የደብረ ብርሃን፣ ጎንደር እና ደሴ ከተሞች ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ጥብቅ ክልከላዎችን ጣሉ

 የጎንደር ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ ለማዋቀር ይፋ ከሆነው ውሳኔ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች ውጥረት መንገሱን ተከትሎ የደብረ ብርሃን፣ የጎንደር እና የደሴ ከተሞች ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ጥብቅ ክልከላዎችን ጣሉ።

በከተሞቹ ከፀጥታ ኃይል አባላት ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን ጨምሮ ሌሎች ገደቦች መጣላቸውን የሦስቱ ከተሞች የፀጥታ ኮማንድ ፖስቶች ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የጎንደር ሚያዝያ 1 እንዲሁም የደብረ ብርሃን እና የደሴ ከተሞች የፀጥታ ኮማንድ ፖስቶች ደግሞ ሚያዝያ 2 ባወጡት መግለጫ፣ ውሳኔውን ያስተላለፉት የከተሞቻቸውን ሰላምና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል መሆኑን አስታውቀዋል።

በሦስቱም ከተሞች ድምጽ አልባ መሳሪያዎች ተብለው የተዘረዘሩ ጩቤ፣ ገጀራ፣ አንካሴ፣ ጦር እና ፌሮ ብረት፤ ግለሰቦች ይዘው መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው ተከልክሏል። እንዲሁም በማንኛውም ቦታና ሰዓት ጥይትም ሆነ ርችቶችንም መተኮስ እንደማይቻል ተገልጿል።

ሌላኛው የከተሞቹ ምክር ቤቶች የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ያስቀመጡት ክልከላ ከመንግሥት እውቅና ውጭ ያልተፈቀዱ ሰልፎችን ማድረግም ሆነ መንገድ መዝጋት፣ እንዲሁም ወታደራዊ ሥልጠና መስጠትን ነው።

በተጨማሪም አድማ መቀስቀስ፣ አድማ ማድረግ እና ማስተባበር እንዲሁም መደበኛ ሥራን ማስተጓጎል በጥብቅ መከልከላቸውን ከተሞቹ በመግለጫዎቻቸው አስቀምጠዋል።

ከተሞቹ በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ የጣሉ ሲሆን፣ በደብረ ብርሃን እና በደሴ ማንኛውም መጠጥ ቤቶች ከምሽቱ 2 ሰዓት ውጭ ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት መስጠት ተከልክለዋል። በጎንደር ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ተቀምጧል።

በተጨማሪም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለ ሲሆን፣ በደሴ ከምሸቱ 1፡30 እንዲሁም በጎንደር እና በደብረ ብርሃን ከተሞች ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ተከልክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የሚከሰቱ ጥቃቶችን ሸሽተው በደብረ ብርሃን ተጠልለው የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከካምፕ ውጭ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህም ወቅታዊ ሁኔታው እስከሚስተካከል ድረስ እንደሚቆይ የከተማው አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ኮማንድ ፖስት በመግለጫ አሰፍሯል።

ፀጉረ ልውጥ (አጠራጣሪ ሰዎች) ሲሉ ከተሞቹ የጠሯቸውን ግለሰቦች በቤት ማሳደር፣ ማከራየት፣ የሆቴል አልጋ ማከራትም እንዲሁም ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ጥቆማ አለመስጠት በሕግ እንደሚያስጠይቅም አሳስበዋል።

መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ የከለከሉት ሦስቱ ከተሞች መታወቂያ ያልያዙ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ማስጠንቀቂያቸውን አስተላልፈዋል።

በሕግ የሚፈለጉ ወይም ተጠርጣሪዎችን ሽፋን የሰጠ፣ የደበቀ፣ ሐሰተኛ መረጃ ሰጥቶ ያስመለጠ፣ በአጠቃላይ የፀጥታ ኃይሎችን የሕግ ማስከበር ተልዕኮ የማደናቀፍ፣ የማወክንም ተግባር መፈጸም እንደሚያስጠይቅ መግለጫዎቹ አስጠንቅቀዋል።

በተጨማሪም በተከለከሉ ቦታዎች በእምነት ተቋማት፣ በመገበያያ ቦታዎች፣ በሕዝብ መሰብሰቢያዎች፣ በመዝናኛ አካባቢዎች ጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት እና መንቀሳስ እንዲሁ ተከልክሏል።

የሠራዊቱን የመለዮ አልባሳት ከልዩ ኃይል፣ ከፖሊስ፣ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ አባላት ውጭ መልበስ ተከልክሏል።

በከተሞቹ ለሚገኙ የአማራ ልዩ ኃይል አባላትም ጥሪ ያስተላለፉት የሦስቱ ከተሞች የፀጥታ ኮማንድ ፖስቶች “በተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ከተለያየ አካባቢ ተነስታችሁ ወደ ከተማችን የመጣችሁ በከተማችን በተዘጋጀው ማረፊያዎች እንድትሰባሰቡ እያሳሰብን፣ ከዚህ ውጭ በተናጠልም ሆነ በቡድን መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እና ጥይት መተኮስ የተከለከለ ነው” ብለዋል።

ከሰሞኑ ልዩ ኃይሎችን ለማደራጀት መንግሥት ከወሰነው ውሳኔ ጋር በተያያዘ የአማራ ልዩ ኃይል ትጥቅ ሊፈታ ነው በሚል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተቃውሞዎች ተነስተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎችም በመከላከያ ሠራዊት እና በልዩ ኃይሉ መካከል ፍጥጫዎችም ተከስተዋል።

የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት ሁለት ሠራተኞች ባለፈው እሁድ በአማራ ክልል፣ ቆቦ አካባቢ መገደላቸውን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ፋኖ እና የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በአንድ ወገን ሆነው ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል ቢሉም፣ ሌላኛው ነዋሪ ግን ግጭት የነበረው በፋኖ እና በመከላከያ መካከል ብቻ ነው በማለት የልዩ ኃይል አባላት በግጭቱ ተሳታፊ እንደልነበሩ ተናግረዋል።

መከላከያ በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ክልክ ያለፈ ኃይል በመጠቀም በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር አቅራቢያ በምትገኝ መራዊ በተባለች ከተማ ቢያንስ ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል ሲል የአማራ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ አስታውቋል። ጦሩ ለቀረበበት ክስ ከመከላከያም ሆነ ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።