በነዳጅ የበለፀገውን የአገሪቱን አካባቢ ለመቆጣጠር የሚፋለሙት የሱዳን ኃይሎች

መሳርያ ትከሻው ላይ ያደረገ የሱዳን ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ላለፉት ሁለት ዓመታት ሁለቱ ተፋላማዊ ወገኖች የበላይነት ለማግኘት በሚያደርጉት ከባድ ውግያ ሱዳን ከፍተኛ ውድመትን አስተናግዳለች

በነዳጅ ዘይት የበለፀገው የሱዳን ኮርዶፋን አካባቢ በጦር ኃይሉ እና በተቀናቃኞቹ ወታደራዊ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ጦርነት ወደ ግጭት ማዕከልነት ተቀይሯል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ሁለቱ ተፋላማዊ ወገኖች የበላይነት ለማግኘት በሚያደርጉት ከባድ ውጊያ ሰፊዋ ሱዳን ከፍተኛ ውድመትን አስተናግዳለች።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን የገደሉ ጥቃቶች መድረሳቸውን ተከትሎ ትኩረቶች በዚህ የአገሪቱ ክፍል ላይ ወደሚደረገው ውጊያ ሆኗል።

"ኮርዶፋንን የሚቆጣጠር የአገሪቱን የነዳጅ ዘይት አቅርቦት እና ከፍተኛ መጠን ያለው የሱዳንን ነዳጅ በብቃት ይቆጣጠራል" ሲሉ የኦሲስ ፖሊሲ አማካሪ አሚር አሚን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ክልሉ ወደብ ለሌላት ደቡብ ሱዳንም ወሳኝ ነው፤ ነዳጇን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችላትን የቧንቧ መስመር የዘረጋችው በኮርዶፋን በኩል በመሆኑ ስለዚህ አካባቢው መረጋጋት የራሷ የሆነ ፍላጎት አላት።

ይሁን እንጂ ከሰኔ ወር ጀምሮ ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሚኖርባቸው ሦስት አካባቢዎች ያተኮረው ጦርነት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በእነዚህ ወራት የሱዳን ሠራዊት ዋና ከተማዋን እና የአገሪቱ የግብርና ማዕከል የሆነችውን ገዚራ ግዛትን መልሶ መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጎ ቆይቷል።

የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ ጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሐን በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 20 ቀን ጦራቸው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከካርቱም ጠራርጎ ካስወጣ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ዋና ከተማዋን ጎብኝተዋል።

ጄነራል ቡርሐን በምሥራቅ ፖርት ሱዳን ከተማ መቀመጥን መርጠዋል።

ይህም አሁንም ወደ ካርቱም በቋሚነት ለመመለስ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ይጠቁማል።

ግጭቱ ወደ 150 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሌሎችን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።

ይህም ከቱኒዚያ ወይም ከቤልጂየም ሕዝብ ጋር እኩል ነው።

በካርቱም ከተማ በውግያው የደረሰ ውድመት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን ግጭት ወደ 150,000 የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉትን ደግሞ አፈናቅሏል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ ወር 2023 በጄነራል ቡርሐን እና በወቅቱ አጋራቸው የፈጥኖ ደራሽ ጦሩ አዛዥ ጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ "ሄሜቲ" መካከል ከፍተኛ አለመግባባት ተከስቶ ወደ ጦርነት ካመሩ በኋላ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ካርቱምን ተቆጣጠረ።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) በ2021 አል ቡርሐን መፈንቅለ መንግሥት በሚወጥኑበት ወቅት እገዛ አድርጎላቸዋል።

ይህ ግን ጄነራል ዳጋሎ የመከላከያ ኃይላቸውን ወደ ጦር ሠራዊቱ የማዋሀድ ዕቅዱን ከተቃወሙ በኋላ ወደ አለመግባባት እና ወደ ጦርነት አድጓል።

የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ተንታኝ አለን ቦስዌል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሠራዊቱ አሁን በኮርዶፋን የሚገኘውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በማሸነፍ በምዕራብ አቅጣጫ ወደ ዳርፉር መግፋት ይፈልጋል።

በሌላ በኩል አርኤስኤፍ ኮርዶፋንን መቆጣጠር ከቻለ "አዲስ ጉልበት" ስለሚሰጠው እና "ዋና ከተማዋን ጨምሮ በማዕከላዊ ሱዳን እንደገና በቅርብ ርቀት ላይ ስለሚያስቀምጠው" ኮርዶፋንን ለመያዝ ይፈልጋል ሲሉ ቦስዌል ተናግረዋል።

የሱዳን ትራንስፓረንሲ ኤንድ ፖሊሲ ትራከር ዳይሬክተር ዶ/ር ሱሌይማን ባልዶ በበኩላቸው ሠራዊቱ በኮርዶፋን የሚገኘውን የአርኤስኤፍ መከላከያ መስመሮችን ሰብሮ መግባት ይችላል በሚለው ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

አብዛኞቹ የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ለዳርፉር አዋሳኝ ከሆነው በምዕራብ ኮርዶፋን ግዛት ከሚኖሩት ከሚሴሪያ ብሔረሰብ የተውጣጡ መሆናቸውን ገልጸው "ስለዚህም የራሳቸውን ማኅበረሰቦች ለመከላከል ይዋጋሉ" ይላሉ።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በምዕራብ ኮርዶፋን ዋና ከተማዋን ኤል ፉላ እና የአቡዛባድን ከተማን ጨምሮ በጦር ኃይሉ የተፈፀመው የአየር ድብደባ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰዋል።

አክለውም "ማኅበረሰቡ አርኤስኤፍን ስለሚደግፍ ብቻ በጅምላ ጥቃት ማድረስ ጎጂ ብቻ ሳይሆን የማይጠቅም ፖሊሲ ነው" ብለዋል።

ካርታ

ጦር ሠራዊቱ አሁንም በክልሉ የነዳጅ ቦታዎችን ተቆጣጥሯል፣ ነገር ግን አርኤስኤፍ የአየር ድብደባው ካልቆመ በደቡብ ኮርዶፋን ወደሚገኘው እና ለደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ወደ ሆነችው ነዳጅ አምራች ሄግሊግ ጦርነቱን እንደሚያሰፋ ዝቶ ነበር።

በኤል ፉላ የአየር ድብደባ የተፈፀመበትን ገበያ ከጎበኙ በኋላ "የጦር ኃይሉ ተመልሶ በምዕራብ ኮርዶፋን ግዛት ዜጎች ላይ የቦምብ ድብደባ ከፈጸመ የሄግሊግን ነዳጅ በመዝጋት ኢንጂነሮችን እንገድላለን" ሲሉ መናገራቸው በሱዳን ትሪቡን ተዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) እንደገለጸው በኤል ፉላ እና አቡ ዛባድ የተፈፀመው ጥቃት፣ በትምህርት ቤት የተጠለሉ ቤተሰቦችን ጨምሮ፣ ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

ኦቻ ጥቃቱን አውግዞ፣ ሰላማዊ ዜጎች እና የሚኖሩባቸው ሕንፃዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ቤቶች እና መጠለያዎች "በፍፁም ዒላማ ሊደረጉ አይገባም" በማለት ተፋላሚ ቡድኖች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕጎችን ማክበር አለባቸው ብሏል።

አርኤስኤፍም ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አድርጓል ተብሎ ተከስሷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በሰሜን ኮርዶፋን ባራ አካባቢ እና ሻግ አልኖም እንዲሁም ሂላት ሃሚድ መንደሮች በተፈፀመ ጥቃት 24 ወንዶች፣ 11 ሴት ልጆች እና ሁለት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ ከ450 በላይ ንፁሃን መገደላቸውን አስታውቋል።

"እነዚህ ጥቃቶች አሰቃቂ ናቸው" ያለው ዩኒሴፍ "አስፈሪው የግጭቱ መባባስን ማሳያ ናቸው" እንዲሁም "ለሰው ልጅ ሕይወት ሙሉ በሙሉ ግድየለሽነትን ያመለክታሉ" ብሏል።

በመጠለያ ውስጥ ያሉ ሰዎች እና ውሃ የተሸከመች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጦርነቱ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ቤታቸውን ጥለው የተሰደዱ ሲሆን፣ በርካቶች እንደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ባሉ ጎረቤት አገራት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይኖራሉ

ግጭቱን የሚከታተለው መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ዬል የሰብዓዊ ምርምር ማዕከል፣ ከሻግ አልኖምን የተገኙ የሳተላይት ምሥሎች "ሆን ተብሎ በመሳሪያ የታገዘ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳይ ነው" ብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ የሕግ ባለሙያዎች መብት ተሟጋች ቡድን ከ200 የሚበልጡ ተጎጂዎች "በቤታቸው ሳሉ ተቃጥለዋል ወይም በጥይት ተደብድበዋል" ብሏል።

አርኤስኤፍ የሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን ኤል ኦቤይድን ለመያዝ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚለውን ዘገባ ተከትሎ የሰዎች ሞት ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋት ጨምሯል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የኡሙ ሱማይማ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች እጅ ገብታለች።

ዶ/ር ባልዶ "ከኤል ኦቤይድ በፊት ለሱዳን ጦር ኃይሎች የመጨረሻው የመከላከያ አካባቢ ነው" ብለዋል ።

አሚን ኡም ሱማይማን መቆጣጠሩ አርኤስኤፍ፣ በኤል ኦቤይድ የሚገኘውን ሠራዊት ለመክበብ እንደሚያስችለው ገልጸው፣ ሠራዊቱ በሌሎች የኮርዶፋን አካባቢዎች ወታደሮቹን ለማስታጠቅ አዲስ የአቅርቦት መስመር ለመፍጠር ይፈልጋል ብለዋል።

በኮርዶፋን የሚካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ዋጋ ከማስከፈሉ በተጨማሪ 390 ሺህ ካሬ ስኩዌር ሜትር በሚሸፍነው አካባቢ የሚካሄደው ይህ ውጊያ የተራዘመ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

አሚን "የጦርነቱን አሸናፊ የሚሆነው አከራካሪ ቢሆንም፤ ግን በእርግጠኝነት መሬት አንቀጥቅጥ ለውጥ ያመጣል" ብለዋል።