የተመድ ባለሥልጣን እስራኤል ወደ ጋዛ የሚያስገቡ ተጨማሪ መንገዶችን እንድትከፍት አሳሰቡ

ውሃ ለመቅዳት ጀሪካን ይዘው በፍርስራሽ መሃል የሚራመዱ ሴት እና ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባውን እርዳታ ልትገድብ እንደምትችል ማስጠንቀቋን ተከትሎ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች የምግብ ፍጆታዎችን እያከማቹ ነው።

እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባውን እርዳታ ለመጨመር ተጨማሪ መንገዶችን እንድትከፍት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ አሳሰቡ።

ኃላፊው ይህን ያሉት እስራኤል፣ ሐማስ ሕይወታቸው ያለፉ ታጋቾችን አስክሬን ቶሎ የማይለቅ ከሆነ ወደ ጋዛ የሚገባውን አቅርቦት ልትገድብ እንደምትችል ካስጠነቀቀች በኋላ ነው።

የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊው ቶም ፍሌቸር በአሜሪካ አሸማጋይነት የተደረሰውን ወሳኝ ስምምነት እንዳይደናቀፍ ሁለቱ ወገኖች በቅርቡ የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የታጋቾች አስክሬን የሚመለስበት ጊዜ መዘግየቱ እስራኤልን ያስቆጣ ሲሆን ወደ ጋዛ የሚያስገባውና በግብፅ እና በደቡባዊ ጋዛ መካከል ያለው የራፋህ መንገድ ረቡዕ ዕለት ተዘግቷል።

በዚህም የተደረሰው ስምምነት ላይዘልቅ ይችላል በሚል የጋዛ ነዋሪዎች ፍጆታዎችን እያከማቹ ሲሆን የምግብ ዋጋም ንሯል።

ነጋዴዎች እና አቅራቢዎች ጦርነቱ እንደገና ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ትርፍ ለማግኘት የምግብ ፍጆታን በመደበቅ የአቅረቦት እጥረት እየፈጠሩ መሆኑን አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የስድስት ልጆች እናት የሆኑትና ከጋዛ ተፈናቅለው በኻን ዩኒስ የሚኖሩት ኒቭን አል ሙግራቢ " ሁል ጊዜ ሰላም መሰማት ሲጀምር አዲስ ስጋት ይከሰታል።እናም ጦርነት እንደገና ሊጀምር ይችላል የሚል ስጋት አለን" ብለዋል።

" በጋዛ ቤቴን አጥቻለሁ። ከቤተሰቦቼ ጋር እዚህ ለመኖር ወስኛለሁ።ምክንያቱም የተኩስ አቁም ስምምነቱን አላምነውም።መፈናቀል አስመርሮናል"

እኝህ እናት ጨምረውም በኻን ዩኒስ ዋና ገበያ ያሉ ነጋዴዎች ለምግብ ፍጆታ የሚጠይቁት ዋጋ በሰዓታት ውስጥ እንደጨመረም ገልጸዋል።

" ምንም እንኳን የምግብ ፍጆታ ዋጋ በድንገት 30 በመቶ ቢጨምርም የሰላሙ ዘላቂነት ላይ እምነት ስለሌላቸው ሰዎች እየሸመቱ ነው። ሁሉም ሰው እርዳታ ይቆማል የሚል ስጋት አለው" ብለዋል።

በዲር አል ባላህ የሚኖሩት የስድስት ልጆች አባት የሆኑት ኻሊድ ሃላስ በበኩላቸው ውሃ፣ መብራት እና መጠለያ ድንኳን እንደሌለ ተናግረዋል።

ሃላስ ከጋዛ ከተማ ሹጃ ኢያ ከተባለ አካባቢ ለበርካታ ጊዜ ለመፈናቀል ተገደዋል።

" ሹጃኢያ አካባቢ ሙሉ በሙሉ ዝግ ነው።ተኩስ ወደ ተቀሰቀሰበት የአትክልት መሸጫ ገበያ ሄጀ ነበር። ምንም ጥበቃ የለንም። በአካባቢው የማያባራ ተኩስ ነው ያለው። እዚያ ያለው ሕይወት ሙሉ በሙሉ ወድሟል" ብለዋል ሃላስ።

የስድስት ልጆች አባት የሆኑት ኻሊድ ሃላስ
የምስሉ መግለጫ, በዲር አል ባላህ የሚኖሩት የስድስት ልጆች አባት የሆኑት ኻሊድ ሃላስ በበኩላቸው ውሃ፣ መብራት እና መጠለያ ድንኳን እንደሌለ ተናግረዋል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአንድ ሳምንት በፊት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ስምምነት ከተደረሰ አንስቶ ወደ ጋዛ የሰብዓዊ ድጋፎች እየገቡ ነው።

ሆኖም በስምምነቱ መሠረት ሐማስ ሰኞ ዕለት ሕይወታቸው ያለፈ 28 የእስራኤል ታጋቾችን አስክሬን ባለመመለሱ እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገቡ አቅርቦቶችን እንደምትገድብ አስጠንቅቃለች።

ሐማስ በበኩሉ የታጋቾች አስክሬን ለመለየት ችግር እንደገጠመው ገልጿል።

እስካሁን የሰባት ታጋቾች አስክሬን ለእስራኤል የተመለሰ ሲሆን የተጨማሪ ሁለት ታጋቾችን አስክሬን ረቡዕ እንደሚመለስ ሐማስ ገልጾ ነበር።

ፍሌቸር በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ሐማስ የሁሉንም የሞቱ ታጋቾች አስክሬን ለመመለስ ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል።

እስራኤልም እንደተስማማችው በሳምንት ውስጥ እርዳታ የጫኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ መፍቀድ እንዳለባት ገልጸዋል።

ፍሌቸር በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪዎች ሕይወት በእነዚህ እርዳታዎች ላይ ጥገኛ መሆናቸውን እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እርዳታ ያለ ገደብ እንዲገባ ግፊት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ወደ ጋዛ የሚወስዱ ተጨማሪ መንገዶች እንዲከፈቱ እና የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን ለመፍታት ሁለቱ ወገኖች እውነተኛ፣ ተጨባጭ የሆነ እና ችግር ፈች መንገዶችን እንዲከተሉ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊው፤ " ከሰላማዊ ሰዎች እርዳታዎችን ማቀብ ግን የመደራደሪያ ነጥብ አይደለም" ብለዋል።

ወደ ጋዛ የሚያስገባው የራፋህ መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ጦርነት ከተከሰተ አንስቶ በአብዛኛው ተዘግቶ ነው የቆየው።

በአውሮፓውያኑ 2025 መጀመሪያ ላይ በተደረሰው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ድንበሩ ጉዳት የደረሰባቸውን ፍልስጤማውያንን ለሕክምና ለማስወጣት በሚል ተከፍቶ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር አካል የሆነውና በጋዛ እርዳታን የሚቆጣጠረው ኮጋት ባለሥልጣን በራፋህ በኩል ሰብዓዊ እርዳታ እንደማያልፍ ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል። ባለሥልጣኑ እንዳሉት በየትኛውም ደረጃ ላይ እንዲህ ዓይነት ስምምነት ላይ አልተደረስም ብለዋል።

የተመድ ባለሥልጣንም በጋዛ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደረሰው ጥቃት እጅጉን እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ማንነታቸውን የደበቁ የሐማስ ታጣቂዎች ስምንት ፍልስጤማውያንን በአደባባይ የገደሉ ሲሆን ይህም በጋዛ ነዋሪዎች ዘንድ ስጋትን ፈጥሯል።

የአሜሪካው ማዕከላዊ አዛዥ አድምስ ብራንድ ኩፐር በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ፅሑፍ ሐማስ በጋዛ ሰላማዊ ሰዎች ላይ መተኮስ እና ጥቃት መፈፀም እንዲያቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ኩፐር ሐማስ የተደረሰውን ታሪካዊ ስምምነት እና የትራምፕን 20 ነጥቦች የሰላም ዕቅድ ያለምንም ማጓተት እንዲያከብር አሳስበዋል።

ሐማስ በበኩሉ ዒላማ ያደረገው ወንጀለኞች እና የእስራኤል ተባባሪዎችን ነው ብሏል።

በስምምነቱ መሠረት እስራኤል ሁሉንም የሞቱ ታጋቾቿን ለመቀበል 15 የፍልስጤማውያን አስክሬኖችን እንደምትመልስ ተስማምታለች።

እስራኤል የ45 ፍልስጤማውያን ታጋቾችን የመለሰች ሲሆን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴርም ይህንኑ ረቡዕ እለት አረጋግጧል።ይህም በእስራኤል የተመለሱ አጠቃላይ አስክሬኖችን ቁጥር 90 አድርሶታል።

ሆኖም የታጋቾች አስክሬን መዘግየቱ በእስራኤል በኩል ቁጣን ፈጥሯል።

በጋዛ ከሞቱት ታጋቾች አንዱ የሆነው አሚራም ኩፐር ልጅ ሮተም እርሱ እና ሌሎች የታጋቾች ዘመዶች "ይህንን ለመታገል ራሳችንን እያበረታን ነው" ብሏል።

" ሐማስ ተጨማሪ ታጋቾችን መልቀቅ እንደነበረበት እና እንዳለበት ግልጽ ነው፤ ግን እየቀለዱ ነው " ሲልም አክሏል።