በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮሎምቢያ የቀድሞ ወታደሮች ሱዳን ውስጥ ምን ያደርጋሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሞኑ የታጠቁ ሱዳናውያን የአንድ ኮሎምቢያዊ ፓስፖርት፣ መታወቂያ እና ሌሎችን ሰነዶችን ሲቀባበሉ በአንድ ማኅበራዊ ሚዲያ በተጋራ ቪዲዮ ላይ ታይቷል።
በፓስፖርቱ ላይ የሚታየው ግለሰብ ስም ክርስቲያን ሎምባና ሞንካዮ የሚል መሆኑንም ቪዲዮው አሳይቷል።
የግለሰቡ መታወቂያ፣ የትራንስፖርት ካርድን ጨምሮ በስፓኒሽ ቋንቋ በልጅ የተጻፈ የሚመስል "አንተ የእኔ ታላቅ አባት ነህ፤ እወድሃለሁ" የሚል መልዕክት የሰፈረበት ደብዳቤ ለዕይታ በቅቷል።
ቢቢሲ ይህንን እና በበርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በቅርቡ የተጋሩ ቪዲዮዎችን ተመልክቷል። እነዚህ ቪዲዮዎች የትና መቼ እንደተቀረጹ ቢቢሲ ማወቅ ባይችልም፤ በቪዲዮዎቹ ላይ የሚታዩት ሰነዶች እውነተኛ እንደሚመስሉ ተረድቷል።
ከቪዲዮዎቹ አንዱ የታተመው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን በጥምረት እየተዋጉ ካሉት የትጥቅ ትግል የጋራ ኃይል (ጄኤፍኤስ) በተሰኘው ቡድን ነው።
ቡድኑ ከቪዲዮው ጋር አያይዞ በፌስቡኩ ላይ ባወጣው መግለጫ ከሊቢያ ወደ ሱዳኗ ዳርፉር እየተጓዙ የነበሩ የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች በቡድኑ በረሃ ውስጥ ተጠልፈዋል ብሏል።
የኮሎምቢያዊውን ሰነዶችን በማጣቀስ "በሱዳን ጦርነት ውስጥ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚያሳይ ነው" ሲል ቡድኑ በመግለጫው አትቷል።
በዚህ ቪዲዮ ላይ ፓስፖርቱ የሚታየው ክርስቲያን ሎምባና ሞንካዮ የት እንዳለ ወይም ስለ መገደሉ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
ሆኖም በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በሚደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወግነው እየተፋለሙ ካሉ በርካታ የኮሎምቢያ ወታደሮች መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችል ከኮሎምቢያ ሚዲያዎች፣ ከኮሎምቢያ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከቢቢሲ ሙንዶ የተገኙ ምንጮች ይጠቁማሉ።
ከጥቂት ወራት በፊትም የሱዳን ጦር ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እየተዋጉ ያሉ "22 የኮሎምቢያ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን" ዳርፉር ውስጥ በፈጸመው የድሮን ጥቃት ገድያለሁ ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Captura de redes sociales
'በመቶዎች የሚቆጠሩ' ኮሎምቢያውያን ወታደሮች
ሦስተኛ ዓመቱን በያዘው ደም አፋሳሹ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ሕይወት ተቀጥፏል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል እንዲሁም በአህጉሪቷ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
በዚህ የሱዳን ጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ ስላሉ ኮሎምቢያውያን ቁጥር ምንም ዓይነት ይፋዊ መረጃ የለም።
ነገር ግን በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች በሱዳን ጦርነት የበርካታ አገር ዜጎች እየተሳተፉ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
ከእነዚህ ሪፖርቶች መካከል ላሲላ ቪቺያ የተባለ መጽሔት ከ300 በላይ ወታደሮች እየተሳተፉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል።
የኮሎምቢያ ወታደሮች በሱዳን ጦርነት እየተሳተፉ ነው የሚሉ የሚዲያ ዘገባዎችን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በሰጡት ምላሽ "ተታልለው ወደ አፍሪካ የሄዱ ወጣቶቻችንን ለመመለስ መንገድ እንዲፈልግ" ለአገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠይቀዋል።
የኮሎምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የዜጎቹን ወደ አፍሪካ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት እንደሚያውቅ ገልጾ "አንዳንድ ወገኖቻችን በተራቀቁ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ መረቦች ተታልለው ከአገር በመውጣት በዓለም አቀፍ ግጭቶች እንደ ቅጥረኛ እየተሳተፉ ነው" ብሏል።
ቢቢሲ ሪፖርት የተደረጉ የኮሎምቢያውያንን የጦርነት ተሳትፎ አሃዝ በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሎምቢያውያን የውጭ አገር ምልመላ
ኮሎምቢያውያን ወታደሮች በውጭ አገራት ጦርነቶች ለመሳተፍ መጓዝ በርካታ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ክስተት ነው።
በአገሪቱ ለዓመታት የዘለቀው የትጥቅ ግጭት እና በአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ላይ ያነጣጠሩ ወታደራዊ ዘመቻዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የሠለጠኑ ወታደሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነዋል።
እነዚህ ወታደሮች በኮሎምቢያ ባለው ዝቅተኛ ገቢ ለመተዳደር ይቸገራሉ።
አማራጭ የሥራ ዕድል በማጣትም እንደ ዩክሬን ወይም ቀደም ባሉ ዓመታት በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ በነበሩ ጦርነቶች ለመዋጋት ወደ ባሕር ማዶ ያቀናሉ።
በኮሎምቢያ የቀድሞ ወታደራዊ መኮንን እንዲሁም የቀድሞ ወታደሮች ፖሊሲዎችን ተንታኝ የሆኑት አልፎንዞ ማንዙር ወደ ውጭ አገራት የሚሄዱ ኮሎምቢያውያን ተዋጊዎች ቁጥር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ መጨመሩን ያስረዳሉ።
ለዚህም መነሻው 'ፕላን ኮሎምቢያ' የተሰኘው እና አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ያደረገችው የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር እና የታጠቁ ቡድኖችን ለመዋጋት በአስር ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወታደራዊ እርዳታን ያካተተተው የሁለትዮሽ ስምምነት እንደሆነ ያስረዳሉ።
"ይህ ሁኔታ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በቂ የገቢ ምንጭ ሳይኖራቸው ከውትድርና የሚገለሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኮሎምቢያውያን ወታደሮችን ፈጠረ" ይላሉ ማንዙር።
እነዚህ የቀድሞ ወታደሮች ዝቅተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ሥራዎች ቃል ተገብቶላቸው በተጻራሪው ወደ ጦር ግንባሮች እንዲሰማሩ ማድረግ የተለመደ ሆኗል።
ይህ ከተገባላቸው ቃል በተቃራኒ የኮሎምቢያውያኑ በጦር ግንባሮች ስምሪት በዩክሬን እየተካሄደ ስለመሆኑ ቢቢሲ ሙንዶ አንድ ዘገባ አውጥቷል።
ይህ ሁኔታ በሱዳን ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል ጥቆማዎች አሉ።
በርካታ ወደ ሱዳን የተመለመሉ ኮሎምቢያውያን በአፍሪካ የፀጥታ ዘርፍ እንዲሰማሩ በሚል ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ባቀኑበት "የተጭበረበረ ሂደት" መሆኑን ቢቢሲ ሙንዶ ከምንጮቹ መስማቱን ዘግቧል።
እነዚህ ምንጮች ይህንን የሚደግፉ ሰነዶች በማስረጃነት ቢያቀርቡም ቢቢሲ ሙንዶ ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ አልቻለም።
የሱዳን ጦር በአሁኑ ወቅት ሦስተኛ ዓመቱን በያዘው የእርስ በእርስ ጦርነት የተባበሩት አረብ ኤምሬት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ተዋጊዎችን በማስታጠቅ እንዲሁም በማጓጓዝ ድጋፍ ታደርጋለች የሚል ክስ ሲያቀርብ ቆይቷል።
በሱዳን ታጣቂዎች ከተገኙት ክርስቲያን ሎምባና ሞንካዮ ንብረቶች መካከል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መገበያያ ገንዘብ አንዱ መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ከለጠፉት እና ቢቢሲ የተመለከተው ቪዲዮ ላይ መገንዘብ ይቻላል።
በተጨማሪም ክርስቲያን ያደረጋቸውን ጉዞዎች በተመለከተ በቲክቶክ እና በፌስቡክ የሰነደ ሲሆን፣ በዚህም የዱባይ እና አቡዳቢ ጉዞዎች መካተታቸውን ቢቢሲ ቪዲዮዎቹን ተመልክቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የጦር መሳሪያዎችን፣ ሎጂስቲክ እና ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ወታደራዊ ድጋፍ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሊቢያ፣ በቻድ እና በደቡብ ሱዳን በኩል እያደረገች ስለመሆኑ "ተአማኒ" መረጃዎችን ማግኘቱን በጥር ወር ባወጣው ሪፖርቱ አውጥቷል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሱዳን ግጭት ተሳታፊ ስለመሆኗ በተደጋጋሚ ስታጣጥል ቆይታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሎምቢያውያኑ የሱዳን ጉዞ
ኡሬና ሳንቼዝ የተሰኙ ምሁር ኮሎምቢያውያን የውጭ አገር ሥራዎችን የሚያገኙት በቀድሞ ወታደሮች በተቋቋሙ የዋትስአፕ ቡድኖች መሆኑን ገልጸው፤ በመጨረሻም እንደ ሱዳን ባሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ይላሉ።
ሳንቼዝ እንደሚሉት ምልመላው የሚከናወኑ መሬት ላይ በሌሉና "በወረቀት ላይ ብቻ በሰፈሩ" ኩባንያዎች መሆኑን ይናገራሉ።
በአብዛኛውም በከፍተኛ የኮሎምቢያ የጦር አዛዦች የተቋቋሙ የዋትስኦፕ ቡድኖች እነዚህ ሥራዎች እንደሚተዋወቁ ያክላሉ።
ኦማር አንቶኒዮ ሮድሪጌዝ ከበርካታ ዓመታት በፊት የኮሎምቢያ የቀድሞ ወታደሮችን ለፀጥታ ሥራዎች ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚልክ ቀጣሪ ኩባንያ ነበረው።
ሆኖም አንዳንዶቹ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አቅንተው ለሊቢያ የፀጥታ ሥራ ተቀጥራችኋል ቢባሉም በሱዳን ጦርነት ተዋጊ እንደሆኑ ያስረዳል።
"በሊቢያ የግል የፀጥታ ኩባንያ እንደሚቀጠሩ ቃል ቢገባላቸውም ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ወግነው ከጦሩ ጋር እንዲፋለሙ ተደርገዋል" ሲል ሮድሪጌዝ ለቢቢሲ ሙንዶ ገልጿል።
"አንዳንዶቹ ቀድሞውኑ ተመልሰዋል፣ ሌሎቹ ደግሞ በቦምብ ጥቃቶች እና በውጊያዎች ከተሳተፉ በኋላ ወደ ኮሎምቢያ ለመመለስ እየጠየቁ ነው። ነገር ግን ቀላል አይደለም" ሲል ሮድሪጌዝ ያስረዳል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ሱዳን እየመጡ ያሉ ኮሎምቢያውያን ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ዘገባዎቹም ሆነ ሮድሪጌዝ ይገልጻል።
ሳንቼዝ በበኩላቸው "የቋንቋ ችግር፣ የግዛቲቱ [ሱዳን] ስፋት እና ኮሎምቢያ በአፍሪካ ያላት የዲፕሎማሲያዊ ውስንነት ለኮሎምቢያውያኑ ወታደሮች ከዚህ ሁኔታ የመውጣት ሁኔታን ፈታኝ አድርጎባቸዋል" ይላሉ።
ቢቢሲ ሙንዶ እነዚህን ክሶች አስመልክቶ የተባበሩትን አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በጠየቀበት ወቅት ክሱን ውድቅ የሚያደርግ ምላሽ ነው ያገኘው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ለየትኛውም ተፋላሚ ወገን ድጋፍ ትሰጣለች የሚባለውን ውድቅ አድርጎ "አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ እና ለጦርነቱ ሰላማዊ እልባት እንዲሰጠው" በመግለጫው አትቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ ያሉ ኮሎምቢያውያን
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፤ በአገልግሎት ላይ ባሉ ወይም በቀድሞ የኮሎምቢያ ወታደሮች ዘንድ በተወሰነው መልኩ በምትከፍለው ደመወዝ ምክንያት ተመራጭ ከሆኑ መዳረሻዎች አንዷ ሆናለች።
በኮሎምቢያ እና በአረብ ባሕረ ገብ መሬት አካባቢ ልምድ ያላቸው እና በዓለም አቀፉ ክራይሲስ ቡድን የደኅንነት እና የግጭት ተንታኝ ኤልዛቤት ዲከንሰን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የተመለመሉ የቀድሞ የኮሎምቢያ ወታደሮች ከዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2015፣ "በየመን ግጭት ተሳታፊ እንደነበሩ" ያስረዳሉ።
"በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ብቻ እንደሚሠለጥኑ፣ ኑሯቸውን በዚያ ብቻ እንደሚያደርጉ እና መቼም ወደ ጦርነት ግንባሮች አንላክም ብለው ያመኑ እና ከውላቸው ውጪ ራሳቸውን በግንባሮች ያገኙ የቀድሞ ወታደሮችን አናግሬያለሁ" ሲሉ ተንታኟ ለቢቢሲ ሙንዶ ገልጸዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ምንም ተሳትፎ የለኝም ብትልም ባለሙያዋ "አሁንም አጠራጣሪ ምልመላዎች እንዳሉ የሚያሳምኑ ሁኔታዎች አሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።
በአውሮፓውያኑ 2010 ገደማ በርካታ የኮሎምቢያን ጦር የለቀቁ ወይም የቀድሞ ወታደሮች የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን የመከላከያ ኃይል ተቀላቅለዋል።
የአገሪቱን የመከላከያ ኃይል የተቀላቀሉት ኮሎምቢያውያን በሱዳን ጦርነት ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ይገኙበት እንደሆነ የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ የለም።
"ይህ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላቲን አሜሪካውያንን ማለትም ኮሎምቢያ፣ ፓናማ፣ ቺሊ፣ ሳልቫዶርን ያካተተ የጦር ክፍል የማቋቋም ፕሮጀክት" እንደሆነ የሚያስረዳው ሮድሪጌዝ፤ ይህም በሕጋዊ እና በመደበኛነት የተፈጸመ እንጂ አሁን ካለው ከሱዳን ጦርነት ጋር ምንም ግንኙት የለውም ይላል።
በኮሎምቢያ የአንድ ወታደር ደመወዝ ከ500 አስከ 700 ዶላር የሚደርስ ሲሆን፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከዚህ ከአራት እስከ አምስት እጥፍ የበለጠ ገቢ ያገኛሉ።
"የደኅንነት ትብብር በኮሎምቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት መሠረት የነበረ ሲሆን፣ አጋርነቱ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይም እያደገ መጥቷል" ሲሉ ሳንቼዝ ያስረዳሉ።















