የሱዳን ጦር በረሃብ ወደተጠቃ አካባቢ እርዳታ ጭነው ሲጓዙ የነበረ የተመድ ተሽካርካሪዎችን ማጥቃቱን አስተባበለ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የሱዳን ጦር በረሃብ በከፋ ወደተጠቃችው የዳርፉር ግዛት አካባቢ እርዳታ ጭነው ሲጓዙ የነበሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን አስተባበለ።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በቁጥጥሩ ስር ባለችው መሊት ከተማ ረቡዕ ዕለት ለተፈጸመው የአየር ጥቃት ጦሩን ተጠያቂ አድርጓል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ስለ ጥቃቱ ብዙ ዝርዝሮችን ባይሰጥም እርዳታ ጭነው ሲጓዙ ከነበሩ 16 ተሽከርካሪዎች መካከል ሶስቱ ተጎድተው በእሳት መያያዛቸውን ገልጿል።
በተሽከርካሪዎቹ መካከል የነበሩ ሁሉም ሰራተኞች ደህና መሆናቸውንም ተቋሙ አክሏል።
ሦስተኛ ዓመቱን በያዘው ደም አፋሳሹ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ሕይወት ተቀጥፏል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል እንዲሁም በአህጉሪቷ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ የአየር ኃይል ባይኖረውም ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ድሮኖችን ይጠቀማሉ።
ይህ ጥቃት በሱዳን ውስጥ በረድዔት ተግባራት ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች አንዱ ነው።
"የረድዔት ሰራተኞች እና ንብረቶች በፍጹም ኢላማ መሆን የለባቸውም"ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተፋላሚ ወገኖች የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግን እንዲያከብሩ አሳስቧል።
የዓለም ፕሮግራም "ተጨማሪ መረጃ እየሰበሰበ" እንዲሁም የረቡዕ ጥቃት ያስከተለውን ጉዳት እየገመገመ መሆኑን አስታውቋል።
እርዳታ የጫኑት ተሽከርካሪዎች ከኤል ፋሸር በስተሰሜን ምዕራብ 90 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና ሜሊት አቅራቢያ ወደምትገኝ በረሃብ በተጠቃች መንደር እያመራ ነበር ሲል የዓለም ምግብ ፕሮግራም አክሎ ገልጿል።
በጦሩ ቁጥጥር ስር የምትገኘው ኤልፋሽር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለአንድ ዓመት ያህል በከበባ ስር ትገኛለች።
ከተማዋ በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች እየተደረገ ያለው ውጊያ የተፋፋመባት ስፍራ ሲሆን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኤልፋሽርን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ውጊያ ባለፉት ሳምንታት አጠናክሮ ቀጥሏል።
ሁለቱም ወገኖች ረሃብን የጦር መሳሪያ በማድረግ እርዳታ እንዳይደርስ እንዲሁም በመዝረፍ ተወንጅለዋል።
በኤልፋሽር ሰኔ ወር ላይ በተፈጸመ ጥቃት አምሰት የረድዔት ሰራተኞች ተገድለዋል።
በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ 12 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ከ4.5 ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞች በአብዛኛው ሴቶች እና ህጻናት ወደ ጎረቤት አገራት ተፈናቅለዋል።















