ሔሜቲ የጎረቤት አገራት ጄቶች እና አየር ማረፊያዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠነቀቁ

ጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ)

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) ከጎረቤት አገሮች የሚነሱ የጦር ጀቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ላይ ኃይላቸው ጥቃት እንደሚያደርስ አስጠነቀቁ።

የሱዳንን ጦር የሚደግፉ የቀጣናው አገራት አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይም ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ገልጸዋል።

ሠራዊታቸው ላይ ጥቃት ለማድረስ ከሱዳን ጎረቤት አገሮች የሚነሱ የጦር ጀቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንደሚመቱ ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።

"ቁሳቁስ ለማድረስ፣ ጥቃት ለመፈጸም ወይም ለመግደል ከየትኛውም ጎረቤት አገር የሚነሳ የትኛውም አውሮፕላን ያሰጋናል" ብለዋል።

የቀጣናው አገራት አውሮፕላን ማረፊያዎች በሱዳን ለሚደርስ ጥቃት መነሻ ከሆኑ የጦር አውድማ እንደሚሆኑ ሔሜቲ ዝተዋል።

ማስጠንቀቂያቸው በተለይ ግብፅ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ቢታመንም፣ ከዚህ ቀደም የወጡ አንዳንድ ሪፖርቶች የሱዳን መንግሥት የጦር አውሮፕላኖቹን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጥቃት ለመጠበቅ ሲል ከፖርት ሱዳን ወደ ኤርትራዋ መዲና አሥመራ ማዘዋወሩን አመልክተው ነበር።

ግብፅ የሱዳን ጦርን በማሠልጠን እና ሰው አልባ አውሮፕላን በማቅረብ በጦርነቱ መሳተፏ ሲገለጽ ቆይቷል።

የሱዳን ጦር "የዘር ጭፍጨፋ" ፈጽሟል ሲሉም ሔሜቲ ከሰዋል። ጦሩ በዳርፉር እና ኮርዶፋን ግዛቶች ጎሳ ተኮር ጥቃት በመፈም "ሰዎችን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ ነው" ሲሉም አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቅርቡ በኮርዶፋን ግዛት በደረሰ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የጎሳ መሪ ተገድለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እርስ በእርሳቸው ሲካሰሱ ቆይተዋል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ባለፉት ጥቂት ቀናት በጦሩ በተያዙ አካባቢዎች በተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ፈጽሟል። ጥቃቶቹ ወታደራዊ መቀመጫዎች እና ንጹኃን ዜጎችንም ዒላማ ያደረጉ ነበሩ።

ውጊያው ከመዲናዋ ካርቱም አልፎ በዳርፉር እና ኮርዶፋን ግዛቶች ተባብሶ ቀጥሏል።

በሌላ በኩል፤ የሱዳን ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የደኅንነት ፍተሻ ካደረ በኋላ አውሮፕላን ማረፊያውን ለበረራ ክፍት አድርጓል።

አውሮፕላን ማረፊያው ከሦስት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ በረራ ትናንት አስተናግዷል።

ሆኖም ግን ባለፉት 24 ሰዓታት በአካባቢው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት እየደረሰ ነው።

አውሮፕላን ማረፊያው በእርስ በእርስ ጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መሠረተ ልማቶች መካከል ይገኝበታል።

የሱዳን ጦር የካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ ለበረራ ክፍት ከመደረጉ ከሰዓታት በፊት ጥቃቶችን በተሳካ ሁኔታ መመከቱን አስታውቋል።

የሱዳን ጦር የካርቱምን የተወሰኑ አካባቢዎች መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ በመጀመሪያ ደረጃ ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ አውሮፕላን ማረፊያውን ለበረራ ክፍት ማድረግ ነው።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ያደረሰው ጥቃት ግን አሁን ላይ በካርቱም ሕይወት እንደቀደመው የመመለስ ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ ያሳያል።

ሁለቱ ተገዳዳሪ ኃይሎች ካርቱምን ለመቆጣጠር ውጊያዎች አካሂደዋል።

የሱዳን ጦር መሪ ሌተናንት ጀነራል አብደል ፋታሕ አል-ቡርሐን ከዳርፉር 24 ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በሱዳን ቀጣይ እጣ ፈንታ ውስጥ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ምንም ሚና አይኖረውም" ብለዋል።

የሱዳን ጦር ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን እንደሚረታ የገለጹት አል-ቡርሐን፣ "ሚሊሻዎች ወይም ሌሎችም የአማጺያን ደጋፊዎች በሱዳን ቦታ አይኖራቸውም" ብለዋል።

አል-ቡርሐን ይሄንን ያሉት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነው።

አውሮፕላን ማረፊያው ከተከፈተ በኋላ ከፖርት ሱዳን የተነሳ 180 ሰዎችን ያሳፈረ አውሮፕላን በሰላም አርፏል።

በመጀመሪያው በረራ ከነበሩ ተሳፋሪዎች መካከል አል-ቡርሐን ይገኙበታል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በ24 ሰዓታት ውስጥ ሁለት የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ፈጽሟል።

በካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ዛሬ ጠዋት ለሦስተኛ ጊዜ ጥቃት ተፈጽሟል።

በቀጣይ አውሮፕላን ማረፊያው በረራዎችን ስለማስተናገዱ ግልጽ አይደለም።

አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች ለማደራደር ሙከራቸውን ቀጥለዋል።

ትናንት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በደቡብ ምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የኃይል ማመንጫ ተቋማት ላይ ጥቃት አድርሷል።

ሱዳን ትሪብዩን እንደዘገበው በሰነር እና በዳማዚን ከተሞች ጥቃቱ ተፈጽሟል።

በሰነር ከተማ ዋነኛ ግድብ አቅራቢያ "አጥፍቶ ጠፊ ሰው አልባ አውሮፕላን ፈንድቷል" ሲሉ አንድ የዐይን እማኝ ተናግረዋል።

በዳማዚን የኃይል ማመንጫ በደረሰው ጥቃት ሳቢያ "ከተማዋ ጨልማለች" ሲሉም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በስደተኞች፣ በሕጻናት፣ በተፈናቃዮች እና በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ዙሪያ የሚሠሩ አራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሱዳን ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

የሱዳን ጦር ካርቱምን መልሶ መቆጣጠሩ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፤ መሠረተ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን ገልጸዋል።

የተመድ ተቋማት በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በዳርፉር እና ኮርዶፋን ግዛቶች የቀጠለው ውጊያ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት በምግብ እጥረት ሳቢያ ለሞት መጋለጣቸውን የተቋማቱ መግለጫ ይጠቁማል።

ከፍተኛ ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባም ጠይቀዋል።

ተቋማቱ የሚደረግላቸው ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት ነፍስ አድን እርዳታ የሚሰጡበት አቅም እንደተገደበም አክለዋል።