የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የእስራኤል ፓርላማ ውሳኔን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የእስራኤል ፓርላማ በወረራ የያዘችውን ዌስት ባንክን ለመጠቅለል ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ዋሽንግተን የጋዛ ግጭት ለማስቆም ያቀረበችውን ዕቅድ አደጋ ላይ ይጥላል በማለት አስጠነቀቁ።
ማርኮ ሩቢዮ የተኩስ አቁሙን በሚመለከት ለመነጋገር ወደ እስራኤል ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት "አሁን የምንደግፈው ነገር አይደለም" ሲሉ የፓርላማውን ውሳኔ እንደማይደግፉ ተናግረዋል።
የእስራኤል የቀኝ አክራሪ ፖለቲከኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለማሸማቀቅ በሚመስል መልኩ ዌስት ባንክን የመጠቅለል ሥልጣን ለሚሰጠው ረቂቅ የመጀመሪያ ይሁንታ በመስጠት ተምሳሌታዊ እርምጃ ወስደዋል።
ፍልስጤማውያን እስራኤል እአአ ከ1967 ጀምሮ በወረራ የያዘችውን ዌስት ባንክን የነፃ አገራቸው አካል መሆኑን ያምናሉ።
ባለፈው ዓመት የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት፣ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የእስራኤል ወረራ ሕገወጥ ነው ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ኔታንያሁ ከዚህ ቀደም የዌስት ባንክን መሬት ጠቅልሎ በእስራኤል ስር ለማድረግ እንደሚፈልጉ ሲናገሩ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ዋነኛ አጋራቸውን አሜሪካን እና ከአስርት ዓመታት ጠላትነት በኋላ ከአገራቸው ጋር ግንኙነት ከፈጠሩት የአረብ አገራት የመገለል ስጋት ስላለባቸው እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበዋል።
በኔታንያሁ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ አክራሪ ብሔርተኞች እስራኤል ዌስት ባንክን በቀጥታ ጠቅልላ በግዛቷ ውስጥ እንድታስገባ ደጋግመው ጠይቀዋል።
ይህንን የሚደግፈው ሕግ ከመንግሥት ውጭ ባሉ የፓርላማ አባላት ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
ሕጉ በከፍተኛ የድጋፍ ድምጽ የጸደቀ ሲሆን 120 መቀመጫዎች ባሉት ፓርላማ ሲቀርብ አብላጫውን ድጋፍ ማግኘቱ ግልፅ አይደለም።
እሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያዘገዩት ወይም ውድቅ ሊያደርጉ የሚችሉባቸው መንገዶች አሉ።
የፍልስጤም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል በፍልስጤም ምድር ላይ ምንም ዓይነት ሉዓላዊ ሥልጣን አይኖራትም በማለት የምክር ቤቱን እርምጃ አውግዘዋል።
እስራኤል በዌስት ባንክ እና በምሥራቅ እየሩሳሌም በወረራ በያዘቻቸው ስፍራዎች 700,000 አይሁዶች የሚኖሩበትን 160 የሚጠጉ ሰፈሮችን ገንብታለች። 3.3 ሚሊዮን የሚገመቱ ፍልስጤማውያን አብረዋቸው ይኖራሉ።
ሰፈራዎቹ ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሕግ ሕገ-ወጥ መሆናቸው ተገልጿል።
ሩቢዮ ወደ እስራኤል ለመጓዝ አይሮፕላን እየተሳፈሩ እንደተናገሩት አሜሪካ እስራኤል ዌስት ባንክን ወደ ግዛቷ ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት እንደማትደግፍ በመግለጽ፣ ለጋዛ ሰላም ስምምነት "አፍራሽ" እና "አስጊ" እንደሚሆን ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ባለ 20 ነጥብ የጋዛ የሰላም ዕቅድ ሁለተኛው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ንግግሮችን ለማስጀመር ግፊት እያደረገ ሲሆን ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና ሁለት ልዩ ልዑካን ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ እስራኤል አቅንተዋል።
የተኩስ አቁም፣ የእስራኤል ጦር በከፊል መውጣት እና የእርዳታ ፍሰትን የሚያካትተው የመጀመርያው ምዕራፍ የሰላም ዕቅድ ከአስር ቀን በፊት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
እስራኤል እና ሐማስ እሁድ ዕለት በመካከላቸው በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ አንዱ ሌላኛውን ስምምነቱን ጥሷል በሚል እርስ በእርሳቸው ሲወነጃጀሉ ቆይተዋል።
ሩቢዮ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማስቀጠል ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ቫንስ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ተስፋን አሳይተዋል።
"በየዕለቱ ተግዳሮቶች ይኖራሉ፤ ነገር ግን እኔ እንደማስበው ከታቀደው በላይ እያደረግን ነው፤ እናም የሳምንቱ መጨረሻ ላይ የነበረውን ማለፋችን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።"
ሁለተኛው የሰላም ዕቅድ በጋዛ ጊዜያዊ መንግሥትን ማቋቋም፣ ዓለም አቀፍ የሚያረጋጋ ኃይል ማሰማራት፣ የእስራኤል ወታደሮችን ማስወጣት እና ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት ያካትታል።
የጋዛ ጦርነት በመስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ በደቡብ እስራኤል ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎች ከገደለ እና 251 ሰዎች አግቶ ከወሰደ በኋላ የተቀሰቀሰ ነው።
ከዚያ ወዲህ የእስራኤል ጦር በጋዛ መውሰድ በጀመረው እርምጃ ከ68,000 የሚበልጡ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ሲል የሐማስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።















