ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀቱን ውሳኔ የሶማሌ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች እንደሚቀበሉ አስታወቁ

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት
የምስሉ መግለጫ, የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት

መንግሥት የክልሎችን ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት ያወጣውን ዕቅድ የሶማሌ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች እንደሚቀበሉት አስታወቁ።

የሶማሌ ክልል ሚያዝያ 02/ 2015 ባካሄደው 12ኛው ምክር ቤት ጉባኤ የክልሉን ልዩ ኃይሎች መልሶ ለማደራጀት ያወጣውን ውሳኔ ማጽደቁን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ምክር ቤቱ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በመከላከያ፣ በፌደራል እና በክልል ፖሊስ መዋቅሮች ውስጥ መካተትን በተመለከተ ገለጻ ከተደረገለት በኋላ እንዳጸደቀው ነው ሙስጠፋ ያስታወቁት።

የክልል ልዩ ኃይልን ማደራጀት የተጀመረው በሶማሌ ክልል በ1998 ሲሆን በወቅቱ በክልሉ ከፍተኛ ተጽእኖ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባርን (ኦብነግ) ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር በፌደራል መንግሥቱ ድጋፍ ነበር።

በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሉን መልሶ ማደራጀት ስለመጀመሩ የተባለ ነገር ባይኖርም መንግሥት የሁሉንም ክልል ልዩ ኃይሎች መልሶ የማደራጀት ውሳኔ በሁሉም ክልል አመራሮች ጥናት ተደርጎበት፣ ያለ ልዩነት ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል።

በተጨማሪም ከልዩ ኃይል አመራሮች እና አባላት ጋርም ከመግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑንም የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በመግለጫው ማስታወቁ ይታወሳል።

ልዩ ኃይሎችን ‘መልሶ ማደራጀት’ በሌሎች ክልሎች

ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ የጋምቤላ፣ የደቡብ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች የልዩ ኃይል ፖሊስን መልሶ ለማደረጀት እየተዘጋጁ እንደሚገኙ የመንግሥት የዜና አውታሮች ዘገባል።

የጋምቤላ ክልል “አዲሱን የልዩ ኃይል አደረጃጀት ለማስፈጸም” ምዝገባ መጀመሩን የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሰናይ አኩዎር ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምዘገባው የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ወደ መደበኛ የክልል ፖሊስ አሊያም ወደ መከላከያ ሠራዊት ለመግባት ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት ነው።

ኮሚሽነሩ አዲሱ አደረጃጀት የፀጥታ መዋቅሩን ይበልጥ የሚያጠናክር በመሆኑ የክልሉ መንግሥት “በሙሉ ልብ” ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተያያዘም፣ በደቡብ ክልል ልዩ ኃይልን መልሶ ማደራጀት መጀመሩን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ መናገራቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

ኮሚሽነሩ ከልዩ ኃይሉ ጋር በተያያዘ ያለው ተግባር ያለምንም ችግር እየተከናወነ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ውሳኔውን “በየደረጃው ያሉ የመንግሥት እና የሠራዊት አመራሮች እንደዚሁም የሠራዊት አባላት በደስታ ተቀብለውታል” ብለዋል።

ሥራውን በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቀም አክለዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የልዩ ኃይሉ አባላትን ወደ መከላከያ ሠራዊት፣ ፌዴራል ወይም የክልል ፖሊስ የሚያሸጋገረውን አሰራር ለመተግበር ክልሉ “በቁርጠኝነት” እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር ሀሩን ዑመርን ጠቅሶ በፌስ ቡክ ገጹ እንዳሰፈረው ውሳኔው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

በተመሳሳይ የሲዳማ ክልልም ልዩ ኃይሎችን የተመለከተውን ውሳኔ እያስፈጸመ መሆኑን ተገልጿል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በክልላቸው በውሳኔው ዙሪያ ከልዩ ኃይል አመራሮች እና አባላት ጋር “በመመካር አስፈላጊነቱ ላይ ታምኖበት ወደ ሥራ መገባቱን” አንስተው በጥቂት ቀናት መልሶ የማደራጀት ተግባሩ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

ከ18 ወራት በፊት የተመሠረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልም “የልዩ ኃይሉን መልሶ የማደረጀት ሥራውን” እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጿል።

የክልሉ ሰላም እና ደኅንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ እንደ አገር “በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት” ልዩ ኃይሉን መልሶ ማደረጀት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 30/2015 ዓ.ም. የክልል ሰላም ደኅንነት ቢሮ ኃላፊዎች ስብሰባ ማደረጋቸው ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ ዝርዝር ጉዳዮች ባይገልጹም የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ የኦሮሚያ፣ አፋር እና ሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች “መልሶ ማደራጀቱን” በአዎንታ እንደሚመለከቱት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የተነሳው ተቃውሞ

መንግሥት ጠንካራ እና የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት በያዘው ዕቅድ መሠረት “የክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን” አመልክቷል።

መንግሥት የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ በማደራጀት በመከላከያ ሠራዊት በፌደራል ፖሊስ እና በክልል መደበኛ ፖሊሶች የማካተት ውሳኔ መጀመሩንም የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ ከብሔራዊው ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።

ይህ ዕቅድም “በሁሉም ክልሎች እኩል በሆነ መንገድ ተፈጻሚ እየተደረገ መሆኑንም” ጄነራል አበባው ጠቅሰዋል።

በአገሪቱ ያሉ ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ተግባር እንደተጀመረ ቢገለጽም በምን ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ የተባለ ነገር የለም። የአማራ ልዩ ኃይል ተሰማርቶባቸው ከነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች ወጥቶ ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተንቀሳቀሰም እንደሆነ ተገልጿል።

በኮረም እና በአላማጣ የነበሩ የአማራ ልዩ ኃይሎች ከየአካባቢዎቹ ወጥተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የአላማጣ ከንቲባ ኃይሌ አበራ ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

ከተለያዩ አካባቢ የመጡ ልዩ ኃይል አባላት ወደ ደሴ፣ ጎንደር እና ደብረ ብርሃን መድረሳቸውን የሦስቱ ከተሞች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስታውቀዋል።

“በተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ከተለያየ አካባቢ ተነስታችሁ ወደ ከተማችን የመጣችሁ በከተማችን በተዘጋጀው ማረፊያዎች እንድትሰባሰቡ እያሳሰብን ከዚህ ውጭ በተናጠልም ሆነ በቡድን መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እና ጥይት መተኮስ የተከለከለ ነው” ብለዋል የከተሞቹ ኮማንድ ፖስት።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በተለያዩ የፌደራል እና የክልል የፀጥታ መዋቅሮች ውስጥ በመካተት ይደራጃል የሚለው መረጃ መሰማቱን ተከትሎ፣ እርምጃው የክልሉን ልዩ ኃይል ትጥቅ ለማስፈታት ነው በሚል ተቃውሞ እና ውጥረት በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቷል።

ትናንት ሚያዝያ 2/2015ን ጨምሮ በተለይ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ቀናት በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ውስጥ ብዙ ሕዝብ የተሳተፈባቸው የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን እንዲሁም መንገዶች ተዘግተው የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ፎቶግራፎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ ታይተዋል።

ከዚህም ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ኃይሎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ፍጥጫዎች ተከስተዋል።

በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ በአማራ ኃይሎች እና በአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል እሁድ ሚያዚያ 01/2015 ዓ.ም. ግጭት ተከስቶ እንደነበረ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ፋኖ እና የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በአንድ ወገን ሆነው ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል ቢሉም፣ ሌላኛው ነዋሪ ግን ግጭት የነበረው በፋኖ እና በመከላከያ መካከል ብቻ ነው በማለት የልዩ ኃይል አባላት በግጭቱ ተሳታፊ እንደልነበሩ ተናግረዋል።

የክልል ልዩ ኃይሎችን የማፍረስ ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ላይ በእኩል ተፈጻሚ የማይሆን እና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት ነው በሚልም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በመንግሥት እርምጃ ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል።

የአማራ ክልል ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፣ ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ተግባር በሁሉም ክልሎች የሚከናወን መሆኑን በመጥቀስ፣ “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው” ብሏል።