ሐማስ በጋዛ የውስጥ ጥቃት ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ተዋጊዎቹን ማሰመራት ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሐማስ ወደ 7,000 የሚጠጉ የጸጥታ ኃይሉን በቅርቡ በእስራኤል ወታደሮች የተለቀቁትን የጋዛ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር በድጋሚ መጥራቱን ከአገር ውስጥ የተገኘ መረጃ አመለከተ።
ቡድኑ ወታደራዊ ልምድ ያላቸውን አምስት አዳዲስ ገዥዎችን ሾሟል። አንዳንዶቹ ቀደም ሲል በታጠቂ ክንፉ ውስጥ ብርጌዶችን ይመሩ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።
ትዕዛዙ የተላለፈው በስልክ እና በጽሑፍ መልዕክቶች ሲሆን ዓላማውም "ጋዛን ከሕገ ወጥ እና ከእስራኤል ተባባሪዎች ለማፅዳት ነው።"
ተዋጊዎቹ በ 24 ሰዓታት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉ አዟል።
ከጋዛ የወጡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት የታጠቁ የሐማስ አባላት ከፊሎቹ የሲቪል ልብስ ለብሰው ሌሎቹ ደግሞ የጋዛ ፖሊስን ሰማያዊ ዩኒፎርም ለብሰው በበርካታ አካባቢዎች ተሰማርተዋል።
በጋዛ ከተማ ሳብራ መንደር ሁለት የሐማስ ከፍተኛ ኃይል አባላት በዱጉሙሽ ጎሳ ታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ከተገደሉ በኋላ ውጥረቱ በከፍተኛደረጃ ጨምሯል።
ከተገደሉት አንዱ የቡድኑን ወታደራዊ መረጃ የሚመራው የሐማስ የትጥቅ ክንፍ ከፍተኛ አዛዥ ኢማድ አቀል ልጅ ነበር።
አስከሬናቸው በመንገድ ላይ መጣሉ ቁጣን ከመቀስቀሱም በላይ ሐማስ ከፍተኛ ምላሽ ይሰጣል የሚል ግምት እንዲጨምር አድርጓል።
የሐማስ አባላት ከ300 የሚበልጡ የዱግሙሽ ታጣቂዎች ተተኳሽ እና ፈንጂ ይዘው የሚገኙበትን አካባቢ ከብቧል።
ሐማስ አንድ የዱጉሙሽ ጎሳ አባል ሲገድል፣ ሌሎች 30 ሰዎችን አግቷል ተብሏል።
የጎሳው የጦር መሳሪያዎቹን በጦርነቱ ወቅት ከሐማስ መጋዘኖች የዘረፋቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ለዓመታት በእጃቸው የነበሩ ናቸው።
ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ጋዛን ማን እንደሚያስተዳድር እርግጠኝነት በሌለበት በዚህ ወቅት የሐማስ እንቅስቃሴ የሚጠበቅ ነበር።
ይህም ሐማስ ትጥቅ እንዲፈታ የሚጠይቀውን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛ ምዕራፍ የሰላም ዕቅድን ሊያወሳስብ የሚችል ቁልፍ ጉዳይ ነው።
በውጭ አገር የሚገኙ የሐማስ ባለስልጣን ስለጉዳዩ በቀጥታ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
"ለሌቦች እና በእስራኤል ወራሪ ለሚደገፉ ሚሊሻዎች ጋዛን መልቀቅ አንችልም። መሳሪያችን ሕጋዊ ነው ... ወረራውን ለመቋቋም እና ወረራውን እስከቀጠለ ድረስ ይቆያሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በጋዛ የፍልስጤም አስተዳደር ውስጥ ለዓመታት ያገለገሉ እና ጡረታ የወጡ አንድ የደህንነት መኮንን ግዛቱ ወደ ሌላ ዙር የእርስ በእርስ ደም መፋሰስ እያመራ ነው ብለው እንደሚሰጉ ተናግረዋል።
"ሐማስ ምንም ለውጥ አላመጣም። አሁንም ቡድኑን ለማቆየት ብቸኛው መንገድ መሳሪያ እና ሁከት እንደሆነ ያምናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ጋዛ በጦር መሣሪያ ተጥለቅልቃለች። በጦርነቱ ወቅት ከሐማስ መጋዘኖች ዘራፊዎች በሺህ የሚቆጠሩ የጦር መሣሪያዎችን እና ጥይቶችን ዘርፈዋል። አንዳንድ ቡድኖችም ከእስራኤል ድጋፍ አግኝተዋል።"
"ይህ ለእርስ በርስ ጦርነት ጥሩ ግብዓት ነው። የጦር መሳሪያ፣ ብስጭት፣ ትርምስ እና የተሰባበረ እና የተዳከመውን ሕዝብ ለመቆጣጠር ተስፋ የሚሰንቅ ቡድን አለ።"
በጋዛ የሚኖሩት የሰብዓዊ መብት ባለሙያው ካሊል አቡ ሻማላ፣ ሐማስ ሥልጣኑን ያስረክብ ወይም የዕቅዱን ተግባራዊነት ለማደናቀፍ ይፈልግ እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል ።
"የጋዛ ነዋሪዎች በርካታ አቀጣጣይ ምክንያቶች በመኖራቸው ውስጣዊ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳለ ጥርጥር የለውም ነው።"
ሐማስ በደረሰበት ከፍተኛ ጫና የሠላም ዕቅዱን ለመቀበል መገደዱን ተናግረዋል።
"በፀጥታ ጉዳዮች ውስጥ መሳተፍን ጨምሮ በማናቸውም መንገድ ተጽእኖውን ለማስቀጠል የሚያደርገው ቀጣይ ሙከራ ስምምነቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና የጋዛን ነዋሪዎች የበለጠ ስቃይ ውስጥ ሊከተት ይችላል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።
ይህም የሰላም ስምምነቱን ያሰናክለዋል በሚል በጋዛውያን ዘንድ ጥልቅ ስጋት ተፈጥሯል።















