ኤል ፋሽር ከተማን ከበባ ውስጥ ያስገባው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል ተከሰሰ

የተፈናቀሉ ሱዳናዊት ሴት

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በዳርፉር የምትገኘውን ኤል ፋሽር ከተማን ከበባ ውስጥ በማስገባት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ፈጽሟል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪዎች አስታወቁ።

ተፋላሚው ኃይል ከበባ ውስጥ ባስገባት ከተማ "ግድያ፣ ማሰቃየት፣ ባርነት፣ መድፈር፣ ወሲባዊ ባርነት፣ አስገድዶ ማፈናቀል፣ በዘር፣ በጾታዊ እና በፖለቲካዊ ምክንያቶች ጥቃቶችን ማድረስ" እየፈጸመ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምርመራ ሪፖርት ያሳያል።

ሪፖርቱ በተጨማሪም በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና በሱዳን ጦር ተፈጽመዋል የተባሉ የጦር ወንጀሎችን ሰፋ ያለ ማስረጃዎችን ዋቢ አድርጎ አካቷል።

ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በደም አፋሳሹ የሱዳን ጦርነት ምንም አይነት የጦር ወንጀል አልፈጸምንም ሲሉ ከዚህ ቀደም አስተባብለዋል።

ተፋላሚዎቹ ሰላማዊ ዜጎችን በተለያዩ መንገዶች እና ሆን ብለው ስልታዊ ጥቃት አድርሰዋል ሲል ይህ ሪፖርት ከሷል።

"ሁለቱም ወገኖች ሆን ብለው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ፣ እስራት፣ ስቃይ፣ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ምግብ እና ህክምና መከልከልን ጨምሮ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል" ሲሉ ይህንን ሪፖርት ያወጣው የተመድ የመርማሪዎች ቡድን ሊቀ መንበር መሐመድ ቻንዴ ኦትማን ገልጸዋል።

"እነዚህ ጥሰቶች በአጋጣሚ የደረሱ አሳዛኝ ክስተቶች ሳይሆኑ እንደ ስልት የተጠቀሙባቸው የጦር ወንጀሎች ናቸው" ሲሉ አክለዋል።

በተለይም የሱዳን ፈጥሮ ደራሽ ኃይል በከበባ ውስጥ ባስገባት ኤል ፋሽር ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም አንድን ህዝብ የማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው ሲል ሪፖርቱ አትቷል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሚያዝያ ወር በኤል ፋሽር አቅራቢያ የሚገኘውን የዛምዛም የተፈናቃዮችን ካምፕ በመውረር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን ከመጠለያቸው እንዲወጡ አስገድደዋቸዋል።

በተፈናቃዮቹ መጠለያ ጣቢያ ያለው ሁኔታ በጣም የከፋ ሲሆን ረሃብ መከሰቱም ታውጇል።

በዳርፉር ግዛት የምትገኘው የኤል ፋሽር ከተማ ከአንድ ዓመት በላይ በከበባ ላይ ትገኛለች።

የአሜሪካ መንግሥት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር አረብ ባልሆኑ ህዝቦች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ሲል ከሷል።

ቡድኑ በበኩሉ ጥሰቱን አስተባብሎ የአካባቢው ሚሊሻዎችን ተጠያቂ አድርጓል።

አሜሪካ የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም እና በሰላማዊ ዜጎች ግድያ ማዕቀብ ጥላባቸዋለች።

ጦሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀ ደም አፋሳሽ ጦርነት ላይ ይገኛሉ።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በከተማዋ ላይ የሚያደርገውን ጦርነት አፋፍሞ መቀጠሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ቀደም ሲል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ 12 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

ከ4.5 ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞች በአብዛኛው ሴቶች እና ህጻናት ወደ ጎረቤት አገራት ተፈናቅለዋል።