የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት ሁለት ሠራተኞቹ አማራ ክልል ውስጥ መገደላቸውን ገለጸ

ቹል ቶንግይክ እና አማረ ክንደያ

የፎቶው ባለመብት, crs

የምስሉ መግለጫ, ቹል ቶንግይክ እና አማረ ክንደያ

የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት ሁለት ሠራተኞች ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ የአማራ ክልል ውስጥ መገደላቸውን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ሲአርኤስ በመባል የሚታወቀው የካቶሊክ የተራድኦ ድርጅት በደኅንነት ኃላፊው እና በሾፌሩ ግድያ የተሰማውን ሐዘን በገለጸበት መግለጫው ስለክስተቱ በዝርዝር ያለው ነገር የለም።

እሁድ ዕለት ከመስክ ሥራ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ አማራ ክልል ውስጥ የተገደሉት የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት ሠራተኞች ቹል ቶንግይክ የደኅንነት ኃላፊ እና ሹፌሩ አማረ ክንደያ እንደሚባሉ ገልጿል።

ሁለቱ የተራድኦ ድርጅቱ ሠራተኞች በድርጅቱ ተሽከርካሪ እየተጓዙ እንዳለ በጥይት መገደላቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ግድያውን የተመለከተ የሚታወቅ ዝርዝር መረጃ እንደሌለ ሲአርኤስ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት የተገደሉበት ሁለቱ ሠራተኞች ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ሳሉ በአማራ ውስጥ መገደላቸውን እንጂ በትክክል የት ቦታ ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸው ያለው ነገር የለም።

በካቶሊክ እምነት ስር የሚገኘው የተራድኦ ድርጅቱ ሠራተኞችን ግድያ በሚመለከት ከአማራ ክልልም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ በኩል የተባለ ነገር የለም።

የፌደራል መንግሥቱ የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ ለማዋቀር ይፋ ያደረገውን ዕቅድ ተከትሎ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተሳተፈባቸው ተቃውሞዎች እየተካሄዱ መሆናቸው ይታወቃል።

እሁድ ዕለት በምሥራቃዊው የአማራ ክልል ክፍል ውስጥ ቆቦ አካባቢ በታጣቂዎች እና በፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዘመዴ ዘውዴ በባልደረቦቻቸው ላይ በተፈጸመው ግድያ “ከባድ ድንጋጤ እና ሐዘን ውስጥ መግባታቸውን” ገልጸዋል።

ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ላይ የሚሰራው የሰብአዊ እርዳታ ተቋሙ የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት “ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ኢትዮጵያውያንን መደገፉን” እንደሚቀጥል አቶ ዘመዴ ዘውዴ የድርጅታቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት (ሲአርኤስ) የአሜሪካ የረድኤት ድርጅት ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ከአንድ መቶ በላይ በሚሆኑ አገራት ውስጥ ይሰራል።

ለሁለት ዓመታት ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ሦስት የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ሠራተኞችን ጨምሮ ሌሎችም የረድኤት ድርጅቶች ሠራተኞች በተለያዩ ጊዜያት መገደላቸው መዘገቡ ይታወሳል።