የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አውሮፕላኗ በሱዳን ጦር የመመታቱን ዘገባ አስተባበለች

የሱዳን ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን ጦርነት

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ቢያንስ 40 የኮሎምቢያ ቅጥረኞችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላኗ በሱዳን ጦር የመመታቱን የሱዳን ብሔራዊ ቴሌቪዥንን ዘገባ አስተባበለች።

አውሮፕላኑ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በሚጠቀምበት ደቡባዊ ዳርፉር በሚገኝ አየር ማረፊያ ሊያርፍ ሲል በጦሩ ተመትቶ ተሳፍረው የነበሩ ቢያንስ 40 የኮሎምቢያ ቅጥረኞች መገደላቸውን የሱዳን ቴሌቪዥን ዘግቧል። በተጨማሪ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሊሰጥ የነበረ የጦር መሳሪያዎች በሙሉ በዚህ ጥቃት መውደማቸውን ዘገባው አክሏል።

"የሱዳን አየር ኃይል በኒያላ አየር ማረፊያ የአየር ጥቃት በመፈጸም በዚህም እርምጃ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል" ሲል የሱዳን ቴሌቪዥን ዘግቧል።

ዘገባው አክሎም "የሱዳን ሉዓላዊነት ቀይ መስመር ነው" ብሏል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ይህንን ዘገባ ውድቅ አድርጋ " በድጋሚ እነዚህ በፖርት ሱዳን ባለስልጣን ተብዬ የተሰራጨው ውንጀላ መሰረተ ቢስ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ሃሰት ነው። ምንም አይነት ማስረጃ የሌለው እና የባለስልጣኑ ቀጣይነት ያለው ሃሰተኛ መረጃ ዘመቻ አካል ነው" ሲሉ አንድ የኤምሬትስ ባለስልጣን ለቢቢሲ በላኩት ኢሜይል ገልጸዋል።

የሱዳን ጦርም ሆነ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት በይፋ ያሉት የለም።

የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቭ ፔትሮ በበኩላቸው መንግሥታቸው ምን ያህል ኮሎምቢያውን እንደሞቱ ለማረጋገጥ እየሞከረ እንደሆነ እና አስክሬናቸውን መመለስ ይቻል እንደሆነ እያጣራ መሆኑን በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ሶስተኛ ዓመቱን በያዘው የእርስ በእርስ ጦርነት የተባበሩት አረብ ኤምሬት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ተዋጊዎችን በማስታጠቅ እንዲሁም በማጓጓዝ ድጋፍ ታደርጋለች የሚል ክስ ሲያቀርብ ቆይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርቶች በበኩላቸው የአረብ ኤምሬትስን በሱዳን ጦርነት ተሳትፎ በተመለከተ ከአለም አቀፍ ድርቶች እንዲሁም በአሜሪካ ፖለቲከኞች መግለጫዎች የተደገፉ "ተአማኒ ማስረጃዎችን" ዋቢ አድርገው አረጋግጠዋል።

በዚህ ሳምንት የኮሎምቢያ ቅጥረኞች ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና አጋሮቻቸው ሊዋጉ ነው የሚሉ ሪፖርቶች ጋር ተያይዞ ውጥረቱ ተባብሷል።

እነዚህ ቅጥረኞች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከአመት በላይ በከባባ ውስጥ ባስገባት ምዕራባዊቷ ከተማ ኤል ፋሽርን ለመቆጣጠር በሚደረግ ውጊያ ተሳትፈዋል ተብሏል።

እነዚህ ቅጥረኞች በአገሪቱ በሚገኝ የግል የጸጥታ ኤጀንሲ መቀጠራቸውን የኮሎምቢያው የዜና ድረገጽ ላ ሲላ ቫቺያ ቀደም ሲል ዘግቧል።

ከቀናት በፊት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የቅጥረኞቹን ስምሪት ጋር በተያያዘ እያመቻቸች መሆኑን ከአንድ መረጃ አሹላኪ ጋር የተደረገ በተደረገ ቃለ ምልልስ ይኸው ድረ ገጽ አስነብቧል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የገንዘብ ድጋፍ ከኮሎምቢያ እና ከአንዳንድ አገራት የመጡ ቅጥረኞችን ተሳትፎ የሚያረጋግጡ ሰነዶችን እና ማስረጃዎችን መንግሥት መያዙን ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።