የሱዳን ሚሊሻ መሪ ከዳርፉር ጦርነት ጋር በተያያዘ በጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የሱዳን ሚሊሻ መሪ ከ20 ዓመታት በፊት በዳርፉር ግዛት የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ጥፋተኛ ተባሉ።
አሊ ሙሐመድ አሊ አብድ-አል-ራህማን ወይም አሊ ኩሻይብ በመባል የሚታወቁት ግለሰብ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከገደለው የጃንጃዊድ መሪዎች አንዱ ነበሩ። ጃንጃዊድ በመንግሥት የሚደገፍ ቡድን ሲሆን ዳርፉርን በማሸበር ይታወቃል።
ኩሻይብ፤ በዳርፉር ከተፈፀመው ወንጀል ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸው የመጀመሪያው ግለሰብ ናቸው የተባሉት ግለሰብ "እኔ አይደለሁም" ሲሉ ተከራክረዋል።
እአአ ከ2003 እስከ 2020 ድረስ በዘለቀ ግጭት በዓለም ላይ ከተፈጠሩት ከባድ የሰብአዊ አደጋዎች አንዱ ነው። በአካባቢው አረብ ባልሆኑ ሕዝቦች ላይ የዘር ማፅዳት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል።
የቀደመው ቀውስ ካበቃ ከአምስት ዓመታት በኋላም ዳርፉር በሌላ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ቁልፍ የጦር ሜዳ ሆናለች። በአሁኑ ወቅት በሱዳን ጦር እና መነሻውን ከጃንጃዊድ ሚሊሻ ባደረገው በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል ጦርነት እየተካሄደ ነው።
በኩሻይብ ችሎት ወቅት በሕይወት የተረፉ ሰዎች መንደሮቻቸው እንዴት እንደተቃጠሉ፣ ወንዶች እንደታረዱ እና ሴቶች ወደ ወሲብ ባርነት ተገደው እንደገቡ ገልጸዋል።
ሰብሳቢው ዳኛ ጆአና ኮርነር በበኩላቸው "በጃንጃዊድ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ መደፈሮች እና ውድመቶች ከማበረታታት በላይ እንዲፈጸም መመሪያ ሰጥቷል" ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም ኩሻይብ አረብ ያልሆኑትን "እንዲያጠፉ" ትዕዛዝ መስጠቱን እና ወታደሮችን "ማንንም ሰው እንዳያልፉ፤ ማንንም በሕይወት እንዳይተርፍ" ማለቱን ተናግረዋል።
የሚሊሺያ መሪው እአአ በ2003 እና 2004 መካከል በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ባተኮሩ በ27 ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
ከውሳኔው በፊት ጥቂት የዳርፉሪ ተወላጆች ቡድን በሆላንድ ዘ ሄግ ወደሚገኘው ፍርድ ቤት ለመግባት በትዕግስት ሲጠባበቁ ታይተዋል።
በመከራቸው ውስጥ ኩሻይብ "የተጫወተውን ወሳኝ ሚና" ምንም ጥርጥር ያልነበራቸው ሲሆን አንድ ግለሰብም "ትዕዛዙን የሰጠው እሱ ነበር። መሳሪያውን ያገኘው እሱ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"እሱ በዳርፉር ወሳኝ እንደሆነ ከጠየቃችሁኝ በጣም ወሳኝ ከሆኑት ውስጥ አንዱ እንደነበረ መናገር እችላለሁ።"
የዳርፉር ጦርነት የጀመረው በወቅቱ በአረቦች የበላይነት የተቋቋመው መንግሥት ጃንጃዊድን በማስታጠቅ ከጥቁር አፍሪካ ጎሳ የተውጣጡ አማፂያንን ለማፈን በማሰቡ ነበር።
ጃንጃዊድ አማጺያኑን ይደግፋሉ ተብለው የተከሰሱትን አረብ ያልሆኑትን ነዋሪዎችን በዘዴ በማጥቃታቸውም የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው ሆኗል።
ተመሳሳይ ስልታዊ ጥቃት አሁንም የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት አካል ሆኖ እየተፈጸመ ይገኛል።
ብዙዎቹ የጃንጃዊድ ተዋጊዎች ከሱዳንን ጦር በተቃራኒ እየተዋጋ ያለውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን (አርኤስኤፍን) ተቀላቅለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አርኤስኤፍ በዳርፉር አረብ ባልሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ የዘር ማትፋት ወንጀል እየፈፀመ ነው ሲሉ ከሰዋል።
በሁለቱ ግጭቶች ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሚሊሻዎችን መቅጠር፣ አመጽን ማፈን እና ጾታዊ ጥቃትን ለጦርነት መሳሪያነት መጠቀም ሲተገበር ቆይቷል ሲሉ በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የሱዳን ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ማቲው ቤንሰን-ስትሮህማየር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በተለይ ጦርነቱ በዳርፉር እየተካሄደ ያለበት መንገድ የሽብር ጦርነት ይመስለኛል" ሲል ገልጸዋል።
"በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ወይም ረሃብን በመጠቀም ምግብ እንዳይገባ በማድረግ በረሃብ እንዲሞቱ ተደርጓል።"
በመጀመርያው የዳርፉር ችግር ሰለባ የሆኑት አብዛኞቹ ተፈናቅለዋል። አይሲሲ ኩሻይብን ክስ ለመመስረት ቢችልም፣ አሁንም ድረስ በሱዳን ባለሥልጣናት ላይ የወጡ የእስር ማዘዣዎች አሉ።
የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በዘር ማጥፋት ወንጀል ቢከሰሱም እሳቸው ግን ክደዋል።
አልበሽር በ2019 በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በሰሜን ሱዳን በወታደራዊ እስር ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።
ኩሻይብ በቅርቡ ቅጣት ይተላለፍባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።















