እስራኤል በጋዛ ላይ የአየር ድብደባ ከፈጸመች በኋላ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነቱ መመለሷን አስታወቀች

በእስራኤል ድብደባ የወደሙ ሕንጻዎች በከፊል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የእስራኤል ጦር እሁድ ዕለት ሐማስ ስምምነቱን "በግልጽ ጥሷል" በማለት የአየር ድብደባ ከፈጸመ በኋላ በጋዛ የተኩስ አቁሙን ተግባራዊ ማድረግ ዳግም እንደሚጀምር አስታወቀ።

በደቡባዊ ጋዛ የአየር ድብደባው የተካሄደው በራፋህ ወደሚገኙ ወታደሮቹ "አሸባሪዎች ፀረ ታንክ ሚሳዔል እና ጥይት ተኩሰው" ሁለት ወታደሮችን ገድለዋል ካለ በኋላ ነው።

ሐማስ ግን በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ስለተፈጠረ ግጭት ምንም እውቀት እንደሌለው አስታውቋል።

እስራኤል እሁድ ምሽት ላይ በጋዛ የሚገኙ የሐማስ ዒላማዎችን መደብደቧን ያስታወቀች ሲሆን፣ በጋዛ የሚገኙ የሆስፒታል ምንጮች ደግሞ በጥቃቱ 44 ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።

ሐማስ ለተኩስ አቁሙ ተግባራዊነት አሁንም ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቆ፣ እስራኤል ግን ጥሰት እየፈጸመች ነው በማለት እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች የተኩስ አቁሙን "ሙሉ በሙሉ ወደ መፍረስ የሚገፉ ናቸው" ሲል አስጠንቅቋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል እሁድ ማታ "የተኩስ አቁሙን ዳግም ማክበር መጀመሩን" ያስታወቀ ሲሆን፣ ስምምነቱን እንደሚያከብር ነገር ግን "ለየትኛውም ጥሰት ከበድ ያለ ምላሽ እንደሚሰጥ" አስታውቋል።

መግለጫው ቀደም ሲል ጦሩ ወደ ጋዛ የሚገቡ እርዳታዎችን ለማስቆም ያወጣው መግለጫ ተቀልብሶ ስለመሆኑ በቀጥታ የገለፀው ነገር የለም።

ከአስር ቀን በፊት በአሜሪካ አደራዳሪነት የተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ጦርነቱን ወዲያውኑ ማስቆም ችሎ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ በተጨማሪ የእስራኤል ወታደሮች በከፊል ወደ ሰሜን፣ ምሥራቅ እና ደቡብ ጋዛ ቢጫ መስመር ሲሉ ወደ ከለሉት አካባቢ የወጡ ሲሆን፣ ወደ ጋዛ በሚገባው ሰብዓዊ እርዳታ መጠን ላይም መጨመር ታይቶ ነበር።

ሐማስ በሕይወት ያሉ ታጋቾችን በሙሉ እንዲሁም ከሟቾቹ ውስጥ የ12ቱን አስክሬን ለእስራኤል አስረክቧል።

እስራኤል በበኩሏ በእስር ቤቷ ውስጥ የነበሩ 250 የፍልስጤም እስረኞችን እና ከጋዛ ሰብስባ ያጎረቻቸውን 1,718 ፍልስጤማውያንን የለቀቀች ሲሆን የ15 ፍልስጤማውያን አስከሬን መልሳለች።

ይህ የተኩስ አቁም ስምምነትን ግን እሁድ ዕለት ፈተና ላይ ወድቋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዓለም መሪዎችን ባለፈው ሳምንት በግብፅ "በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም" በሚል መሪ ቃል ስር ካሰባሰቡ በኋላ የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ ጋዛ ውስጥ ስጋት ተፈጥሯል።

አሁን ይህ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲቀጥል የአሜሪካ ግፊት ያስፈልጋል።

ለዚያም ይመስላል የትራምፕ ልዩ ልዑክ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር በቅርቡ ወደ እስራኤል ያቀናሉ ተብሏል።

ቀደም ሲል እሁድ ዕለት የእስራኤል ጦር "በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ አካባቢ የአሸባሪዎችን መሠረተ ልማት ለማፍረስ ወደሚንቀሳቀሱ የእስራኤል ወታደሮች ፀረ ታንክ ሚሳኤል እና ተኩስ ከፍተዋል" ሲል ወንጅሏል።

"በምላሹ የመከላከያ ሠራዊቱ በአካባቢው ያለውን ስጋት ለማስወገድ እና ለሽብር ተግባር የሚውሉትን መተላለፊያ ዋሻዎች እና ወታደራዊ መዋቅሮችን ለማፍረስ በአካባቢው ድብደባ ማድረግ ጀምሯል።"

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ በራፋህ አካባቢ ስለተፈጠረ ማንኛውም ግጭት የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በመገለጽ አስተባብሏል።

በመግለጫው አል-ቃሳም ብርጌድ "ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ጦርነቱ ዳግም ካገረሸበት ጊዜ ጀምሮ ከቀሪ ቡድኖቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ተቋርጧል።

"ስለዚህ በእነዚያ አካባቢዎች ከሚፈጸሙት ተግባራት ጋር ምንም ግንኙነት የለንም፤ እናም እዚያ ካሉ ተዋጊዎቻችን ጋር አንዳቸውም በሕይወት ካሉ መገናኘት አንችልም።"

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ሁለት ወታደሮች "በራፋህ ውስጥ በደረሰው አሳዛኝ ክስተት" ተገድለዋል ብሏል።

ጽህፈት ቤቱ ቀደም ሲል ኔታንያሁ ከመከላከያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው "በጋዛ ሰርጥ የአሸባሪዎች ዒላማዎች ላይ ከባድ እርምጃ እንዲወስዱ" መመሪያ ሰጥቷቸዋል ብሏል።

በአቅራቢያው ከሚገኘው የአውሮፓ ሆስፒታል በስተደቡብ የሚኖሩ ነዋሪዎች ጥቃቱ በከባድ መሳሪያ የታጀበ መሆኑን ገልጸው በራፋህ አንዳንድ ክፍሎች የደረሱ ፍንዳታዎች ከባድ እንደነበሩ ገልጸዋል።

በእሁዱ ጥቃት ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሲያለቅሱ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

በምሥራቅ ኻን ዮኒስ "የእሳት ቀለበት" ሲሉ በተለምዶ በሚጠሩት አካባቢ ቢያንስ 12 የአየር ድብደባዎች መፈፀማቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

ጥቃቱ በከተማዋ ላይ ከፍተኛ ጭስ ያስነሳ ሲሆን፣ በአቅራቢያው በተጠለሉ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ላይ ስጋትን ፈጥሯል።

በማዕከላዊ ጋዛ፣ በአል-አቅሳ ሆስፒታል የሚሠሩ አንድ ዶክተር እንዳሉት በአል-ዛዋይዳ ድንኳን ውስጥ በሚገኝ ትንሽ የባሕር ዳርቻ ካፌ እና በኑሴይራት የሚገኝ ሕንፃ ላይ ሁለት የተለያዩ ጥቃቶች ከደረሱ በኋላ ዘጠኝ አስከሬኖች ወደ ሆስፒታላቸው መጥተዋል።

የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በባሕር ዳርቻው ላይ ግዙፍ የእሳት ኳሶች ከታዩ በኋላ ከባድ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን፣ ወዲያው አምቡላንስ እና የሕይወት አድን ሠራተኞች ወደ ስፍራው ተሰማርተዋል።

በአል-ዛዋይዳ ጥቃት ከተገደሉት መካከል ስድስቱ የአል-ቃሳም ብርጌድ አባላት መሆናቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልፀዋል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ በጃባሊያ የሐማስ ጦር አዛዥ የሆነው ያህያ አል-ማብሁህ ሲሆን ሞቱ ቡድኑ የተኩስ አቁሙን ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ካጋጠመው ከፍተኛ ኪሳራ መካከል ሆኖ ተመዝግቧል።

በኑሴይራት የሚገኘው የአል-አውዳ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ፣ የእስራኤል የአየር ጥቃት ተፈናቃዮችን ባስጠለለ ትምህርት ቤት ላይ ከደረሰ በኋላ አራት አስከሬኖች ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ዶክተሩ አክለውም ከተጎዱት መካከል በርካታ ሴቶች እና ሕጻናት ይገኙበታል ብለዋል።

በትራምፕ አደራዳሪነት በተካሄደው ባለ 20 ነጥብ የተኩስ አቁም ስምምነት ሐማስ ከአሁን በኋላ በእስራኤል ላይ ስጋት ላለመፍጠር መሳሪያውን ማስረከብ አለበት።

ሐማስ በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው የጋዛ ሰርጥ ክፍል ውስጥ ያለ ከልካይ እየተንቀሳቀሰ ነው ያለውን የወንጀለኛ ቡድን ዘራፊዎችን በማስታጠቅ እስራኤልን ከሷል።

ግዛቱን ለ18 ዓመታት ያስተዳደረው ሐማስ በእስራኤል ጦር ድጋፍ መሳሪያ ከታጠቁት አቡ ሻባብ ከተባሉ የታጣቂ ቡድኖች ፈተና ገጥሞታል።

የእሁድ ጠዋቱን ክስተት የሚያውቅ የአካባቢው ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጸው የሐማስ ተዋጊዎች ከአቡ ሸባብ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን ላይ የእስራአል ጦር በሚቆጣጠረው ስፍራ በደቡብ ምሥራቅ ራፋህ ጥቃት አድርሰዋል።

ታጣቂዎቹ በድንገት በታንክ ላይ መተኮሳቸውን እና የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን የገለጹት የዓይን እማኙ ወዲያው የእስራኤል አየር ኃይል አካባቢውን መደብደብ ጀምሯል።

አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣን ሐማስ ከቢጫው መስመር ጀርባ በሚገኙ ወታደሮቻችን ላይ የተኮሰባቸው ቢያንስ ሦስት አጋጣሚዎች አሉ ሲሉ ተናግረዋል፤ ጥቃቶች "ከየትኛውም የውስጥ ውጊያ ጋር የተገናኙ አይደሉም" ሲሉ አክለዋል።

የእስራኤል ጦር አሁንም ከ50 በመቶ በላይ ጋዛን ተቆጣጥሮ ይገኛል።

በራፋህ የተካሄደው ጥቃት ዩናይትድ ስቴትስ ሐማስ በጋዛ በሰላማዊ ሰዎች ላይ "ተጨባጭ" ጥቃት ለማድረስ ማቀዱን የሚገልጹ "አሳማኝ መረጃዎች" እንዳሏት ከተናገረች ከሰዓታት በኋላ ሲሆን፣ ይህም የተኩስ አቁም ስምምነትን "በቀጥተኛ እና በከባድ" ሁኔታ መጣስ ነው ብላ ነበር።

በፍልስጤማውያን ላይ የታቀደ ጥቃት "በአደራዳሪዎች ጥረቶች የተገኘውን ከፍተኛ ውጤት ያዳክማል" ሲል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ ተናግሯል።

ሐማስ ሊፈፀም የታቀደ ማንኛውንም ጥቃት የለም ሲል በጥብቅ አስተባብሏል።

ከሳምንት በፊት በጋዛ ከተማ የሐማስ የፀጥታ ኃይሎች እና የታጠቁ የዱግሙሽ ቤተሰብ አባላት መካከል ከባድ ግጭት ተቀስቅሶ 27 ሰዎች ተገድለዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሐማስን በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ግድያ በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "ሐማስ በጋዛ ሰዎችን መግደሉን ከቀጠለ፣ ይህ ስምምነት አልነበረም። ሄዶ ከመግደል ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም" ብለዋል።

በኋላ ላይ አሜሪካ ጦሯን ወደ አካባቢው እንደማትልክ ግልጽ አድርገዋል።

ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በደቡብ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ 1,200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደለ እና ሌሎች 251 ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ከፍተኛ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለጸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ 68,000 ሰዎች በእስራኤል ጥቃት የተነሳ ተገድለዋል።