የሱዳን አማፂያን በርስ በእርስ ጦርነቱ ትልቅ ለውጥ ያመጣል የተባለ ከተማን መቆጣጠሩን ገለፀ

በሱዳን በቀጠለው ጦርነት የተነሳ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገድደዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሱዳን በቀጠለው ጦርነት የተነሳ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገድደዋል

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) በርስ በእርስ ጦርነቱ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል የተባለውን የኤል-ፋሸር ምዕራባዊ ከተማ መቆጣጠሩን ገለፀ።

ቡድኑ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ባወጣው መግለጫ ኤል-ፋሸርን "ከአሸባሪው ሠራዊት ጋር ከሚተባበሩ ታጣቂዎች እና ከቅጥረኞች መዳፍ" ነጻ አውጥቶ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግሯል።

አር ኤስ ኤፍ ኤል-ፋሸርን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር ከሆነ የሱዳን ጦር በዳርፉር ክልል በእጁ ስር ያለ የመጨረሻው አካባቢ በመሆኑ ትልቅ ኪሳራ ይገጥመዋል።

የሱዳን ጦር ሠራዊት እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

ይህ የሆነው አማፂ ቡድኑ የጦሩ 6ኛ ዲቪዥን ዋና መስሪያ ቤት በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን ካስታወቀ እና "ግዙፍ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን" ማውደሙን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን መማረኩን ይፋ ካደረገ በኋላ ነው።

ቢቢሲ ቬሪፋይ በማኅበራዊ ሚደያ ላይ በስፋት የሚዘዋወሩ እና በሱዳን ጦር ሠራዊቱ ካምፕ ውስጥ የአርኤስኤፍ ተዋጊዎችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ትክክለኛነት አረጋግጧል።

በአካባቢው የሠራዊት ደጋፊ የሆኑ ተዋጊዎች፣ ፖፑላር ሪዚስታንስ፣ አርኤስኤፍ "የኃይሉን ከፍተኛ ሞራል" ለማዳከም "በሚዲያ የሐሰት ዘመቻ" አካሂዷል ሲል ከስሷል።

አርኤስኤፍ ላለፉት 18 ወራት ኤል-ፋሸርን ከብቦ የሠራዊቱን ካምፖች እና ሰላማዊ ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ድብደባ ሲፈጽም ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በግጭቱ ወደ 300,000 የሚገመቱ ሰዎች መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ተግለጿል።

በነሐሴ ወር የሳተላይት ምስሎች በከተማዋ ዙሪያ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ ሰፋፊ ግንቦች መገንባታቸውን አሳይቷል።

አርኤስኤፍ ለሳምንታት ከበርካታ አቅጣጫዎች በአካባቢው የጦር ሠራዊቱ ዋና መስሪያ ቤት ተደርጎ ወደሚቆጠረው 6ኛ እግረኛ ጦር ማዘዣ ሲጠጋ ነበር።

አሁንም አንዳንድ የኤል-ፋሸር አካባቢዎች በጦር ሠራዊቱ እና በአጋር ታጣቂ ቡድኖች ቁጥጥር ስር ቢሆንም ነገር ግን እነዚያ ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ ይቆያሉ ተብሎ አይጠበቅም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር እሁድ ዕለት እንደተናገሩት ከኤል ፋሸር በሚወጡ ዘገባዎች "በጣም ሰግቻለሁ" በማለት በዳርፉር እና በተቀረው ሱዳን አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ፍሌቸር በመግለጫቸው "በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች መውጫ አጥተው፣ በፍርሃት፣ በድብደባ እና በረሃብ ውስጥ ናቸው። ያለ ምንም ምግብ፣ እርዳታ፣ የጤና እንክብካቤ ወይም ደህንነት ብቻቸውን ናቸው" ካሉ በኋላ የተጠናከሩ ጥቃቶች ወደ ከተማዋ ርዳታ ለማስገባት "የማይቻል" አድርጎታል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች አርኤስኤፍ አካባቢውን ከብቦ በቆየበት ወቅት በሰብአዊነት ላይ በርካታ ወንጀሎችን ፈጽሟል ሲሉ ከሰዋል።

አሜሪካ በበኩሏ አርኤስኤፍ በዳርፉር አረብ ባልሆኑ ሕዝቦች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ብላለች።

ሱዳን የፈጥኖ ደራሹ እና የሱዳን ጦር ከፍተኛ አዛዦች በመካከላቸው ባለው የሥልጣን ሽኩቻ የተነሳ መግባባት ባለመቻላቸው እንደ አውሮፓውያኑ ከ2023 ጀምሮ በግጭት እየታመሰች ነው።

በግጭቱ በመላ አገሪቱ ከ150,000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ደግሞ ቤታቸውን ጥለው ተሰድደዋል። ይህም በዓለም ላይ ከደረሱት የከፉ ሰብዓዊ ቀውሶች አንዱ ነው።

ሠራዊቱ አብዛኛውን ሰሜናዊ እና ምሥራቅ የአገሪቱን ክፍል ሲቆጣጠር እስካሁን ድረስ ኤል-ፋሸር በዳርፉር ውስጥ የመጨረሻው በመንግሥት ኃይሎች እና አጋሮቹ ቁጥጥር ስር ያለ ዋና ከተማ ነበር።

አርኤስኤፍ ከሞላ ጎደል ሁሉንም የዳርፉር አካባቢዎች እና አብዛኛው የአጎራባች ኮርዶፋን ክልል ይቆጣጠራል።

ቀደም ሲል ቡድኑ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር በአል-ፋሸር ተቀናቃኝ መንግሥት ለመመስረት ተስፋ እንደሚያደርግ ተናግሮ ነበር።