በሱዳን ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት በምግብ እጥረት መሞታቸውን የህክምና ባለሙያዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጦርነት በተጎዳችው ሱዳን፤ ምስራቃዊ ዳርፉር ግዛት በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ በተፈጠረ ከባድ የምግብ እጥረት ምክንያት ባለፈው ወር 13 ህፃናት መሞታቸውን የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ።
ላጋዋ በተባለው ካምፕ ውስጥ የሚሠሩ አባላት ያሉት 'ዘ ሱዳን ዶክተርስ ኔትዎርክ' የተባለ የሙያ ድርጅት፤ በመጠለያው ያለው "የሰብአዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን" አስታውቋል።
ሀገሪቱን ባወደመው የ27 ወራት የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት የተፈጠረው የረሃብ ቀውስ በተፈናቃዮች ዘንድ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲስፋፋ ማድረጉንምም ተናግሯል።
በኤል ዳኢን ከተማ ውስጥ የሚገኘው መጠለያ ቢያንስ 7,000 ሰዎች የሚኖሩበት ሲሆን በተደጋጋሚ ጊዜያትም በታጣቂ ቡድኖች ጥቃት ሲደርስበት ቆይቷል።
በሀገሪቱ ረሃብ መከሰቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸው በምዕራብ ዳርፉር በሚገኝ ካምፕ ውስጥ ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ግን ረሃቡ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፍቷል።
'ዘ ሱዳን ዶክተርስ ኔትዎርክ' ላጋዋ ካምፕን አስመልክቶ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ "ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የሰብአዊ ድርጅቶች ለካምፑ ነዋሪዎች በተለይም ለህፃናት እና ለነፍሰ ጡር ሴቶች ምግብ እና መሰረታዊ የጤና እንክብካቤ ለማቅረብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ ድርጅቱ ጥሪ ያቀርባል" ብሏል።
ካምፑ የሚገኝባት የምስራቅ ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ዳኢን፤ ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጋ ባለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሙሉ ቁጥጥር ስር ነች።
ሶስተኛው ዓመቱን የያዘው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት፤ የሰብአዊ ድጋፍን አቅርቦቶች እንዲደናቀፉ፣ ኢኮኖሚው እንዲፈራርስ፣ እንዲሁም ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል።
እነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ የምግብ ቀውሱን አስከትለዋል።
በሀገሪቱ ከሚታየው የረሃብ ሁኔታ በተጨማሪ በዳርፉር የኮሌራ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል የእርዳታ ቡድኖች አስጠንቅቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ በታዊላ ከተማ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል። በከተማው፤ ከሰኔ ወዲህ 1,500 ከባድ ህመም ያጋጠማቸው ሰዎች በኮሌራ መያዛቸውን እንደተረጋገጠ ሪፖርት ተደርጓል።
የውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ አገልግሎቶች መቋረጥ በሀገሪቱ ካለው ዝቅተኛ የክትባት ሽፋን ጋር ተዳምሮ የኮሌራ ወረርሽኝ አደጋን እንደጨመረም የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።
ሱዳን በሚያዝያ 2023 ወደ የእርስ በእርስ ጦርነት የገባችው በሀገሪቱ ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል የነበረው ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻ ማደጉን ተከትሎ ነው።
ሁለቱ ባላንጣዎች፤ አንድ ላይ መፈንቅለ መንግሥት በመፈጸም ስልጣን የያዙ አጋሮች የነበሩ ቢሆንም ወደ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደገፈው ሀገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር የማሸጋገር እቅድ ምክንያት ተለያይተዋል።
ይህ ጦርነት በዓለም ላይ እጅግ የከፋው የሰብአዊ ቀውስ ሱዳን ውስጥ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን የተገደሉ ሲሆን ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገድደዋል። አንድ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ደግሞ በረሃብ ላይ ናቸው።















