ሐማስ የታጋቾችን አስከሬን የያዙ ናቸው የተባሉ ሦስት የሬሳ ሳጥኖችን አስረከበ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
የታጋቾችን አስክሬን የያዙ ናቸው የተባሉ ሦስት የሬሳ ሳጥኖችን ሐማስ እንዳስረከበ የእስራኤል መከላከያ አስታወቀ።
እስራኤል በቀይ መስቀል አማካኝነት የሬሳ ሳጥኖቹን ተረክባለች። የአስከሬን ምርመራ እንደሚካሄድም ተገልጿል።
አስከሬኖቹ ታግተው የነበሩ እስራኤላውያን መሆናቸው ከተረጋገጠ በጋዛ የሚቀሩት የስምንት እስራኤላውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎች አስከሬኖች ብቻ ይሆናሉ።
በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ዕቅድ የመጀመሪያ ዙር መሠረት ሐማስ 20 በሕይወት ያሉ ታጋቾችን እና የ28 ታጋቾችን አስከሬን ለመልቀቅ ተስማምቷል።
እስራኤል ሐማስ አስከሬኖችን ለመመለስ ዘግይቷል ብትልም ሐማስ በበኩሉ ከፍርስራሽ ሥር አስከሬኖችን ማውጣት ጊዜ እንደሚወስድ አስታውቋል።
የሐማስ ታጣቂ ክንፍ አል-ቃሲም ብርጌድ እንዳለው አስከሬኖቹ የተገኙት በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ ዋሻ አቅራቢያ ነው።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኤክስ ገጻቸው "ለታጋቾች ቤተሰቦች መረጃ ሰጥተናል። በዚህ ከባድ ጊዜ እንደግፋቸዋለን። ሁሉም ታጋቾች እስከሚመለሱ ጥረታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
የታጋቾች ቤተሰቦች ማኅበር የሁሉም ታጋቾች አስከሬን ተገኝቶ በአፋጣኝ እንዲመለስ ኔታንያሁ ላይ ጫና እያሳደረ ነው።
ማኅበሩ ባወጣው መግለጫ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆራጥነት ትዕዛዝ ሰጥተው የሁሉንም ታጋቾች አስከሬን ያስመልሱልን" ሲል ጠይቋል።
ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁሙን በመጣስ እርስ በእርስ ይካሰሳሉ።
ትናንት እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ባደረሰችው የአየር ጥቃት አንድ ሰው መገደሉ ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ዒላማ ያደረገው "ለወታደሮች ስጋት የሆነን" ታጣቂ መሆኑን አስታውቋል።
በትራምፕ የሰላም ዕቅድ መሠረት ሐማስ ሁሉንም በሕይወት ያሉ ታጋቾች ሲለቅ፤ እስራኤል 250 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እና 1,718 ታጋቾችን ፈትታለች።
ሐማስ የ15 እስራኤላውያን ታጋቾችን አስከሬን ሲያስረክብ፤ እስራኤል የ225 ፍልስጤማውያንን አስከሬን መልሳለች።
አስከሬናቸው በጋዛ ከነበረ 11 ሰዎች መካከል አንድ ታንዛኒያዊ እና አንድ ታይላንዳዊ ይገኙበታል።
ሐማስ ከሁለት ዓመት በፊት ባደረሰው ጥቃት 1,200 ገደማ ሰዎች ተገድለው፤ 251 ሰዎች ታግተዋል። እስራኤል በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከ68,500 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተዘግቧል።















