ግብፅ እና ቀይ መስቀል በጋዛ የታጋቾች አስከሬን ፍለጋ ላይ መሳተፍ ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ከግብፅ እና ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የተውጣጡ ቡድኖች በመስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ ታግተወ በጋዛ ሕይወታቸው ያለፈ ታጋቾችን አስከሬን እንዲፈልጉ ፈቃድ ተሰጣቸው።
የእስራኤል መንግሥት እንዳለው ቡድኖቹ በጋዛ "ቢጫ መስመር" ተብሎ በተከለለው እና የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሚቆጣጠረው አካባቢ አስከሬኖቹን እንዲፈልጉ ተፈቅዶላቸዋል።
እሁድ ዕለት የእስራኤል ጦር በሚቆጣጠረው የጋዛ አካባቢ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ጋር በመሆን ፍለጋውን እንዲያግዙ የሐማስ አባላት እንዲገቡ አንደተፈቀደላቸው የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
እስካሁን ድረስ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ሐማስ ከ28 የታጋቾች አስከሬን ማስረከብ የቻለው የ15ቱን ብቻ ነው።
አሜሪካ ባሸማገለችው በዚህ የተኩስ አቁም ሐማስ የታጋቾቹን አስከሬን ሙሉ በሙሉ ማስረከብ ይጠበቅበታል።
ቡድኑ ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን አክሎ ገልጿል።
ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ የታጋቾችን አስከሬን "በፍጥነት" እንዲመልስ አለበለዚያ ግን "በዚህ ታላቅ ሰላም ላይ የተሳተፉ ሌሎች አገራት እርምጃ መውሰድ ይጀምራሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ የግብፃውያን ቡድን ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ጋር በመሆን የታጋቾችን አስከሬን እንዲፈልግ እንደተፈቀደለት ተናግረዋል።
ከ"ቢጫው መስመር" ባሻገር ባሉ አካባቢዎች የአስከሬን ፈለጋውን በቁፋሮ ማሽኖች (ኤክስካቬተር) እና በከባድ መኪኖች በመታገዝ እንደሚያካሄዱም ጨምረው አስታውቋል።
"ቢጫ መስመር" ተብለው የተቀመጡት ድንበር የሚገኘው የእስራኤል ጦር በመጀመሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ለቅቆ የወጣባቸው እና በሰሜን፣ በደቡብ እና በምሥራቅ ጋዛ የሚገኙ አካባቢዎች ናቸው።
እስራኤል እስካሁን ድረስ እንዲህ ዓይነት የፍለጋ ቡድን ወደ አካባቢው እንዲገባ አልፈቀደችም።
ትራምፕ ባሸማገሉት የጋዛ የሰላም ዕቅድ ላይ ከኳታር እና ከቱርክ ጋር ፈራሚ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ግብፅ ናት።
ይህ የፍለጋ ዜና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በተገቢው መንገድ ለመቅበር እና ሐዘናቸውን ለመወጣት በሚፈልጉ ቤተሰቦች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል።
ዓለም አቀፉ ቀይመስቀል ድርጅት በታጋቾች መመለስ ዙሪያ በሰፊው እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል።
ሐማስ በሕይወት ያሉትን ታጋቾችንም ሆነ የሞቱትን በቀጥታ ለእስራኤል መከላከያ ኃይል አያስረክብም።
በቅድሚያ ለዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት ካስረከበ በኋላ ለእስራኤል መካለከያ ኃይል እንዲያስተላልፍ ያደርጋል።
ነገር ግን የግብፅ ፍለጋ ቡድን በጋዛ ሰርጥ መሰማራት አዲስ ነው።
የእስራኤል ጦር ለሁለት ዓመት ያህል አካባቢውን በከባድ መሳሪያ ከደበደበ በኋላ 84 በመቶ የጋዛ አካባቢ ወደ ፍርስራሽነት መለወጡ የመንግሥታቱ ድርጅት ግምት ያሳያል።
ሐማስ የታጋቾቹን አስከሬን ለማግኘት የቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ገልጾ ነገር ግን በእስራኤል ጦር ጥቃት ወደ ፍርስራሽነት ከተቀየሩት ሕንጻዎች ስር ማውጣት አስቸጋሪ እንዳደረገበት አስታውቋል።
አሁን ግን ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር በትብብር እየሠራ ነው።
እሁድ ዕለት የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ሐማስ አስከሬኖቹ የት እንደነበሩ ያውቃል ብለዋል።
"ሐማስ በቂ ጥረት ቢያደርግ ኖሮ የታጋቾቻችንን አስከሬን ማውጣት ይችል ነበር" ሲሉ ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ቅዳሜ ዕለት የታጋቾቹ አስከሬን በፍጥነት የማይመለስ ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቀቀዋል።
"የተወሰኑት አስከሬኖችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን ሌሎች አሁን መመለስ ይቻላል እና በሆነ ምክንያት ያንን ማድረግ አልተቻለም። ምናልባት ትጥቅ ከመፍታት ጋር ይያያዝ ይሆናል" ብለዋል።
ትራምፕ አክለውም "በቀጣዮቹ 48 ሰዓታት የሚያደርጉትን እስቲ እንይ። በቅርበት እየተከታተልኳቸው ነው" ብለዋል።
እሁድ ዕለት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው በትራምፕ ዕቅድ መሠረት በጋዛ ያለውን የተኩስ አቁም ለማስቀጠል የትኛው የዓለም አቀፍ ኃይል እንዲሰማራ እንደምትወስን ተናግረዋል።
"ደኅንነታችን በእኛው ቁጥጥር ስር ነው፤ ዓለም አቀፍ ኃይሎችን በተመለከተም በእስራኤል ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን ኃይሎች እንደምትወስን ግልፅ አድርገናል፤ አሁንም ሆነ ወደፊት የምንሰራው በዚህ መንገድ ነው" ሲሉ የካቢኔ ስብሰባቸውን ሲጀመሩ ተናግረዋል።
አርብ ዕለት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ "በርካታ አገራት" የሚሰማራው ጦር አካል ለመሆን መጠየቃቸውን ነገር ግን በሚሳተፉት አገራት ላይ እስራኤል ፈቃደኛ መሆን እንዳለባት ተናግረው ነበር።
ይህ የቱርክ ጦር ተሳትፎን ለማመልከት የቀረበ ሲሆን፣ እስራኤል ግን ፈቃደኛ አለመሆኗን አስቀድማ አሳውቃለች።
ነገር ግን ይህ የሰላም አስከባሪ ኃይል ያለ ሐማስ ስምምነት እንዴት በአካባቢው እንደሚሰማራ ግልጽ አይደለም።
እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ያህሉን ካገተ በኋላ ነው።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ 68,519 በጋዛ ሰርጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።















