ልዩ ኃይልን መልሶ የማዋቀር ውሳኔ በአማራ ክልል ከተሞች የቀሰቀሰው ተቃውሞ

በጎንደር ከተማ ለተቃውሞ የወጡ

የፎቶው ባለመብት, sm

የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ ለማዋቀር የተጀመረውን እርምጃ በመቃወም ቅዳሜ እና እሁድ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው ተዘገበ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለም በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ፣ የአድማ ጥሪ እና የመንገድ መዝጋት ተግባራት መታየታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚ ፓርቲ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የክልሉን ልዩ ኃይል በተለያዩ የመከላከያ እና የፀጥታ ተቋማት ውስጥ ለማካተት የተያዘውን ዕቅድ በጥድፊያ ተግባራዊ ለማድረግ እየተወሰደ ባለው እርምጃ፣ “በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ከፍተኛ ሕዝባዊ ቁጣን ቀስቅሷል” ብሏል።

የአገሪቱ ክልሎች ያሏቸው ልዩ ኃይሎችን በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌደራል ፖሊስ እና በክልል ፖሊስ ኃይሎች ውስጥ እንዲካተቱ የሚያደርግ ዕቅድ ይፋ ከተደረገ በኋላ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአማራ ክልል ውጥረት እና ተቃውሞ አጋጥሟል።

በተለይ በሳምንቱ ማብቂያ ቀናት በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ውስጥ ብዙ ሕዝብ የተሳተፈባቸው የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን እንዲሁም መንገዶች ተዘግተው የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ፎቶግራፎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ ታይተዋል።

“ተቃውሞ እና የእንቅስቃሴ መስተጓጎል”

ቢቢሲ ከተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ለማጣት እንደሞከረው የክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር የወትሮ እንቅስቃሴዋ ተገትቶ በተለይ እሁድ ዕለት ተቀዛቅዛ የነበረች ሲሆን፣ በትላልቆቹ የክልሉ ከተሞች በጎንደር እና በደብረ ማርቆስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ የወጡበት የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ቢያንስ በሁለት ከተሞች ውስጥ እሁድ ዕለት የፌደራል መንግሥቱን የክልሉን ልዩ ኃይል በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተቃውሞ መሰማታቸውን እና የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዶበታል በተባለው የጎንደር ከተማ አንድ ነዋሪ ለዜና ወኪሉ እንደተናገሩት፣ የመንግሥትን እርምጃ በመቃወም የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ቅዳሜ ሌሊቱን በሙሉ ወደ ሰማይ ሲተኩሱ ነበር ብለዋል።

መልሶ ማደራጀቱን ተከትሎ ከተፈጠረ ውጥረት ጋር በተያያዘ ተግባራዊ በሚደረገው ዕቅድ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳር ዶ/ር ይልቃል በሰጡት ማብራሪያ፣ የክልል ልዩ ኃይል አባላት በፈቃዳቸው ወደ መከላከያ ሠራዊት፣ ወደ ፌደራል እና የክልል የፖሊስ ኃይሎች ውስጥ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሉት በአሁኑ ወቅት “አብዛኛው የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ውይይታቸውን አጠናቀው ውሳኔውን በካምፕ ውስጥ ሆነው እየተጠባበቁ ነው” በማለት፣ ከካምፕ የወጡ የልዩ ኃይሉ አባላትም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ በምትገኘው የቆቦ ከተማ የሚገኙ ሁለት ነዋሪዎች ከከተማዋ ውጪ የመድፍ ተኩስ መስማታቸውን ለሮይተርስ ገልጸዋል። ነገር ግን ይህ ተኩስ ከየትኛው ወገን እንደተተኮሰ ግልጽ አለመሆኑ ተዘግቧል።

አብን በበኩሉ እሁድ ዕለት በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን እና በተለያዩ አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል ያለ ሲሆን፣ በተለይም በራያ ቆቦ ከተማ እና በዙሪያዋ “በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ተኩስ” ሲደረግ እንደነበር ገልጿል።

እሁድ ዕለት ቢያንስ በስድስት የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ መሆናቸውን ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቻውን ያልጠቀሱ ነዋሪዎች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በበርካታ አካባቢዎችም ተቃዋሚዎች በድንጋይ፣ በእንጨት እና በተለያዩ ነገሮች ዋና መንገዶችን በመዝጋታቸው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በመገታቱ በበርካታ የክልሉ ከተሞች ውስጥ የወትሮ እንቅስቃሴ ተገትቶ እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

“የመረጃ ክፍተት እና ፕሮፓጋንዳ”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፌደራልም ሆነ የክልሉ መንግሥት የተካሄዱትን የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንዳለ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሚካሄደውን ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማዋቀር ውሳኔውን በተመለከተ “በተፈጠረ የመረጃ ክፍተት በአንዳንድ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ፣ የአድማ ጥሪ እና የሰዎች እና የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴን የመገደብ አዝማሚያዎች እያታዩ ናቸው” ብለዋል።

ውሳኔውን በማስፈጸም በኩል በተፈጠረ ክፍተት እና “በተነዛው ፕሮፖጋንዳ” ችግሮች መከሰታቸውን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ይህም በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን እና “ቅሬታው የመነጨው በተሟላ መንገድ ለሕዝቡ መረጃ ባለመድረሱ” መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የልዩ ኃይል አባላቱን መልሶ ለማደራጀት በሚከናወነው ሥራ ዙሪያ “የሚነሳው ጥያቄ ትክክል ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ለአገር የሚጠቅም መሆኑን መገንዘብ ይገባል” በማለት አስረድተዋል።

ዶ/ር ይልቃል ጨምረውም “የአማራ ልዩ ኃይልን በተለይ ትጥቅ ለማስፈታት እና ለመበተን ውሳኔ እንደሌለ” እና ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማዋቀር በፌዴራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት ስምምነት በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል በተለየ መንገድ ትጥቅ የማስፈታት እና የመበተን ዓላማ እንደሌለ በመግለጽ፣ ሕዝቡ ይህንን በመረዳት “በመመካከር ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ በማሰብ ማስከን ይገባል” ብለዋል።

የክልል ልዩ ኃይሎችን የማፍረስ ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ላይ በእኩል ተፈጻሚ የማይሆን እና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት ነው የሚለው ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በመንግሥት እርምጃ ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል።

መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይልን ለማፍረስ ያሳለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአማራ አካባቢዎችን እና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት እና አደጋ የሚዳርግ አደገኛ ውሳኔ መሆኑን በመግለጽ አብን ከቀናት በፊት በፌደራል ኃይሎች እና በአማራ ክልል ልዩ ኃይል መካከል ውጥረት መከሰቱን ገልጾ ነበር።

“ቀውስ እና ትርምስ እንዳይፈጠር”

አብን እሁድ ሚያዚያ 01/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የፌዴራሉ መንግሥት “የልዩ ኃይሉን አመራር ከሠራዊቱ በመነጠል እና ስንቅ፣ ሎጂስቲክ እና ደሞዝ በመከልከል ጭምር ለመበተን ጥረት እያደረገ ይገኛል” በማለት የከሰሰ ሲሆን፣ ይህ እርምጃም “በዕዝ የማይመራ እና መንግሥት የማይቆጣጠረው ኃይል በመፍጠር ክልሉን ወደ ቀውስ እና ትርምስ የሚወስድ ነው” ሲል አስጠንቅቋል።

ስለዚህም አብን መንግሥት “በጥድፊያ የጀመረው ነው” ያለውን የአማራ ልዩ ኃይልን መልሶ የማደራጀት ዕቅድን በይፋ በማቆም በክልሉ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ እና ውጥረት የሚያረግብ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማዋቀር እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ ባወጡት ሰፊ መግለጫ ላይ፣ መንግሥት የክልሎች ልዩ ኃይል አባላትን ወደ አገር መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም ወደ መደበኛ የክልል ፖሊስ ለማስገባት ሲዘጋጅ የቆየ መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔው “ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን” ተግባራዊ እንደሚደረግ እና ከዚህ አንጻር “ሆን ብለው የአፍራሽ ሚና በሚጫወቱ ላይ፤ ተገቢው የሕግ ማስከበር እርምጃ” መንግሥታቸው እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።

ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀቱ ተግባር በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንደሚሆን በመግለጽም፣ ከዚህ በተቃራኒ የተለያዩ “ዥንብሮችን የሚነዙ አካላት ገሚሶቹ ባለማወቅ፣ የተቀሩት ደግሞ ዓላማቸው ሕዝብ ከማበጣበጥ የዘለለ አይደለም” በማለት ወቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም እርምጃውን ከተቃወሙት መካከል “ጥቂት የማይባሉት ‘የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ አለበት’ ብለው ሲጽፉ እና ሲሞግቱ የከረሙ ናቸው” በማለት መንግሥት የጀመረውን የክልል ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራውን እንደሚገፋበት እና በሚያደናቅፉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል።

ይህንን የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ በተመለከተ የተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድጋፋቸውን በመግለጽ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ እየቀረቡ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በሕግ ከተፈቀደላቸው የፀጥታ አስከባሪ ኃይል ባሻገር ወተደራዊ የሥልጠና፣ የትጥቅ እና አደረጃጀት ያላቸው ልዩ ኃይሎች ያሏቸው ሲሆን፣ በዚህ ላይ የፌደራል መንግሥቱ እርምጃ እንዲወስድ በተለያዩ ወገኖች በተደጋጋሚ ሲጠየቅ መቆየቱ ይታወሳል።

አሁን መንግሥት እየወሰደ ያለውን የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ እና ወደ ክልል ፖሊስ እንዲካተቱ ያሳለፈው ውሳኔ ላይ ከአብን በተጨማሪ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) የተባሉት ፓርቲዎች አቋማቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተናጠል ባወጡት መግለጫ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ውሳኔውን ደግፈው፣ ነገር ግን በአገሪቱ ካለው ሁኔታ አንጻር አሁን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው በማለት ተችተዋል።

ጨምረውም ይህ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ሌሎች የመከላከያ እና የፀጥታ ተቋማት የማካተቱ እርምጃ ተግባራዊ ሲደረግ፣ ሌላ ቀውስ በማያስከትል ሁኔታ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ መሆን እንዳለበት መክረዋል።