ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በተለይ በአማራ ክልል ከፍተኛ ተቃውሞ ከተሰማ በኋላ ነው።
ውሳኔውን የሚቃወሙ የአማራ ክልል በአጎራባች ትግራይ እና ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለአማራ ስጋት ስለሆኑ ልዩ ኃይል መበተን የለበትም በማለት ይከራከራሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ “ለኢትዮጵያ አንድነት” እና “ለሕዝብ ሰላም” ሲባል አስተዳደራቸው የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌላ መዋቅር ማስገባት አስፈልጎታል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ይህ እቅድ በአማራ ክልል ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሳበት ሲሆን ትናንት ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ እና ደብረ ብርሃን ጨምሮ በሌሎች የክልሉ ስፍራዎች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱም የቆቦ ነዋሪዎች ትናንት እሁድ ረፋድ 3 ሰዓት አካባቢ የጀመረው የተኩስ ድምጽ አንዴ ጋብ እያለ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀጥሎ እየተካሄደ ቀኑን ሙሉ የተኩስ ልውውጡ መካሄዱን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ወደ ወልዲያ መውጫ ኖክ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሲካሄድ በነበረው የተኩስ ልውውጥ የከባድ ጦር መሳሪያ ድምጽ ጭምር ይሰማ ነበር ብለዋል።
“የመድፍ ድምጽ ይሰማ ነበር። ዛሬ ጠዋትም [ሰኞ] የከባድ ጦር መሳሪያ ድምጽ ይሰማ ነበር። አሁን ግን ጋብ ብሏል” ሲሉ ተናግረዋል።
የቆቦው ግጭቱ እንዴት ጀመረ?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ ግጭት መከሰቱን እንጂ ቀድሞ ተኩስ ከየትኛው ወገን እንደከፈተ አላወቁም። ሌላኛው ነዋሪ ግን ግጭቱ የተጀመረው የፋኖ አባላት በአገር መከላከያ ወታደራዊ ተሸከርካሪ ላይ ተኩስ ከከፈቱ በኋላ ነው ብለዋል።
“አኩርፈው ተቀምጠው የነበሩት ፋኖዎች መከላከያ ወዳለበት ሄደው ኦራል መኪናውን ሲያገኙ ተኮስ ጀመሩ ከዚያ በኋላ እነሱም አጸፋውን መለሱ” በማለት የተኩስ ልውውጡ መባባሱን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልፈዋል።
የእሁድ እለቱን ግጭት ማን እንደጀመረው አላውቅም ያሉት ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ ወደ ሌላ የፀጥታ መዋቅር አንገባም በማለት አፈንግጠው የወጡ የልዩ ኃይል አባላት ከፋኖ ጋር በአንድ ጎራ ሆነው ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር መጋጨታቸውን ይናገራሉ።
ሁለተኛው ነዋሪ ግን በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩት ፋኖዎች እንጂ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት አይደሉም ይላሉ። “ልዩ ኃይል አልገጠመም። ልዩ ኃይል ከተማ ውስጥ ባለ በካምፑ ውስጥ ቁጭ ብሎ ነበር አሁንም እዚያው ነው ያለው። ፋኖዎች ናቸው መከላከያን የገጠሙት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የደረሰ ጉዳት
ሁለቱም ነዋሪዎች በግጭቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ በትክክል መናገር ባይችሉም፣ ሦስት የፋኖ አባላት ስለመገደላቸው ሰምተናል ብለዋል።
“ሦስት ፋኖ ተገድሏል። አንድ ፋኖ ተቀብሯል። የሁለቱ አስክሬን ግን ገና እስካሁን አልተነሳም እየተባለ ነው። በመከላከያ በኩል ስለደረሰው ጉዳት ግን የማውቀው ነገር የለም” በማለት በዚያ በኩል የደርሰውን ጉዳት ማወቅ ከባድ ነው ብለዋል።
ሌላኛው ነዋሪ ለሰዓታት የተካሄደው ግጭት መቆሙን ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ ከግጭቱ በኋላ የፋኖ አባላት ከአካባቢ ሸሽተው ስለመውጣታቸው መስማታቸውን ተናግረዋል።
በቆቦ አካባቢ ስለተከሰተው ግጭት እና ስለደረሰው ጉዳት ከከተማዋ እና ከአማራ ክልል ባለሥልጣናት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ምላሽ አላገኘም።
ከእሁድ ዕለቱ ግጭት በኋላ ከተማዋ ውስጥ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ ቢሆንም ሰኞ ዕለት ያለው እንቅስቃሴ በጣም ቀዝቃዛ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
“ትናንት ከተማው ጦርነት ላይ ነው የዋለው። ሕዝቡ ከቤት አልወጣም ነበር። ዛሬም መንገዱ ባዶ ነው። ውስጥ ለውስጥ ግን ሰው መንቀሳቀስ ጀምሯል” ይላሉ ዛሬ ሰኞ በቆቦ ከተማ ስላለው ሁኔታ የተጠየቁት ነዋሪ።
ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ሌላ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ለማስገባት የመንግሥት ዕቅድ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ በቆቦ ተቃውሞዎች እንደነበሩ ይገልጻሉ።
“ተቃውሞ ከተጀመረ እና መንገድ ከተዘጋ ሦስት ቀን ሆኖታል” የሚሉት ነዋሪው ከትናንት በስተያ ቅዳሜ ዕለት ደግሞ በከተማዋ ሰልፍ ተካሂዶ እንደነበረ ያስታወሳሉ።
ዛሬ ሰኞ ንጋት አካባቢም መንገድ የተዘጋበትን ድንጋይ ነዋሪው እንዲያነሳ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መንገድ ላይ ያገኙትን በኃይል እያደረጉ ነው ብለዋል።
ነዋሪዎቹ ዛሬ ሰኞ ረፋድ ላይ የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች ትናንት ግጭት ውስጥ የገቡ ኃይሎችን ለማስታረቅ ጥረት ስለመጀመራቸው ጨምረው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሚካሄደውን ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማዋቀር ውሳኔውን በተመለከተ “በተፈጠረ የመረጃ ክፍተት በአንዳንድ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ፣ የአድማ ጥሪ እና የሰዎች እና የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴን የመገደብ አዝማሚያዎች እያታዩ ናቸው” ብለዋል።
ጨምረውም በአሁኑ ወቅት “አብዛኛው የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ውይይታቸውን አጠናቀው ውሳኔውን በካምፕ ውስጥ ሆነው እየተጠባበቁ ነው” በማለት፣ ከካምፕ የወጡ የልዩ ኃይሉ አባላትም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።












